Site icon ETHIO12.COM

24 ሠዓታት በውትድና ህይወት ክፍል 9 – “እኛ ፈንጂው ላይ ተንከባለን…እናንተ…

ተራኪው መኮንን በወቅቱ የነበሩት ትዝታውና እውነታው ይበልጥ ይገለጥለት ዘንድ ቀንና ዓመተ ምህረቱን መጥቀስ ፈልጓል። ቀኑ ሰኔ 14 ሲሆን ዓመተ ምህረቱ 1992 ዓ.ም ነው።

ሠራዊቱ ከሠፈረበት ካምኘ ተነስቶ ጥቂት ኪሎ ሜትሮችን ከተጓዘ በኋላ አንድ ተራራማ ሥፍራን ተገን አድርጎ በየክፍሉ በሠልፍ ተቀመጠ። ግዳጅ እንዳለና የተልዕኮው ዝርዝር ወቅቱ ሲደርስ እንደሚገለፅ አመራሮች አሳወቁ።

ጉዞው የምሽት ነበር። በገላጣ መሬት ላይ ሳይሆን ሸጥን ተከትሎ መሆኑ ታወቀ።የሠው ሐይል ቁጥጥር ተደረገ።የጉዞ ቅደም ተከተል ወጣ።በሂደቱ በምንም ተዓምር ድምፅ መሠማት እንደሌለበት ማስጠንቀቂያ ተሰጠ።

ጉዞው የሚደረገው በክፍለ ጦር ደረጃ ነው። በትንሹ የድሽቃና የመትረየስ ሸንሸሎች፣ ሞርተር ከነሙሉ ግብአቱ ለአብነት ቢነሳ ድምፅ ሰጪዎች ናቸው። እንኳን ሙሉ ትጥቅ ተይዞ መሬቱ ባዶ እጅ በድቅድቅ ጨለማ የሚሞከር አይደለም።መብራት ቀርቶ አንፀባራቂ የሆኑ ማናቸውም ነገሮች ክልክል ናቸው።

ሠዓቱ ደርሶ ጉዞው ተጀመረ። ያ ሁሉ የሰው ሐይል ከነሙሉ ትጥቁ ተንቀሳቅሶ ከዛላንበሣ ከተማ በስተ ሰሜን ሶቢያ የተባለ ሥፍራ ሲደረስ አንዲት ድምፅ አልተሰማም ነበር። ውትድርና የማይቻል የሚመስለውን መቻል መሆኑን በወቅቱ አንድ መሪ የተናገሩት በተግባር ታየ።

ተራኪው የግል ገጠመኙን መቼም አይረሳም።የምሽት ጉዞ ከመጀመሩ በፊት ከቀን ጀምሮ ከፍተኛ የራስ ምታት ቁርጥማትና ብርድ ብርድ ይለው ነበር።ከተንቀሳቃሽ የህክምና ቡድኑ ጋር ሄደው ሲመረመር ሙቀቱን ያዩ ባለሙያዎች በወቅቱ አዲግራት አካባቢ የነበረው ክፍለ ጦር እንዲሄድ ወስነው ነበር። በፍፁም በጀ አላለም። ማስታገሻ ወስዶ እራሱን በሽርጥ አሥሮ ከጦሩ ጋር ተጉዞ ከሥፍራው ደርሷል።

ከክፍሉ አልለይም ማለት ብዙ አያስገርምም።በወቅቱ ክፍላቸው ወደ ግዳጅ ሊሠማራ መሆኑን የሰሙ በሆስፒታል የነበሩ አባላት ህመማቸው ሳይሻላቸው ሁሉ ከነ ገዋናቸው ጠፍተው ከጓዶቻቸው ጋር ይቀላቀሉ ነበር።

መኮንን የነበረበት ክፍለ ጦር በወቅቱ የተሰጠው ግዳጅ በዘላንበሳ ግንባር ሶቢያ ንዑስ ግንባር ድሬ ፣ አላድሬ ፣ ጥሲኒ ፣ ድድሺና ሞለክሲቶ ፣ እያለ እስከ ዝነኛው የአይጋ ተራራ ግርጌ የመሸገውን ጠላት ምሽግ በማጥቃት ማስለቀቅ ነበር።

