ETHIO12.COM

“ኑ ! የወልቃይት ምድር ነጻ ወጥቷል” በስደት የሽሽት ኑሮ ላይ የነበሩ አማሮች ወደ ወልቃይት ጠገዴን ሰቲት ሁመራ ተመለሱ

በአሸባሪው ሕወሃት ግፍ ምክንያት ከወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ተሰደው የነበሩ አማራዎች ወደ ቀያቸው ሲመለሱ ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው።

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 08/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ነዋሪዎች በአሸባሪው ሕወሃት ላለፉት 30 ዓመታት ግፍ ሲፈጽምባቸው ቆይቷል፡፡ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ነዋሪዎች ግፉ ሲበዛ የመከራ ጽዋውን አልችል ሲሉ ቀን እስኪወጣ በሚል በተለያዩ የዓለም ክፍል በስደት ቆይተዋል፡፡ አንድ ቀን ወደ ቀያቸው እንደሚመለሱ እና በሀገራቸው ሠርተው እንደሚኖሩ ተስፋም ያደርጉ ነበር፡፡

በአሸባሪው ሕወሃት ግፍና በደል ሲደርስባቸው ሀገራቸውን ለቀው ለስደት የተጋለጡት እና ከ30 ዓመታት በላይ በሱዳን ካርቱም በስደት ላይ የቆዩት የወልቃይት ጠገዴ አማራዎች የክልሉ መንግሥት ከሱዳን መንግሥት ጋር በመነጋገር ባደረገላቸው ጥሪ መሰረት 270 ስደተኞች ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።

የወልቃይት ጠገዴ የሰቲት ሁመራ ከተማ ሕዝብ ከስደት የተመለሱትን ወገኖቹን አቀባበል አድርጎላቸዋል። ወደ ወልቃይት አማራ መኖሪያችሁ እንኳን በደህና መጣችሁ ብለዋቸዋል፡፡ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ አስተዳደር ምክትል አስተዳዳሪ እና የሰላም እና የሕዝብ ደኅንነት መምሪያ ኀላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ” እንኳን ደህና መጣችሁ ከሕዝባችሁና ከቤተሰባችሁ ጋር ኾናችሁ የተገኘውን ተቃምሰን አብረን እንኖራለን ” ብለዋል።

“በማኀበር ተደራጅታችሁ አልያም በግልም ቢኾን ሥራ እንድትሠሩ መደረግ አለበት። ትልቁና ዋናው ነገር አብሮ መሥራት በጋራ ማደግ ስለኾነ እርስ በእርስ ልንደጋገፍ ያስፈልጋል። በከተማው ምንም ችግር የለም እንዳትሰጉ ሰላም ነው፤ እኛ እስካሁን ስምንት ወራችን ነው፤ በሑመራ አንድም ሰው አልሞተም አንዳችም ችግር አላጋጠመንም ሰዎች በውጭ ኾነው የሚያወሩትን አትስሙ ከሁሉም የጸጥታ ኀይሎች ጋር የከተማችንን ሰላም እያስጠበቅን እንገኛለን ” ብለዋል።

ከወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ተሰደው ከቆዩት መካከል ማለደ ንጉሴ አንዱ ነው፡፡ ወጣት ማለደ ” በአሸባሪው ሕወሃት ምክንያት ነው የተሰደድኩት፤ አዛውንቱን፣ ወጣቱንና ጎልማሳውን እየገደሉ ኖረዋል፤ ሟቾች እንደ ሰው እንኳን አልተቀበሩም፤ ምክንያቱም አማራ በመኾናቸው ብቻ።

መከራው ቢጸናብን ተሰደናል” ነው ያለው። ሌላኛው ከስደት ተመላሽ ማለደ ማሞነህ አሸባሪው ትህነግ ባለፉት ዓመታት አማራዎችን ገድሏል፤ ንብረት አጥፍቷል። እኛን በመከራና ስቃይ ከሀገራችን እንድንወጣ አድርጎናል። 27 ዓመታት በስደት ቆይቻለሁ” ብሏል።

ወደ ሀገራችን እንድንመለስ እና አንገታችንን ቀና አድርገን እንድንሄድ የሕይወት መስዋእትነት ለከፈለልን ለአማራ ልዩ ኀይል፣ ለአማራ ሚሊሻ እና ለጀግናው መከላከያ ሠራዊት ምስጋና እናቀርባለን ነው ያለው። ከስደት የተመለሱት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ተወላጆች በስደት ላይ ላሉ ሁሉ “ኑ ሀገራችን ሰላም ናት፤ የወልቃይት ምድር ነጻ ወጥቷል፤ ወልቃይትን በጋራ እናልማት” ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። ዘጋቢ፡- ያየህ ፈንቴ – ከሁመራ

Exit mobile version