ETHIO12.COM

የአየር ሃይልና አየር ወለድ አስደማሚ ገድል በሶማሊያ ሰማይ – አልሸባብ ጉያ የገቡት ቀይ ለባሾች

Se kildebildet

ግንቦት 26 ቀን 2013 አየር ኃይላችን በሶማሊያ ሰማይ…..ለፀረ-ሽብር ዘመቻ የምዕራብ ሶማሊያ ዋና ከተማ በሆነችው ባይደዋ ከተማ አውሮፕላን ማረፊያ አንድ እስኳድሮን የኢትዮጵያ አየር ሃይል ተዋጊ ሄሊኮፕተር ቤዝ መስርቶ ግዳጅ መፈፀም ከጀመረ ቀናት አስቆጥሯል።

ከተዋጊው ሄሊኮፕተር በተጨማሪ በተለያዩ የግዳጅ ቀጣናዎች ለሚገኙ እግረኛ ተዋጊ ሃይላችን ሎጀስቲካዊ አቅርቦትን የሚያቀላጥፉ በተጠንቀቅ ደረጃ አንድ ላይ የሚገኙ የትራንስፖርት ሄሊኮፕተሮችም ግዳጅ እየተጠባበቁ ነው።

17:00 ሰዓት (በወታደራዊ ሰዓት አቆጣጠር)

ዓይንና ጆሮዋቸውን በከፍተኛ ንቃት ከፍተው ከወታደራዊ መገናኛቸው መረጃ የሚጠባበቁት የስኳድሮን አዛዥ አንድ በፍጥነት መከወን የሚገባው ትዕዛዝ ደረሳቸው።ከላይ ባልኳችሁ ወታደራዊ ሰዓት ማለት ነው።

ከባይድዋ ከተማ 45 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ አንዲት የገጠር መንደር በእግረኛ ሃይላችን የማያዳግም ምት ከተበታተነው የአልሸባብ ሃይል – አምስት በተዋጊ ሽብርተኛ ቡድኑ ወሳኝ ስፍራ ያላቸው አመራሮች መመሸጋቸው ነበር ትዕዛዙን የወለደው ግዳጅ።

ወትሮውንም ትዕዛዝ ያግኙ እንጂ ሽብተኛውን አሳምረው ማደባየት የሚችሉበቱ ባለ ብሩህ አዕምሮዎቹ ወጣት በራሪ መኮንኖች – ቴክኖሎጂ ምስጋና ይግባውና – መዳረሻቸውን መነሻቸው ላይ እርግጠኛ ሆነው የተዋጊ ሄሊኮፕራቸውን አቅጣጫ አስተካክለው ግዳያቸውን ለመጣል ከነፉ።ሁለት በቅርብ ርቀት ተከታትለው ይበሩ የነበሩት የአየር ንስሮቻችን ተዋጊ ሄሊኮፕተሮች የሽብር አመራሮቹ የመሸጉበት የገጠር ቀበሌ ደርሰው ቁልቁል ሲመለከቱ ግን ያልተጠበቀና ግዳጃቸውን ለመፈፀም የማያስችል አንድ እክል ገጠማቸው።

በለስ ላይቀናቸው ይሆን?

ለማንኛውም ታሪኩን እንቀጥል።17:30 ሰዓት /አሁንም ወታደራዊ ነው/ከፊት ቀድሞ ሁነቱን የተመለከተው መልከ-መልካምና ቆፍጣናው በራሪ መኮንን ያየውን ጉዳይ ለጠቅላይ ማዘዣ በፍጥነት አስተላልፎ ተለዋጭ ትዕዛዝን ለመስማት ጆሮውን አቅንቶ መጠባበቅ ጀመረ።ምን ይሆን?ነገሩ እንዲህ ነው።

…ቀደም ሲል የነገርኳችሁ የሽብር ቡድኑ አመራሮች የኢትዮጵያ ተዋጊ ሄሊኮፕተር ስኳድሮን መኖሩን ያውቁ ነበርና ቢመጣብን ብለው አንድ ሰይጣናዊ ክፉ ውጥን ወጥነው ኖሯል።በዚያች የገጠር መንደር የሚገኙ ህፃናትን በሙሉ ሰብስበው በሄሊኮፕተሩ ዒላማ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ ባሏቸው ቦታ ሁሉ ሰብሰብ ሰብሰብ አድርገው ማታለያ መጫዎቻዎች አዘጋጅተው ነፍስ የማያውቁትን ንፁሃን ለሰለባነት ጭዳ ይሆኑ ዘንድ አስቀምጠዋል።

