Site icon ETHIO12.COM

ዜና ምርጫ – አራት ሺህ ታዛቢዎች ተሰማሩ፤ አማራ ክልል ፖሊስ ጥሪ አስተላለፈ

በአገሪቷ ምርጫ በሚካሄድባቸው አካባቢዎቸ 4 ሺህ የሚጠጉ ታዛቢዎች ይሰማራሉ

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ኅብረት

በመጪው ሰኞ ለሚካሄደው 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ 4 ሺህ የሚጠጉ የምርጫ ታዛቢዎችን እንደሚያሰማራ የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ኅብረት ገለጸ።ኅብረቱ በድምጽ መስጫው እለት በድምጽ አሰጣጥና ቆጠራ እንዲሁም ድምጽ ከተሰጠ በኋላ ያለውን የምርጫ ሂደት በተመለከተ የሚኖረውን ትዝብት አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

የኅብረቱ አባል አቶ ሳህለስላሴ አበበ ምርጫው በአገሪቱ ዴሞክራሲን ለማስፈን እንደሚያስችል በማመን በዜጎች ዘንድ ተዓማኒ እንዲሆን ታዛቢዎችን በማሰልጠን እንዲሰማሩ ተደርጓል ብለዋል።የኅብረቱ የታዛብነት መርሃ ግብር በሳይንሳዊ መንገድ በተመረጠ የመረጃ አሰባሰብ ላይ የተመሰረተ መሆኑንና በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ተመሳሳይ መጠይቆች እንዳሉት ገልጸዋል።

በምርጫው እለት እንደ ምርጫ ጣቢያዎች ብዛት ተመጣጣኝ ዘዴ በመጠቀም እስከ ሁለት ሺህ ታዛቢዎች የሚሰማሩ ሲሆን ቀሪዎቹ በአካባቢያቸው የምርጫ ጣቢያ በተንቀሳቃሽና ቋሚ ታዛቢነት ይሰማራሉ ብለዋል። የኅብረቱ የምርጫ ትዝብት አስተባባሪ አቶ ቢኒያም አባተም “ታዛቢዎች በቀን ቢያንስ አምስት ጊዜ አዲስ አበባ ለሚገኘው የኅብረቱ የመረጃ ማዕከል የጽሁፍ መልዕክት ይልካሉ” ብለዋል።

ድምጽ መስጠት ከመጀመሩ በፊት ያለውን ዝግጅት በተመለከተ፣ ድምጽ መስጠት ሲጀመር፣ ቀን የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱንና የድምጽ ቆጠራው ተጠናቆ ውጤት ከተለጠፈ በኋላ ሪፖርት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።የምርጫ ታዛቢዎች ነፃና ገለልተኛ እንዲሆኑ በማሰብ ሁሉም ከሲቪክ ማህበራት መመልመላቸውንና የማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ አባል እንዳልሆኑ በቃለ መሀላ ጭምር ማረጋገጣቸው ተገልጿል።ኅብረቱ ከ175 በላይ የሲቪክ ማኅበራትን ያቀፈና ምርጫው ፍትሃዊና ተዓማኒ ሆኖ በሠላም እንዲጠናቀቅ ችግሮች ከተከሰቱም አፋጣኝ መፍትሄ እንዲያገኙ ለማስቻል የተቋቋመ አገር በቀል ድርጅት ነው።

ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

በመጪው ሰኞ የሚካሄደው ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡ ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመሆን የድርሻውን እንዲወጣ ፖሊስ ጥሪ ቀረበ።የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር በሰላም ማስከበር ዙሪያ ዛሬ ማምሻውን መግለጫ ሰጥተዋል።ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ በዚሁ መግለጫቸው እንዳስታወቁት፤ ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ፖሊስ አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በማጠናቀቅ የተቀናጀ ስምሪት አድርጓል።በዚህም የፀጥታ ኃይሉ ከክልል እስከ ቀበሌ በሚገኙ ሁሉም የምርጫ ክልሎችና ጣቢያዎች ስምሪት ተሰጥቶ አስፈላጊውን ጥበቃ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

መራጩ ህዝብም ያለምንም የፀጥታ ስጋት ወጥቶ ይሆነኛል፣ ያስተዳድረኛል ብሎ ያመነበትን የፖለቲካ ፓርቲ እንዲመርጥም የፀጥታ ኃይሉ አስፈላጊውን ሁሉ ጥበቃ ያደርጋል ብለዋል።ቀደም ብሎ ከክልል እስከ ቀበሌ ለሚገኘው የፀጥታ ኃይል በምርጫ ወቅት ስለሚያከናውናቸው የህግ ማስከበር ስራዎች አስፈላጊው ስልጠና መሰጠቱንም ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የክልሉ የፀጥታ ኃይል ከፌደራል ፖሊስ፣ ከመረጃና ደህንነት፣ ከመከላከያና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት የተውጣጣ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝም ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።

ህብረተሰብ በተለይም ወጣቱ ለሰላም መጠበቅ ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመሆን የአካባቢውን ሰላም ነቅቶ በመጠበቅ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅም ለህግ የበላይነት መከበር ህዝቡ የራሱን አስተዋፅኦ እንዲያደርግም ኮሚሽነር ተኮላ አመልክተዋል።ፖሊስ ከምርጫ በፊት፣ በምርጫው ዕለትና በኋላ ምን ማድረግ እንዳለበት ለአባላቱ አስፈላጊው ግንዛቤ መፈጠሩን ጠቅሰው፤ ምርጫውን አስመልክቶ እስካሁን ያጋጠመ ነገር አለመኖሩንም ገልጸዋል።በክልል ደረጃ የተቋቋመው ግብረ ኃይል በአንድ ማዕከል ሆኖ ማንኛውንም ሊያጋጥም የሚችል ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመከላከል ሲሰሩ መቆየቱንና ይህም እስከ ምርጫው ማብቂያ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። ኢዜአ

Exit mobile version