Site icon ETHIO12.COM

‹‹ የኢትዮጵያ ጉዳይ የኢትዮጵያዊያን ብቻ ነው፤ ኃላፊነትም አደራም አለባቸው›› ዶ/ር አልማው ክፍሌ

ምርጫ ለሀገራችን ሰላምና ደህንነት ወሳኝ ጉዳይ ነው። ዲሞክራሲን የምንለማመድበት፣ በመረጥነው መንግስት የምንተዳደርበት፣ አሁን ከሚታዩና ከሚሰሙ አስከፊ ችግሮች ሁሉ የምንላቀቅበት መንገድ ቀያሽ ነው። ለምርጫው ስኬታማነት የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት ከፍ ያለ ነው ።በተለይም ሀጋራችን በተለያዩ ጉዳዮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ጫና ውስጥ በገባችበት በዚህ ወቅት ምርጫውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማጠናቀቅ ትልቁ የቤት ስራችን ነው ።

ምርጫ በዲሞክራሲያዊው ምርጫነቱ እንደ ምሳሌ ተጠቃሽ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ መፍጠር የምንችልበት እንደሆነም ይታመናል ። ለዚህም ሁሉም በምርጫው ተዋናይ የሆነ አካል ሕግንና ህግን ብቻ መሰረት አድርጎ መንቀሳቀስ ይገባል ። እኛም በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የህግና የታሪክ መምህር የሆኑት ዶክተር አልማው ክፍሌ ጋር በምርጫ ህጎች ዙሪያ ቆይታ አድርገናል። ሀሳቡንም እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

አዲስ ዘመን፡- ለምርጫ ስኬት የተቀመጡ የምርጫ ህጎች ምን ምን ናቸው?

ዶክተር አልማው፡- በአገራችን ዘጠኝ ያህል ታሪካዊ ምርጫዎች ተካሂደዋል። ስድስት እየተባለ የሚነገረው ኢህአዴግ የነበረበትን ዘመን ለመዘከር ታስቦ የተደረገ ይመስለኛል። በእነዚህ ጊዜያት በተለይም ስድስት ተብሎ በተወሰደበት ጊዜ በርካታ የምርጫ ህጎች ወጥተዋል። ነገር ግን እንድንነጋገር የተፈለገው ስኬትን መሰረት አድርገን በመሆኑ የባለፉትን ከአሁኑ ጋር በማነጻጸር ለማንሳት እንሞክራለን።

የፖለቲካ ምህዳሩ ብዙዎችን የሚያሳትፍ ከማድረግ አኳያ መጀመሪያ የተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 11/13/ 2011 ነው ፤ ይህ ህግ የፓርቲዎች የመመዝገቢያ ህግ ነው። ይህ መሻሻል ትልቅ ለውጥ አምጥቷል። ምክንያቱም ኢህአዴግ ስልጣኑን ለሌላ ላለመስጠት ሲል በ1984እና በ1997 ዓ.ም የወጣውን ህግ 1500 ደጋፊ ያለውና አባል ያፈራ ፓርቲ መመዝገብ ይችላል ይላል። ይህ ደግሞ ብዙ ፓርቲዎች እንዲፈጠሩ ያደርጋል። በዚህም አገሪቷ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት አላት ፤ አገሪቷ ዴሞክራሲያዊ ናት የሚል ገጽታ ለመገንባት የተጠቀመበት ነው። ሥራው ግን 1ሺ500 አባል የያዘ ፓርቲ 110 ሚሊዬን ባለባት አገር ውስጥ ከቤተሰብ እንደማይዘል ይታወቃል። ስለዚህም የእርስ በእርስ መተማመንን ለማጥፋት ሲል በስፋት ሲጠቀምበት ቆይቷል።

አሁን በወጣው ህግ ግን 10ሺ አባላት ብቻ ያለው ፓርቲ ነው መመዝገብ የሚችለው። ይህ ደግሞ መጀመሪያ 108 የነበረውን ፓርቲ ወደ 81 አወረደው። አዳዲስ መስፈርቶች ሲወጡ ደግሞ ዳግም በደንብ እየተጣራ ሄዶ በመጨረሻ ተወዳዳሪ የሚሆኑት 47ቱ ብቻ ነጥረው እንዲወጡ ሆነዋል። ከዚህ በላይ ህጉ ቢሻሻል ደግሞ ወደ አምስትና ሁለት የሚወርዱበት ሁኔታ ይፈጠር ነበር። ግን አሁንም ቢሆን ብዙ ልዩነት የፈጠረ ሥራ ተሰርቷል።