በጠቅላይ ሰፈር በወታደራዊ አመራር ጥበብ የተካኑቱ መሪዎች በአንፃሩ ሌላ መላ ዘየዱ።ይህ ዘዴ በፍጥነት ወደ ወታደራዊ ትዕዛዝ ተቀየረናም ተለዋጭ ትዕዛዝ ሲጠባበቅ ከነበረው ወጣት በራሪ መኮንን ጆሮ ደረሰ።ትዕዛዙም።”ምንም ዓይነት ዕርምጃ ሳትወስድ ወደ ጠቅላይ ሰፈር ተመለስ።”የመልስ ጉዞውን ሲጀምር ሁለተኛው ሄሊኮፕተርም ተከተለው።ወጣቱ በራሪ መኮንን “ምን ታስቦ ይሆን?” ጥያቄው ነበር።ሁለቱ ሄሊኮፕተሮች የመልስ ጉዟቸውን ሳይጨርሱ ከጠቅላይ ሰፈር ሌሎች ሁለት ሄሊኮፕሮች ተነስተው ወደ ገጠሪቷ መንደር በመምጣት ላይ ናቸው።

እነዚህኞቹን መጪዎች ከበፊቶቹ የሚለያቸው ነገር ነበር።ያም በአስገራሚ ፍጥነትና ቅልጥፍና በየትኛውም ቦታና ሁኔታ ማንኛውንም ውስብስብ ግዳጅ በቅፅበት በመከወን የተራቀቁ ፈርጣም ባለ ንቁ አዕምሮና አካል ሆነው በስልጠና የበቁ ልዩ ሃይሎችን ይዘዋል።

ለሽብርተኞቹ ዕይታ በማይመች ሁለት አቅጣጫ ሁለቱም ሄሊኮፕተሮች የያዟቸውን ሳተና ባለቀይ መለዮዎች በአስገራሚ ፍጥነት በገመድ ሲወርዱ ያየን – ምን ዓይነት ብቃት ነው ያስብሉ ነበር።ልዩ ሃይሎቹ የመንደሯን መውጫ መግቢያ አጥረው እንዲህ ተብሎ ሊገለፅ በማይችል ወታደራዊ ስልት የመንደሯን ቤቶች ሙሉ ለሙሉ በፍተሻ አካለው አምስቱን ሽብርተኛ አመራሮች በቁጥጥር ስር ሲያውሉ፣አመራሮቹ የተማመኗቸውን ጥበቃዎች ያለጥይት ተኩስ ያስወገዱበት ሁናቴ ድንቅ ነበር።

የአልሸባብ ሽብርተኛ ቡድኑ አምስት አመራሮች ከተያዙ በኋላ በባለቀይ መለዮቹ ብርቱ ምት የተቆለፉት ጠባቂዎችም ለጊዜው ካሸለቡበት ፍዘት ነቅተው በተጨማሪ ምኮኝነት ቁጥር ማብዣ ሆኑ።የልዩ ሃይሉ ፈታሽ ቡድን አካባቢውን በጥንቃቄ ሲፈትሽ በየዛፎች ላይ በጥንቃቄ የታሰሩና ያለማቋረጥ ይቀርጹ የነበሩ ስምንት ካሜራዎችን አገኙ።

አልሸባብ ሆዬ ለካስ – የጀግናው አየር ሃይላችን ስልጡኖቹን ተዋጊ ሄሊኮፕተሮች ጠላቴን እስካገኘሁ ህፃናቱ ቢገደሉስ ምን አገባኝ ብሎ ጭፍን እርምጃ የሚወስድ መስሏቸው ኖሯል።ወስዶ ቢሆን ኖሮ ደግሞ ያንን ለዓለም ህዝብ አሳይቶ ኢትዮጵያን ማሳጣት።ንፁሃኑ ህፃናት አንዳች ነገር ሳይሆኑ ብቻ ሳይሆን የጥይት ዘር አንድም ሳይተኮስ 19:00 ሰዓት (ያው በወታደራዊ መሆኑ ነው) – ሁሉም ነገር ተጠናቀቀ።ሰራዊታችን ህዝባዊ ነው ስንል እንዲህ ያሉ ሀቆችን በመንተራስ ኩራት ነው።

በነገራችን ላይ ይህ የሆነው ከጥቂት ዓመታት በፊት ነው።ጸሃፊው በሶማሊያ በነበሩ ግዳጆች መለስ ቀለስ እያለ የመዘገብ እድል አግኝቶ ነበርና በአይኑ በብረቱ የተመለከተው እውነት ነው።”ድል ለጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን”

ሻምበል አስቻለው ሌንጫ – FDRE Defense Force – የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት


Exit mobile version