በዚያ የመሬት ገፅታ ግዳጅ ላይ ማጥቃት በህይወት የመትረፍ እድሉ ሃምሣ ሃምሣ በጭራሽ ሊሆን አይችልም።አሥር ከመቶ ነበር ማለት ይቀላል።

ተራኪው ይሄንን ሲል ምክንያት አለው።በወቅቱ ጠላት ለነበረው ሐይል የምሽግ አሰራር ጥበብ ዛሬም ድረስ አድናቆት አለው።የቡድን መሣሪያዎች መጠጊያዎች ላይ ታስረዋል።ምድብተኞቹ ደግሞ ሲከፋ መሸሽ የማይችሉ አካል ጉዳተኞች ናቸው።

በወቅቱ የመሐንዲስ ሙያተኞች እንዳረጋገጡት የተጠመዱ ፈንጂዎች ከዓለም አቀፍ ህግ ውጭ የተተከሉ ሳይሆን የተዘሩ ነበሩ ማለት ይቻላል።ምድር ላይ ብቻ ሳይሆን በዛፎች ላይ ሁሉ ፈንጂዎች ተጠምደው ነበር።በምድር ላይ የተዘሩትም ፀረ ሰውና ፀረ ተሽከርካሪ ተቀናጅተው ነው።

በግንባሩ የምሽግ ሰበራ ግዳጅ የተሠጣቸው ክፍሎች ለሊቱን ድምፅ ሳያሰሙ፣ በመሐንዲስ እየተደገፉ፣ የጠላት ምሽግ ተጠግተው “ሰ” ሠዓቱን መጠበቅ ነበረባቸው። ከሰባሪ ቀጥሎ ደምሳሾች በቅርብ ርቀት ተጠግተው ተቀምጠዋል። “ሰ” ሠዓት – ጀምር የሚል ትዕዛዝ የሚሰጥበት ቅፅበት ነው።

የቦንብ ወርወሪዎች ተግባር ፣ የቡድን ድጋፍ ሰጪ መሣሪያ ምድብተኞች ሚና፣ አመራር ቢሰዋ ወይም ቢቆስል ተክቶ የሚያዋጋው ፣ የአግላዮች ሥራ ተለይቷል።በሚገርም ሁኔታ ብዙዎች ያንን ሁሉ መሠናክል አልፈው የጠላት አፍንጫ ሥር ቦታ መያዝ እና ማደር ችለዋል።

ስለጨለማው አንድ ነገር መጨመር ሁኔታውን የበለጠ ይገልፃል ብሎ ያምናል ተራኪው።የጦርነት ታሪኩን ለመዘገብ ከኮርም ሆነ ማዕከል የተመደቡ የሚዲያ ሙያተኞች ነበሩ።ተጠግተው እንዲያድሩ ከጦሩ ኋላ እንዲጠጉ ትዕዛዝ ተቀብለው መንገዱን የሚያውቅ መሪ ተመድቦላቸዋል።እነሱ ግን መንገድ ስተው ከጦሩም አልፈው ፈንጂ ወረዳ ይደርሳሉ። ለወገን ጦር ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የጠላት ፈንጂ በማስወገድ ላይ የነበሩ የወገን መሐንዲሶች አስቁመው ሲጠይቁዋቸው ሁኔታውን ይነግሯቸዋል።

ባለሙያዎቹ በሉ ተመለሱ።ጦሩን አልፋችሁ መጥታችኋል ።አሁን የምትገኙት በነፍስ ወከፍ መሣሪያ ተኩስ የውጤት ርቀት ላይ ነው ብለው ይመልሷቸዋል።ከጠላት ወረዳ ከራቁ በኋላ አንዱ”የሀገሬን የድል ዜና እሠራለሁ ብዬ የሻዕቢያ ሚዲያ ዜና ግብዓት ሆኜ ነበር።ለትንሽ ተረፍን” ማለቱ ከድሉ በኋላ በሠራዊቱ ጋ ከገጠመኞቹ አንዱ ሆኖ ይነገር እንደነበር ያስታውሳሉ።

የመጠጋቱ ሥራ ለአብዛኞቹ ቢሳካም የተወሰኑቱ ከክብደቱ አንፃር ማለፍ አልቻሉም።የሰበራ ሠዓት ደርሶ ሲመለከቱ ምን ይሻላል? ለሚለው ጥያቄ አንዳንድ አባላት መፍትሔ አመጡ።መፍትሔው ግን ከውሳኔዎች ሁሉ የላቀ ነበር።