ምክንያቱም በ110 ሚሊዬን ህዝብ ውስጥ 10ሺህ ህዝብን ማቀፍ ብዙውን ማካተት ብቻ ሳይሆን አውቆ ለመስራትም ያግዛል። ጠንካራ ሀሳብ ያለው አደረጃጀት ለመፍጠር፣ ተደማጭነትን ለማምጣትና አገራዊ ራዕይን አስፍቶ ለማየት እንዲሁም ለመተግበር ከፍተኛ አስተዋዕጾ ይኖረዋል። በተመሳሳይ የአገርን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲፈጠሩም በር ይከፍታል።

ሌላው በህግ ደረጃ የሚታየው የጥላቻ ህግ መውጣቱ ሲሆን፤ የምርጫው ሂደት ሰላማዊ እንዲሆን ያደረገ ነው። እስከዛሬ በነበሩት ምርጫዎች ያላግባብ ሰዎች ሲዘረጠጡ ነበር፤ ብሔርና ማንነት ጭምር ይነካ ነበር። በ2012/ በወጣው ህግ ግን ይህ ሁሉ እንዲቆም እድል ሰጥቷል። ፓርቲዎች የራሳቸውን ሀሳብ የሚሸጡበትን፣ የፖለቲካ ማኒፌስቶና አማራጫቸውን የሚያሳዩበትን መንገድ ያሳየም ነው። ህዝብም ማን ምንድነው የሚለውን እንዲያይ ያደረገበት ነው። አላስፈላጊ አምባጓሮዎች እንዲወገዱም አድርጓል።

ሦስተኛው የምርጫ ህግ ደንብ ጸድቆ መውጣቱ ነው ፤ ከምርጫ ቦርድ አደረጃጀት ጀምሮ ያሉ ሥራዎችን በምን መልኩ መከናወን እንዳለባቸው ያስቀመጠና መመሪያ የሆነ ነው። ፓርቲዎች እንዴት ይወያዩ፣ እንዴት ይጣመሩ፣ የሚዲያ አጠቃቀማቸው ምን ይምሰል፣ ግብዓት እንዴት ይቅረብና መሰል ነገሮችን በሚገባ አስቀምጦ በዚያ አሰራር እንዲሄድ ያስቻለም ነው። ይህ ቢሆንም ፍጹምነት መጠበቅ የለበትም። ምክንያቱም ምርጫ ቦርድ በ1947 ተመስርቶ በ1948 የምርጫ ህግን ቢያወጣም ለይስሙላ እንጂ በሥራ ሲተገበር አልታየም። አሁን በትንሹ መሰረታዊ ለውጦች ከተደረጉ በኋላም ነው ዲሞክራሲን ለማረጋገጥ ወደ ጀማሪነት እየገባን ያለነው። ስለዚህም ሥርዓቱ መዳበሩ በራሱ ትልቅ ነገር እንደሆነ መወሰድ አለበት። ይህንን ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎችና መንግሥት ኃላፊነትን ወስደው ማሳደግ አለባቸው።

የጸረ ሽብር ህግ ጸድቆ በሥራ ላይ መዋልም የምርጫውን ስኬታማነት ሊያሳይ የሚችል ነው። አገርን የሚያተራምሱ ጽንፈኛ ኃይሎችን ለመመከት፤ የውጪ ጠላትን የሚሸሽጉና ሀሳባቸውን የሚያራምድ አካላትን ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አድርጓል። ተግባራቸውን የማያቆሙ ከሆነ ደግሞ በህግ እንዲጠየቁ መንገድ ከፍቷል። በዚህም አሁን አተራማሾች እየተጠየቁ በመሄዳቸው የምርጫው እንቅስቃሴ የተረጋጋ እንዲሆን እድል ሰጥቷል። ፉክክሩና መሰል እንቅስቃሴዎችም ሰላማዊ እንዲሆኑ መንገድ ጠርጓል። የሚፈናቀል፣ የሚሞትና የሚጎዳ የህብረተሰብ ክፍል እንዳይኖርም ብዙ መሻሻሎችን ያስገኘ ነው።

አዲስ ዘመን፡- በምርጫ ጉዳይ ላይ ከህግ አንጻር የመንግስት ሀላፊነት እንዴት ይገለጻል?

