Site icon ETHIO12.COM

በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫን ተከትለው የሚነሱ ክርክሮች ካሉ ለማስተናገድ ፍርድ ቤቶች ዝግጁ መሆናቸው ተገለጸ


በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫን ተከትለው የሚነሱ ክርክሮች ካሉ ለማስተናገድ ፍርድ ቤቶች ዝግጁ መሆናቸውን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት መዓዛ አሸናፊ ተናገሩ።

በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ከ2014 እስከ 2018 በጀት ዓመት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ላይ ከፌዴራልና ክልል ፍርድ ቤቶች አመራሮች፣ የፖሊስና ወታደራዊ ፍርድ ቤት፣ የማረሚያ ቤት፣ የሕግ ባለሙያዎችና ሌሎች የፍትሕ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።

መድረኩን የከፈቱት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ እንዳሉት፤ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ሶስት ግቦች በማስቀመጥ እየተሰራ ይገኛል።

አንደኛው ግብ የዳኝነት ነፃነት፣ ገለልተኝነትና ተጠያቂነት ሲሆን ሁለተኛው የዳኝነት ቅልጥፍና ተደራሽነት መሆኑን ገልጸዋል።

ሶስተኛው ግብ ለዳኝነት አገልግሎት አስተዳደራዊ ድጋፎችን ማጠናከር መሆኑን አንስተው፤ በነዚህ ግቦች ላይ ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል።

“ከ2014 በጀት ዓመት ጀምሮ የሚተገበረው ስትራቴጂክ ዕቅድም እነዚህን ጉዳዮች ተግባራዊ ለማድረግ ይሰራል” ብለዋል።

ባለፉት ሶስት ዓመታትን የዳኝነት ነፃነትና ተጠያቂነት ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው፤ “ይህም የሕግ የበላይነትን፣ የመንግስትን ቅቡልነት ያስተናግዳል፤ ኢንቨስትመንትን ያበረታታል” ብለዋል።

በአሁኑ ጊዜ ፍርድ ቤቶች በነፃነት እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።

በፍርድ ቤቶች እየተተገበረ ያለው ማሻሻያ ዋና ዓላማ ፍርድ ቤቶች በህዝብ ዘንድ ተዓማኒነት እንዲያተረፉ ማድረግ እንደሆነም ተናግረዋል።

ፍርድ ቤቶች ጥቂት ቀናት የቀረውን 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ተከትሎ ለሚመጡ ክርክሮች ፍርድ ቤቶች ዝግጁ መሆኑን ገልፀው፤ ፍርድ ቤቶች ብቁ ውሳኔ ሰጭ ሆነው እንደሚያገለገሉ አረጋግጠዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ፣ መንግስት፣ ፓርቲዎችና ህዝቡም በፍርድ ቤቶች ላይ ተቋማዊ እምነት እንዲያሳድሩም ፕሬዚዳንቷ አስገንዝበዋል።

Exit mobile version