ETHIO12.COM

የፌዴ.ም.ቤት አፈጉባኤ ለአውሮፓ ህብረት የስራ ሃላፊዎች-ወ/ሮ ዳግማዊት ለኔዘርላንድ ጠ/ሚ ከጠ/ ሚ ዐቢይ የተላከ ደብዳቤ አደረሱ

ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አደም ፋራህ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን መልዕክት ለአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቻርለስ ሚሼል እና ለአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ዩርሱላ ቮን ደር ላየን አድርሰዋል፡፡

አፈጉባኤው ከአውሮፓ ህብረት አመራሮች ጋር ኢትዮጵያ ሰላማዊ፣ ነፃ፣ እና ፍትሓዊ ምርጫ ለማድረግ እያደረገች ያለው ጥረት፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር፣ በትግራይ እየተደረገ ያለው የሰብአዊ ድጋፎችና ሌሎች የጋራ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

በዚህ ወቅትም የአውሮፓ ህብረት የስራ ሃላፊዎች በትግራይ ክልል ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ በአግባቡ እንዲደርሳቸው የሚደረገው ጥረት ይበልጥ መጠናከር እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

የስራ ሃላፊዎች በትግራይ የተፈጸመውን የሰብአዊ መብት ጥሰት አስመልክቶ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽን ጋር በጋራ የጀመረው የምርመራ ሂደት የሚበረታታ ነው ማለታቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያመለክታል፡

የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለኔዘርላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ሩቴ የተላከ ደብዳቤን አደረሱ፡፡

ደብዳቤውን ለሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ እና የውጭ ንግድ እና ልማት ትብብር ሚኒስትር ሲግሪድ ካግ አስረክበዋል፡፡

በዚህ ወቅትም ከሚኒስትሯ ጋር በተለያዩ ጉደዮች ላይ ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡

በውይይታቸው ወቅትም በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ፣ በመጪው ሃገራዊ ምርጫ፣ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ድርድር እና በኢትዮ ሱዳን የድንበር ውዝግብ ዙሪያ መምከራቸውንም ገልጸዋል፡፡ via . FBC


Exit mobile version