ዶክተር አልማው፡- መንግስት እንደ መንግስት የለውጥ ሀይል ነው። በዚህም ይህ መንግስት የለወጠውን ህግ ሳይሸራረፉ እንዲፈጸም ማድረግና ራሱም ፈጽሞ ማሳየት የመጀመሪያው ነው። በእርግጥ መንግስት በብዙ ነገሮች የተከበበ ነው። አብዛኛው አባላቱ ከኢህአዴግ የወጡ ናቸው። የለመደ አመላቸውን ሊተገብሩ ይችላሉና ይህንን ማስቆም የእርሱ ኃላፊነት ነው። ከህዝብ ተአማኒነትን ለማግኘት ብዙ ልፋትን ይጠይቃልና አባላቱ የነበረ መጥፎ አሰራሮችን እንዳይደግሙት በማድረግ ተዓማኒነቱን ማረጋገጥም ሌላው ኃላፊነቱ ነው።

ዋጋ ተከፍሎበት የመጣ ለውጥ ህጉን ተከትሎ እንዲሰራበት ካላደረገ ብዙ ኪሳራን በአገር ላይ ሊያስከትል ይችላል። ስለሆነም አንድ አገር ሉአላዊነቷ ተከብሮ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ አደረገች የሚባለው አራት ነገሮችን ስታሟላ ነው። እነዚህ አራት ነገሮችም የመጀመሪያው ገለልተኛ የሆነ የምርጫ ቦርድ ማቋቋም ፤ በሁለተኛ ደረጃ የሚነሳው ገለልተኛ የሆነ የፍትህ ተቋም ነው። ሦስተኛው ደግሞ ገለልተኛ የሆነ የሚዲያ አካል ፣ አራተኛው ተግባራዊ የሚሆን ህገመንግስት ናቸው። ስለዚህም እነዚህን ማቋቋም ብቻ ሳይሆን ሥራቸውን መደገፍና ውጤታማ እንዲሆኑ ማገዝ ይኖርበታል። ይሁንና በሥራቸው ጣልቃ ገብቶ ግራ ሊያጋባ አይገባም።

አዲስ ዘመን፡- ከህግ አንጻር የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ወቅት ሃላፊነት ምን መምሰል አለበት?

ዶክተር አልማው፡– የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ውድድር አገርን ለማዳን ከሆነ አገር ምን ትፈልጋለች የሚለውን ተከትለው መስራት የመጀመሪያ ኃላፊነታቸው ነው። ዲሞክራሲ ያለባት፤ የተረጋጋችና ልማቷ የተፋጠነ አገርን የሚፈልግ ፓርቲ መሆኑንም በተግባር ማሳየት ሌላው ኃላፊነቱ ነው። ምርጫው ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ቅቡልነት ያለው እንዲሆንም የህዝብን ስሜት ተከትለው መስራትና እምነታቸውን መስጠት አለባቸውም። የአላስፈላጊ ማንጓጠጥና ህግን መጣስንም በፍጹም ልብ መቃወም ይኖርባቸዋል።

ምርጫ በራሱ ግብ አይደለም። ምርጫ በራሱ ዲሞክራሲ ሊሆንም አይችልም። የዲሞክራሲያዊ ስርዓት መገለጫ አንዱ ባህሪ እንደሆነ ማወቅ አለባቸው። አገራችን አሁን በብዙ ችግሮች ውስጥ ነው ያለችው። የኑሮ ውድነቱ ከውጪ ጫናው ጋር ተዳምሮ ብዙ ፈተና እየገጠማት ነው። ብዙ ወጣቶችም ሥራ ይፈልጋሉ። ስለሆነም በምርጫ ወቅት የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህንን አስበው ሰላማዊ ምርጫ እንዲከናወን አባሎቻቸውን በደንብ መከታተልና ህጋዊነትን ይዘው እንዲሰሩ ማድረግ ኃላፊነት አለባቸው። ለአመጽ እንዳይነሳሱም ቁጥጥር ሊያደርጉ ይገባል።

ሁሉም ነገር ፍጹም ይሆናል ተብሎ ስለማይታመን ስህተቶች ቢኖሩም እንኳን ወደ ነውጥ ከመምጣት ይልቅ በህግ አግባብ መልስ ለማግኘት መሞከርም ይኖርባቸዋል። ለአገርና ለእውነት ታማኝ መሆንም አለባቸው። የሚወዳደሩት ህዝብን ወክለው እስከሆነ ድረስ ህዝብን አምነው ህዝባዊ መሆናቸውን በሥራቸው ጭምር ማሳየት ዋናው ኃላፊነታቸው ነው። በሰላማዊ መንገድ መከራከርና ሀሳባቸው እንዲያሸንፍ ማድረግም ይገባቸዋል። ሥርዓት ባለው መንገድ ምርጫው እንዲካሄድ ትብብር ማድረግም አለባቸው።