“እኛ ፈንጂው ላይ ተንከባለን እናመክናለን።እናንተ እለፉና በጉጉት ለሚጠብቃችሁ ህዝባችሁ ድል አብስሩ” አሉ

አማራጭ አልነበረም።ተፈቀደላቸው።ከአበው በወረሱት ወኔ በገባቸው ልክ ለውድ ሀገራቸው ክብር ሥጋቸው ለአሞራ እንኳን እንዳይተርፍ ሆኖ በፈንጂ አየር ላይ ተበተነ።ሌሎች እነሱ በከፈቱት መንገድ ገብቶ ድልን ተቀናጀ። ይሄን ገድል ፈፅሞ የአውደ ውጊያ ሜዳሊያውን በቤተመንግስት ቤተሰቦቹ የተረከቡትን የቤንሻንጉል ተወላጁ ምክትል አሥር አለቃ በሽር ሙስጠፋን ተራኪው ከበርካታ የዚህ ግንባር ጀግኖች ሠማዕታት ውስጥ በአብነት ያነሳል።

በእቅዱ መሠረት ተጠግተው ያደሩት ቦንብ ወርዋሪዎች እራሳቸውም እየተወረወሩ ታሪክ ሠሩ። በሦሥትና አምስት ደቂቃዎች ምሽግ ተቆጣጠሩ።ለሀገራችሁ ነው የተባሉት የሁለቱም ሀገር ወጣቶች ወደቁ።

በማግስቱ የድል ዜና በምድሪቷ ናኘ።ዛላንበሳ ላይ ብሔራዊ ሠንደቅ ዓላማችን በክብር ተውለበለበ።ድሉ የእኛ የኢትዮጵያውያን ቢሆንም ለቅሶው የሁለቱም ሀገራት እናቶች ሆነ።

የጦርነት ጥሩ የሠላም መጥፎ እንደ ሌለ በዚህ ግንባር የረገፈው የሰው ህይወት በቂ ማሳያ ነው ። ቁስሉን በወታደር ቤት የከፋ የሚያደርገው የሚገነባው ፍቅር ነው ይላል ተራኪያችን።

አማራው ከደቡብ ፣ ኦሮሞው ከሶማሌው ፣ አፋሩ ከጋምቤላ ፣ ቤንሻንጉሉ ከሐረር ፣ ትግራዩ ከድሬው ፣ አዲስ አበቤው ከመላው ኢትዮጵያ ጋር ቤተሰብ የሚፈጥርበት ሙያ ነው ውትድርና።ለአስተዳደር ተብሎ የተዘጋጁ የክልል ወሰኞች በፍቅር የሚፈርሱበት ፣ ኢትዮጵያዊ ወንድማማችነት የሚገነባበበት ተቋም ነው።

እንደ ዓይን ብሌን የሚመለከቱትን የኢትዮጵያ ገፀበረከት የሆነ ጓደኛ ሃያ አራት ሠዓት ባልሞላ ጊዜ ማጣት ከሞቱም በላይ ውጊያ ላይ ሲኮን ከነዩኒፎርሙ እንደ ነገሩ አፈር ማልበስ ያማል። ከጓደኞችህ ተለይተህ እኔን መሸኘት የለብህም ያሉት እናት ከውጊያ በኋላ ከልጃቸው ጋር እንደማይገናኙ ሲታሰብ ያንገበግባል። የበለጠ የሚያመው ደግሞ ስንት ህይወት ተከፍሎ የተያዘን መሬት ባልታወቀ ምክንያት ልቀቁ ሲባል እና የጦርነቱ ትርጉም ሲጠፋ እንቆቅልሽ ሲሆን ነው።

ቀጥሎ ያለው በኤርትራ ምድር ቆይታ ነው። የሃያ አራት ሠዓቱን በዚህ መግታት ግን ግድ ይላል።24 ሠዓታት በውትድርና ህይወት የመኮንኑ ትውስታና ትረካ ይቀጥላል።ሠላም!

ሻለቃ ፈይሳ ናኔቻ
ፎቶግራፍ Google image defense force FB

Exit mobile version