Site icon ETHIO12.COM

“…የኢትዮጵያን ህልውና የማስጠበቅ ጉዳይ የዜጎች ሁሉ የጋራ አጀንዳ ሊሆን ይገባዋል” ኦባንግ ሜቶ

Obang

በነገው እለት ለሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ ክንውን ዜጎች የድርሻቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ ሲሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ሜቶ ተናገሩ። የኢትዮጵያን ህልውና የማስጠበቅ ጉዳይ የዜጎች ሁሉ የጋራ አጀንዳ ሊሆን ይገባዋል ነው ያሉት።

የሰብአዊ መብት ተሟጋቹና የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ መስራች ኦባንግ ሜቶ በነገው እለት የሚካሄደውን ምርጫ አስመልክቶ ለኢዜአ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ለምርጫው ካርድ የወሰዱ ሁሉ ድምፃቸውን በመስጠት ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን እንዲጠቀሙ ሲሉ መልእክታቸውን አስተላለፈዋል።

የምርጫ ሂደቱ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍፁም የተረጋጋ ሆኖ እንዲከናወን ዜጎች የድርሻቸውን ሃላፊነት እንዲወጡም ጠይቀዋል። ለምርጫ ሰላማዊ ክንውን ተፎካካሪዎች፣ ደጋፊዎችና አጠቃላይ የዜጎች አገርን ታሳቢ ያደረገ የትብብር ሂደት ወሳኝ መሆኑንም ነው የገለፁት።

በውድድር ዓለም አሸናፊና ተሸናፊ መኖሩ ግድ ነው ያሉት አቶ ኦባንግ ውጤቱን በፀጋ መቀበል ደግሞ ከተፎካካሪዎች የሚጠበቅ ሃላፊነት መሆኑን ጠቅሰዋል። በውድድሩ ሂደት ቅሬታዎች ቢኖሩ እንኳን አሰራሮችን ተከትሎ ችግሩን መፍታት እንደሚቻል ተናግረዋል።

በምርጫ ሂደት ወቅቱን ጠብቆ መፎካከር ይቻላል፤ ኢትዮጵያን የማቆየትና ህልውናዋን የማስጠበቅ ጉዳይ ግን ለነገ የማይተው የዜጎች ሁሉ የጋራ አጀንዳ መሆኑን አብራርትዋል። ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች የግጭት እና የጥላቻ መንስኤ ከመሆን በመታቀብ ለጋራ አገር ተመሳሳይ አቋም ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል።

በዘንድሮው የምርጫ ፉክክር የተፎካካሪ ፓርቲ እና የገዥው ፓርቲ አመራሮች በአንድ መድረክ ተገናኝተው መልካም ምኞት መለዋወጣቸው የዴሚክራሲ ባህላችን እየዳበረ ለመምጣቱ ማሳያ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት ከውስጥም ከውጭም ጫናዎች ቢበረቱም ኢትዮጵያዊያን ለሌሎች በር ባለመክፈት በጋራ እንቁም ሲሉም መልእክታቸውን አስተላለፈዋል። ኢትዮጵያን ለመለወጥና የዴሞክራሲ ስርአትን ለማጎልበት በአንድ ልብ ልንሰራ ይገባልም ነው ያሉት።

የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማገሌዎች፣ ምሁራን የጸጥታ ሃይሎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአጠቃላይ ህዝቡ ለምርጫው ሰላማዊነት ሃላፊነቱን ይወጣ ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

Exit mobile version