ገዢው ፓርቲ ህግ ፈጽሞ ማሳየት መቻል አለበት።ምክንያቱም ለሌሎች አርአያ ነው። ስለሆነም አጠቃላይ ፓርቲዎች ለሥነምግባሩ፣ ለህጉ መገዛት አለባቸው። ግልጸኝነትን መርህ ማድረግ፣ ተጠያቂነትና ቅቡልነት ያለው አሰራሮችን መከተል በምርጫ ወቅት ሊተገብሩት የሚገባ ኃላፊነቶች ናቸው።

አዲስ ዘመን፡- ለምርጫ ቦርድ ህግ የሰጠው ኃላፊነት እንዴት ይታያል ?

ዶክተር አልማው፡– ምርጫ ቦርድ ማለት ህዝብን በእውነት ዳኝቶ የወደፊት ተስፋውንና የአገሪቱን መሪ በካርዱ እንዲያስፈጽምለት የተቀመጠ አስፈጻሚ ነው። በዚህም ህዝብ የወከለው ሰራተኛ ነውና ለህዝብ የድምጹን እውነታ የሚገልጥለት ነው። የስልጣኑ ባለቤት ህዝብ ነው ፤ ሁሉም በአንድነት አስፈጻሚ ሆኖና ወስኖ ተገቢውን ውጤት ማምጣት አይችልምና በውክልና ህዝብ የሚያስቀምጠውና እምነቱን የሚሰጠው ተቋምም ነው። ስለዚህም ይህንን እምነቱን ማረጋገጥ የመጀመሪያው ኃላፊነቱ ነው።

ሌላው ኃላፊነቱ በምንም መልኩ አድሎአዊ ሊሆን አይገባውም። ገለልተኛ ሆኖ የህዝብን ድምጽ ለህዝብ መልሶ መስጠትም አለበት። የአኮረፉ፣ መንግስት ሊገለብጡና አገርን ሊያተራምሱ የተዘጋጁ ብዙ አካላት አሉና ከማንም ሳይወግን እውነቱን ለእውነተኛው ህዝብ ካላስተላለፈ አጋጣሚ የሚሰጥ ኃይል ነው የሚሆነው። ስለዚህም ታማኝነቱን በተግባር በገለልተኝነት ማረጋገጥ ይኖርበታል።

አዲስ ዘመን፡- በምርጫ ወቅት ለጸጥታ አካላት የተሰጠ ኃላፊነት ምንድነው ?

ዶክተር አልማው፡– በእስከዛሬው እንቅስቃሴ የጸጥታ አካሉ የኢህአዴግ እንጂ የህዝብ እንዳልሆነ በብዙ መንገድ ይነገራል። ወገንተኝነቱ ጭምር የመንግስት ነበር ማለት ይቻላል። ስለዚህም ይህ ምርጫ በለውጥ ውስጥ ያለበትን ሁኔታ የሚያሳይበት ነውና የእኔ ነው የሚለውን ህዝብ በማገልገል ታማኝነቱ ለህዝብ እንደሆነ ማሳየት የመጀመሪያው ኃላፊነቱ ነው። ከዚህ በተጓዳኝ ከሰራ ተአማኒነትን ሊያገኝበት የሚችልበት እድል የሚሰጠው ነውና ይህንን መጠቀም ይኖርበታል። አገራዊ ስንቅ ሰንቆ ኢትዮጵያን የማዳን ሥራ ማከናወንም ከምንግዜውም በላይ አሁን የተሰጠው ኃላፊነት ነው።

የሚችላቸውን ምርጫዎች በሚችለው ልክ 24 ሰዓት ሰርቶ የሚችላቸውን ጣቢያዎች ማስፈጸም አለበት። የማይችላቸውን ጣቢያዎች ምርጫ ብዙ አይነት ስለሆነ በዚያ መልኩ ለመስራት መሞከር አለበት። ለምሳሌ ጠቅላላ፣ የማሟያ፣ እንደገና የሚደረጉ ምርጫዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ስለሆነም ሁኔታዎችን አመቻችቶ አራዝሞ ማድረግ ይኖርበታል። ከዚያ ውጪ የማይችለው ውስጥ ገብቶ አገርን ችግር ውስጥ እንዳይከት መጠንቀቅ አለበት። የምርጫውን ውጤት ሳያረጋግጥ እንዲገለጽ መፍቀድ የለበትም። ስለዚህም ምርጫ ቦርድ ከመንግስት የበለጠ ይህንን አገር የማስቀጠል ኃላፊነት እንዳለበት አምኖ መስራት ይኖርበታል።

አዲስ ዘመን፡- ከምርጫ ጋር ተያይዞ የፍርድቤቶች ኃላፊነት እንዴት ይገለጻል?

