Site icon ETHIO12.COM

ከፍተኛ ውድመት በደረሰባት የሰሜን ሸዋዋ አጣዬ ከተማ የመንግስት አገልግሎት ነገ ይጀመራል

በሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬ ከተማ አስተዳደር የመንግስት አገልገሎት ማስጀመሪያ ስነ ስርዓት መድረክ ዛሬ ተካሂዷል።

ከሶስት ወራት በፊት በአካባቢው በተፈፀመ ጥቃት አጣዬ ከተማ ከፍተኛ ሰብዓዊና ንብረት ወድሟል።

በዚህም ሩብ ሚሊዮን ገዳማ ዜጎች ተፈናቅለዋል የመንግስት አገልግሎትም ተቋርጦ ቆይቷል።

በዛሬው ዕለትም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴዔታ ዶክተር አህመዲን መሀሐድ የተሰበሰበ የአገልግሎት ተቋማት የቢሮ ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል።

”በከተማ የደረሰባት ጥፋት ልብ ሰባሪና ሰላማዊ ማህበረሰብ የማይወክል ነው ያሉት ዶክተር አህመዲን፣ አራት አይነት የድጋፍ ደረጃዎች እየተተገበሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም መሰረታዊ 1ኛ የዕለት ደራሽ ድጋፍ፣ 2ኛ ሀብትና ንብረታቸው የወደመባቸውን መደገፍ፣ 3ኛ በግጭቱ ጥፋት ምክንያት የጠፋውን መልካም ድባብ ለመሠለስ እርቀ ሰላም ማካሄድና በመጨረሻም በጉዳት ምክንያት የተቋረጠውን የመንግስት አገልግሎት ማስጀመር ነው ብለዋል።

እንደ አንድ ተወላጅና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊ የመንግስት ስራ ማስጀመሪያ አገልግሎትን ለማስጀመር ከሚመሩት ሚኒስቴር መስሪያ ቤትና ከተለያዩ ወዳጆች በማስተባበር ያሰባሰቡትን የቢሮ መገልገያ ቁሳቁስ አስረክበዋል።

የመንግስት አገልግሎት ተቋማት መጀመሩ ከተማዋ ወደነበረበት ሰላም ለመመለስ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልፀው፤ለዚህ ተፈፃሚነት ግን የመንግስት ሰራተኞች ቁርጠኝነት ይጠይቃል ብለዋል።

የሰሜን ሸዋ ምክትል አስተዳዳሪ ዋሲሁን ብርሀኑ በበኩላቸው ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት የደረሰበትን አጣዬ ከተማና አካባቢውን ወደነበረበት ለመመለስ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።

ይህ ድጋፍም ከተማዋን ዳግም ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠልፀዋል።

የአጣዬ ከተማ ከንቲባ አቶ አገኘሁ መክቴ በበኩላቸው ተፈናቃዮችን በሙሉ ለመመለስና ሕግ የመኖሩ ማረጋገጫ በመሆኑ የመንግስት አገልግሎት ለማስጀመር ሲሰራ ቆይቷል።

በዕለቱ የተደረገው የቁሳቁስ ድጋፍም የከተማ አስተዳደሩን ጥረት ለማገዝ የጎላ ፋይዳ እንዳለው ገልፀዋል።

ከነገ ጀምሮ መንግስታዊ አገልግሎት ወደ ስራ ይመለሳል፣ ቀደም ብለው አገልግሎት የጀመሩ ተቋማትም የተጠናከረ አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል ነው ያሉት።

ነዋሪዎችም በአሉባልታ ሳይሸበሩ ወደነበሩበት አካባቢ በመመለስ ከተማዋን ለመገንባት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የፀጥታ ስራው ቀዳሚ ተግባር ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ ዳግም ግጭት እንዲቀሰቀስ ለማድረግ ትንኮሳዎች ስለሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሁሉ በጥንቃቄ መታየት አለበት ብለዋል።

የአጣዬ ከተማ ነዋሪዎች ለድጋፉ አመስግነው፣ነገር ግን አሁንም ያለስጋት የመኖር ዋስትናን እንዳላገኙ ገልፀው፤ የመኖር ዋስትናቸው እንዲረጋገጥ መንግስት እንዲሰራ ጠይቀዋል – (ኢዜአ)

Exit mobile version