Site icon ETHIO12.COM

“ኢትዮጵያውያን በተፈተንን ቁጥር እንደ ወርቅ ማንፀባረቃችንን…»ሻምበል አስቻለው ሌንጫ

ከመቆየታችን በላይ ማቆያችን….
“ሳቅ ፈገግታ ደስታን ሁሌ የምናየው፣
ሀገር በነፃነት ፀንታ ስትኖር ነው።”

ክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ
* * * * *
ፍካታችንን ለማክሰም ፣ ደስታችንን ለማጨለም ፣ ተስፋችንን ለመንጠቅ ከውስጥ እስከ ውጭ በተቀናጀ ሴራ የሚዶልቱብን ጠላቶቻችን አንድ ነገር ያውቃሉ።
እሱም -‘ሀገር ስትታመም ዜጋው ጤና ማጣቱን’።

አንድ ነገር ግን አበክረው ያጤኑ አይመስልም።ኢትዮጵያውያን በተፈተንን ቁጥር እንደ ወርቅ ማንፀባረቃችንን።

እኛ ፣ እኛ ነንና በአሁንነት ብቻ ተመስጠን ለደመ-ነፍሳዊ ቆይታ የምንዳክር ሃሳብ የለሾች እንዳንሆን ሆነን የተፈጠርንም ነን።

ባዕዳኑ የሚለኩን በከሃዲያኑ ጥቂት ባንዳዎች ልቦለዳዊ የእብለት ትርክት ከሆነ “እርማችሁን አውጡ” እንላቸዋለን።

ለዚያም ነው ትላንትን አልፏል ብለን እንደ አሮጌ ቁና አሽቀንጥረን ሳንጥል በጎውን ከመጥፎው በሚያነፅር የትዝታ ሰፌድ አንገዋለን ለዛሬያችን የሚበጅ የሃሳብ ጭማቂ የምንጠምቀው።

ለዚያም ነው አሁንን/ዛሬን/ በመኖራችን ውስጥ ከትላንት ጋር እያስተያየን ከመፃኢ-ነጋችን ጋር እያስማማን ከእኔነት እየፈለቀ ወደ እኛነት ባህር የሚቀላቀል ሲዋሃድ እያደገ እየተለቀ የሚገዝፍ ተግባር በመከወን ምልልስ ደፋ ቀና የምንለው።

ለዚያም ነው ነገን ዛሬ ላይ እየተለምን በብሩህ ተስፋ እየኳልን የሚጨበጥ ርዕይ ይዘን ለዚያ ስኬት በከፍተኛ ሃይል ተሞልተን የምንጓዘው።

ለዚህ ደግሞ ታላቁ የህዳሴ ግድባችን ዋቢ ይሆነናል።

የሀገርነትን ትርጉም ብሎም የአንጡራ ታሪክ ባለቤትነትን “ከኛ ወዲያ ላሳር” ብንል ቅንጣት የምናፍርበት ነገር አይኖርም።

ኢትዮጵያውያን ስንመራረቅ “ዕድሜና ጤና ይስጥህ” እንባባላለን።

ረጅም ዕድሜ ቢኖር ያለ ጤና ዋጋ ስለሌለውም አይደል የምንወደውን ሰው ስንመርቅ ከእድሜው ጋር ጤናን አዳብለን የምንመኝለት?

ረጅም እድሜ አድሏቸው በተቸራቸው የዕድሜ ቆይታ ማየት የሚሹት፣እንዲሆን የሚፈልጉት ሳይሆንላቸው ሲቀር “ወይ ዕድሜ ዘልዛላ ይህን ልታሳየኝ ነው የጎለትከኝ” ብለው ሀዘን ያቀጨመው ፊታቸውን ያሳዩን አዛውንቶች ባይገጥሙን እንኳን መኖራቸው አያጠራጥርም።

ለሰው ልጅ ዕድሜ ወይንም መቆየት በራሱ ብቻውን ግብ እንዳይደለ አስረጂ ይሆነናል።

ዛሬ ላይ ሀገራችንን አሳምመው እኛ ዜጎችን ጤንነት በማሳጣት መኖራችንን እንድናማርር የሚሹ ተስፋና ደስታችንን ለመንጠቅ የሚውተረተሩ የውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ጠላቶች በጠራራ ፀሃይ የጦር አውርድ ቀረርቶ ሲያሰሙ እያስተዋልን ነው።

ተፈጥሯዊ ፀጋ ሳንነፈግ ፣ ለነፃነቱ ቀናዒ የሆነ ህዝብ እያለን ፣ በጥንታዊ ስልጣኔ ገናናነታችን ብዙ ተብሎልን የነበርን እኛ ከታሪክ ስብራታችን አገግመን ፣ እኛው በኛው ተካክመን ትንሳኤያችንን ለማብሰር በደከምን ስለምን ጦር ይሰበቅብናል? ብለን ብንጠይቅ መልከ-ብዙ ምላሾች እናገኛለን።

ዋናው ቁም-ነገር ሀገር ስትታመም እያንዳንዱ ዜጋ ጤና ማጣቱን ማስተዋል ፣ ያለጤና ደግሞ ዕድሜም ረብ የለሽ መሆኑን ማጤን ላይ ነው።

ለዚህም ነው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በየሙያ መስኩ ፣ በምድር ሃይል ፣ በአየር ሃይል ፣ በባህር ሃይል እና በሳይበር ሀይል ተደራጅቶ ሀገርን አሳምሞ ዜጋን ጤና ከሚነሳ ማንኛውም የውስጥም ሆነ የውጭ ጠላት በጀግንነታዊ ተጋድሎ እየተከላከለ የሚገኘው።

ጀግናው ወጥቶ-አደር ከመቆየቴ በላይ ማቆያዬ ብሎ ያምናል።ማቆያው / የሱ ብቻ ሳይሆን የመላው ዜጎች/ ማቆያችን ሀገራችን ኢትዮጵያ ነች። ያለ ኢትዮጵያ የኛ ብቻ መቆየት ምንም ነውና።

እኛ የበዙ ተስፋዎች ከፊት ለፊታችን ይጠብቁናል። ኢትዮጵያችን ያለ አንዳች ጥርጥር ታላቅ ትሆናለች። ዜጎቿም ዕድሜን ከጤና ጋር አግኝተው ደስታቸውን የሚያበዙባት ምድር ትሆናለች።

ለዚያም ወጥቶ-አደሩ ሙያው ሀገርና ህዝብን ለመታደግ ማንኛውንም ጠላት በጀግንነት ተፋልሞ ማሸነፍ ፣ የሀገር ሉዓላዊነትን አስከብሮ አስተማማኝ ሰላም ማፅናት ነውና ፤ ይህንን በፅናት እያደረገው ይገኛል።”ከመቆየቴ በላይ ማቆያችን” ብሎ።ስለምን? ስለኢትዮጵያና ህዝቧ።ጋሽ ጥሌ “ሁሉም በሀገር ነው” ብሏልና

ኢትዮጵያ ታሸንፋለች. ሰኔ 7 ቀን 2013-

ሻምበል አስቻለው ሌንጫ via defense force Fb

Exit mobile version