ዶክተር አልማው፡- ፍርድ ቤቶች ከምርጫ ቦርድ ቀጥሎ ትልቅ ኃላፊነት ያለባቸው ተቋማት ናቸው። በመሆኑም እስከዛሬ ድረስ በነበራቸው አካሂድ መሄድ የለባቸውም። ምክንያቱም ገለልተኝነቱ አይታይባቸውም። የመንግስት ነበሩ ብሎ መውሰድም ይቻላል። ስለዚህም የመጀመሪያ ሥራቸው መሆን ያለበት ገለልተኝነታቸውን ለህዝብ ማሳየት ነው። ይህንን ሲያደርጉ ደግሞ በምርጫው ላይ የሚቀርቡ ችግሮችን በአግባቡ ህግን ተንተርሰው ፍትህ መስጠት መቻል አለባቸው። ምላሻቸውም ቢሆን አሳማኝና መረጃን ተገን ያደረገ ሊሆን ይገባዋል።

ፍትህ የሁኔታዎች ውጤት ነው። በዚህም በዓለም ላይ ፍርድ አያደላም የምንልበት ሁኔታ አይኖርም። ለመልከኛው፣ ለባለስልጣኑ፣ ላለው አለያም በደንብ ለሚናገረው ሊያደላ ይችላል። ድሃንም አገልግሎ አያውቅም። ነገር ግን በዚህ አገር ሁኔታ መሰረት የምንተክልባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አሉን። ከእነዚህ መካከል አሁን የሚደረገው ምርጫ አንዱ ነው። ለእውነት ሰርቶ ህዝብ ህዝብ መሽተት መቻል አለበት። መጨቆን በቃህ የሚባልበት ጊዜ ይህ ምርጫ ነውና ይህንን ማሳየት መቻል አለበት። ህዝብን ከጉልበተኛ አሰራር፣ ከሙሰኛ ጫና ነጻ ሊያወጣው ያስፈልጋል። የሀሳብ ልዕልና፣ የፍትህ፣ የሰላምና የዲሞክራሲ አገር እንዲሆንም ፍርድቤቶች በዚህ ምርጫ ትልቅ አቅም ሆነው ማለፍ ይኖርባቸዋል።

አዲስ ዘመን፡- ከምርጫው እንቅስቃሴ ጀምሮ እስከ ፍጻሜው ድረስ ያለው የውጪና የአገር ውስጥ ታዛቢዎችስ ሚና ከህግ አኳያ እንዴት ይታያል?

 ዶክተር አልማው፡– የታዛቢዎች ኃላፊነት የሚጀምረው ከቅድመ ምርጫ ጀምሮ ነው። በዚህም የሀብት ክፍፍሉ ፍትሀዊነት፣ ህጉ ፍትሀዊና ሁሉንም አቃፊ መሆኑን፣ የምርጫ አፈጻጸም ስርዓቱ ሚዛናዊነትን፣ ማስፈጸሚያ ህግጋቱ ጠንካራ ነወይና ማስፈጸም ይችላል ወይ የሚለውን በአግባቡ ይታዘባሉ፤ ይመረምራሉም። ከዚያ በመቀጠል የምርጫ ጣቢያው በአግባቡ መደራጀቱን ፣ የሚዲያ ክፍፍሉን ፍትሀዊነት ይመለከታሉ። የምርጫ ቦርድን ሥራ፣ የፍትህ ተቋማቱንና የመንግስትን ኃላፊነት መወጣት ይመረምራሉ። የፓርቲዎች አደረጃጀትንም ቢሆን በሚገባ ያያሉ። የምርጫ አያያዙን ከአተገባበሩ ጋር እያዛመዱ ይታዘባሉም።

በምርጫ ወቅት ደግሞ የምርጫ ጣቢያዎች በአግባቡ መደራጀታቸውን፣ ተመዝጋቢዎች ህግን ተከትለው መመዝገባቸውን፣ የግብዓት አቅርቦቱ የሚፈለገው ቦታ ላይ ደርሶ ዝግጁ ነወይ፣ በቂ ነው የሚለውን ይመለከታሉ። ምርጫው እየተከናወነ ሳለ ማዋከብ አለ፣ ጣልቃ ገብነቶች አሉ ወይ የሚለውንና የአስፈጻሚ አካላት ህግን ተከትሎ መስራት አለመስራታቸውን ይከታተላሉ፤ ይታዘባሉ።

የምርጫ ቦታ ምቹነትና የምርጫ ሰዓት መከበሩንም የሚከታተሉት እርሱ ናቸው ። አቆጣጠሩን፣ ውጤቱ በአግባቡ መሰነዱንና ውጤቱ ለህዝብ እንዴት እንደታወጀ የመታዘብ ኃላፊነት አለባቸው ። ይህ ሲሆን ደግሞ እንደሌሎቹ ተቋማት ገለልተኛ መሆናቸውን ፣የህዝብ መሆናቸውን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል ። ከተጭበረበረም እውነታውን ገልጾ በህግ እንዲታይ መከታተል መቻል አለባቸው ።

አዲስ ዘመን፡- ምርጫና የህዝብ ኃላፊነት በህጉ እንዴት ይሰናሰላሉ?

ዶክተር አልማው፡– ዜጎች በምርጫው ጊዜ ማድረግ ያለባቸው የጽሞና ጊዜውን በአግባቡ መጠቀምና ለአገር ይበጃል የሚሉት ላይ ለመወሰን መዘጋጀት ነው። ማንነታቸውን የሚገልጽ መታወቂያቸውን ይዘው ወደ ምርጫ ጣቢያ መሄድ አለባቸው። ሥርዓት ባለው መልኩ ምርጫውን መሳተፍ ይኖርባቸዋል ። ያለአድሎና ያለጥላቻ የሚፈልጉትን መምረጥ፣ እርዳታ ለሚፈልጉ ግለሰቦች እርዳታቸውን መቸር ይጠበቅባቸዋል። የምርጫ ደንብ ጥሰቶችን ሲመለከቱም በቸልታ ማለፍ የለባቸውም። ከዚያ ይልቅ ጊዜ ሳወስዱ ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ ትልቁ ኃላፊነታቸው ነው።

የምርጫ አስፈጻሚ አካሉ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ምርጫውን እንዲያስፈጽም በቻሉት ሁሉ መደገፍ አለባቸው ። ምቹ አካባቢን መፍጠርም ይጠበቅባቸዋል።

አዲስ ዘመን፡- የሚዲያው ሚናስ እንዴት ይታያል?

ዶክተር አልማው፡- ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው እንደሚባለው ሚዲያው ከሚያስተላልፈው መልዕክት ጋር በተያያዘ በጣም ትልቅ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት። በተለይም በምርጫ ወቅት የሚተላለፉ መልዕክቶች በጣም ጥንቃቄ የተመላባቸው ሊሆኑ ይገባል። ምክንያቱም አገር የሚያናውጥና ብዙ ነገሮችን የሚያበላሽ ሊሆን ይችላል። ስለዚህም አላስፈላጊ የሆኑ ውዥንብሮችን አለማስተላለፍ፣ ምርጫውን የሚያበላሽ ምህዳር አለመፍጠር፣ ከህግ ውጪ አለመንቀሳቀስ ይኖርባቸዋልም። ለአገርና ለህዝብ አገልጋይነታቸውን ገለልተኛ በመሆን ማሳየትም ይጠበቅባቸዋል።

ስለሆነም ሚዲያው ገለልተኛ ሆኖ እውነቱን መርምሮ እያወጣ ለህዝብ ይፋ ማድረግ አለበት። ተጠያቂነትንም ሊያሰፍን ይገባል። ነገር ግን አገርን በሚንድበት መልኩ ሊሆን አይገባም። ምክንያቱም ለእነዚህ አካላት አገርና ህዝብ አደራ ተሰጥቷቸዋል። በመሆኑም አደራቸውን በልተው ፓርቲ ማገልገል የለባቸውም።

አዲስ ዘመን፡- በምርጫ ወቅት አለመግባባቶች ሲፈጠሩ በምን መልኩ ነው የሚፈቱት ?

ዶክተር አልማው፡– አለመግባባት የሚኖር ጉዳይ ነው። እንደውም ፈረንጆቹ ኖርማል ነው ይሉታል። ስለዚህም ሁላችንም በአንድ አቋም ላይ እንድንወድቅ አይጠበቅም። ምክንያቱም የአቅም፣ የአመለካከት፣ የኢኮኖሚና የእውቀት ልዩነቶች በመካከላችን ይኖራሉ። በዚህም በአፈጻጸም ላይ ሰው ሊጠይቅ ይችላል። ያንን በአግባቡ ማስረዳት መቻልና በምክንያት ማሳመን ችግሩን ሊፈታ የሚችለው። ስለሆነም አለመግባባቶች በመተማመንና ወደ አንድ ሀሳብ ለመቅረብ በመሞከር ሊፈቱ ይችላሉ።

በህግና በህግ አግባብ እንዲሁም በሰለጠነ አካሄድ ብቻ ነው መፈታት ያለበት። የሰለጠነ አካሄድ ማለት ውይይታዊና ህጋዊ በሆነ መንገድ መስመር ማስያዝ ነው። ተበድያለሁ ያለ ፓርቲም በህግ አግባብ ጥያቄውን ማቅረብ በዳይ የሆነውም ራሱን ሳይሸሽግ እውነታውን አስረድቶ በመደጋገፍም ነው ችግሩ ሊፈታ የሚገባው። አለመግባባቶች የሚፈቱት አንዱን በማጥፋት አይደለም። በማሸነፍ ብቻ አገር እንደማይደራጅ አውቆ መሸነፍም ያስፈልጋል።

ለአብነት አንድ ፓርቲ ከ50 በላይ ድምጽ አምጥቶ ባለፈበት ወቅት አንድ ጣቢያ የአራቱ ድምጽ ስህተት ተፈጽሞ ቢታይ ካልተስተካከለልኝ አገር አጠፋለሁ ብሎ መነሳት ተገቢነት የሌለው ጉዳይ ነው። ምክንያቱም የአራት ሰው ድምጽ ተስተካከለም አልተስተካከለም የሚመጣ ለውጥ የለም። ስለዚህም መሆን ያለበት እውነታውን አጋልጦ ዳግም እንዳይከሰት አርሞ ማለፍ ነው። ከስልጣን ይልቅ አገርና ህዝብ እንደሚቀድም ሁሉም መረዳት ይገበዋል። አርቆ ማየት የዛሬው ሥራ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል።

ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ ስንቃኝ አሜሪካን ብቻን ብናነሳ ከምርጫ ጋር በተያያዘ ሦስት አሰላለፍ ይዛ ብቅ ብላለች። የመጀመሪያው ምርጫውን ማካሄድ የለባችሁም አለች። የሚሰማሽ የለም ስትባል ፣አይደለም በምርጫ እንዲሳተፍ ስሙም ህልውና እንዳይኖረው የሚፈለገውን በሽብር የተፈረጀውን ህወሓትን እርቅ አውርዱለት ስትል አሰማች። ምክንያቱም በዚህኛው ምርጫ እንደእርሱ የሚጠቅማት ማንም ስለማይኖር ጋሻጃግሬውን ተጠቅማ አገራችን ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖርባት ለማድረግ ጥረቷን አጧጧፈችው። ሆኖም ይህም አልተሳካላትም።

አሁን ደግሞ ሰላም አስከባሪ ሀይል እያሰለጠኑ ይገኛሉ። ምክንያቱም በምርጫው ላይ ውዥንብር ፈጥረው አገሪቷ ትረጋጋ በሚል መንፈስ ያስገባሉ። ይህ ደግሞ እንደነ ሶርያ እንድንሆንላቸው በመፈለግ የሚያደርጉት ነው። ምክንያቱም ሰላም አስከባሪ የገባበት አገር መቼም ሰላሙ ሊመጣ አይችልምና። ስለሆነም ፓርቲዎች ይህንን አውቀው በምርጫ ወቅት የሚፈጠሩ ማንኛውንም ችግር በህግና በህግ አግባብ እንዲፈታ መስራት ትልቁ ኃላፊነታቸው ነው።

ምርጫ ቦርድም ሆነ ፍርድቤቶች ይህንን ጉዳይ በቸልታ ሳያዩ ያለ አድሎ ትክክለኛ ፍትህን ለህዝብ መስጠት ይኖርባቸዋል። የኢትዮጵያን ጉዳይ ኢትዮጵያዊያን ብቻ ነው ኃላፊነትም አደራም ያለባቸው። አለዚያ ግን አገራችንን ማጣታችን አይቀርም።

አዲስ ዘመን፡- የምርጫ ውጤትን ከማሳወቅ አኳያስ ህጉ ምን ይላል?

ዶክተር አልማው፡– ምርጫን በሚመለከት ውጤት ተናጋሪው ምርጫ ቦርድ ብቻ እንደሆነ ያስቀምጣል። ሌላው አካል ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንዲያደርግ አይፈቀድለትም። በተለይም ተፎካካሪ ፓርቲዎች በምንም መልኩ ግምት ማሰማት የለባቸውም። ባደረጉት እንቅስቃሴና ወሬ ብቻ እኛ ተመራጭ ነን፤ በማኒፌስቶዋቸውም እኛ አንደኛ ነን የሚሉበት ጊዜ አብቅቷል። ሁሉም መስመሩን ይዞ ነው የሚጓዘው። እናም ምርጫ ቦርድ ውጤቱን ይፋ እስኪያደርግ ድረስ ማንኛውም ፓርቲ ህዝብን ውዥንብር ውስጥ ሊከት አይገባም። ይህንን የሚያደርጉ ከሆነ አገርን ከመናድ የተናነሰ ስራ እንዳልሰሩ ሊያውቁ ይገባል።

አሸናፊ ፓርቲ ለህዝብና ለአገር እንዲሰራ እውቅና መስጠት ከዚህ ሊጀምር ይገባል። ለዚህ ደግሞ ስርዓተ መንግስቱን እንዲያስተካክል አሸናፊውን ማገዝ ያስፈልጋል። ከዚያ ውጪ በምርጫ ጣቢያም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ሁከት መፍጠር አግባብነት የለውም። በህግም ያስጠይቃል።

አዲስ ዘመን፡- በምርጫው ዙሪያ ቀረ የሚሉት ነገር ካለ?

ዶክተር አልማው፡- መንግሥት፣ ፖለቲከኛውና ምርጫ ቦርድ ሁሉም ሥራቸውን በአግባቡ ሰርተው ህዝብ መሪውን እንዲመርጥ ማድረግ አለባቸው። ይህ ሲሆን አገር በሚቀጥለው የፖለቲካ ሴራ ውስጥ እንዳትገባ እድል ይሰጣታል። ቂም ይዞ ሥርዓቱን ለመገርሰስ ከመስራቱ ተላቆ ተገዢ እንዲሆን፤ ልማታዊነትን በተግባር እንዲያነሳ ያደርገዋል። እንዲረጋጋም ፍቱን መደኃኒቱ ይሆንለታል። በተለይ ተተኪው ትውልድ መልካም ስርዓትን ተምሮ አገር እንድትቀጥል ብዙ እንዲለፋ እድል ይሰጠዋል።

የሀሳብ ብልጫን አይቶ ስለሚያልፍም ለሚቀጥለው ምርጫ ሀሳብ እንጂ ጉልበት ያሸንፍን መርሁ አያደርግም። አገርን ከመተናኮልና ሌላ ጣልቃ ገብ አካላትን ከመጥራትም ነጻ ይሆናል። ስለሆነም ይህንን አስቦ በመሥራት ምርጫውን ማከናወን ያስፈልጋል። ከግል ጥቅም ይልቅ አገርና ህዝብን ማስቀደም የሁሉም ኃላፊነት መሆን አለበትም።

በሺዎች የሚቆጠሩ ሯጮች ሮጠው የሚያሸንፉት ደረጃ የሚይዙት ብቻ እንደመሆናቸው ሁሉ በምርጫም ሁሉም ፓርቲ ሊያሸንፍ አይችልም። ስለሆነም ፓርቲዎች ሁለተኛና ሦስተኛ ጭምር መውጣት ማሸነፍ ነውና ራሳቸውን ማዘጋጀት አለባቸው።

መንግስት የሚሆነውን አካል በብዙ መንገድ የሚሞግቱበትን እድል አግኝተውበታልና። እኔ ብቻ ያነሳሁት ሀሳብ ህዝባዊ ነው፤ የእኔ ሀሳብም ሆነ ቅስቀሳ ልዩ ነው። በዚህም እኔ ብቻ አሸንፋለሁ ማለት መጨረሻ ላይ የተሳሳተ ውሳኔ ውስጥ ይከታል። ስለሆነም ፓርቲዎች ከአሁኑ ራሳቸውን ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል። መሸነፍም እንዳለ ማወቅ ይገባቸዋል። ውሳኔው በካርዱና በመጨረሻዋ ሰዓት ላይ መሆኑንም መረዳት ይገባል። ህዝቡ አይቷል፣ ሰምቷልም ሙያ በልብ ብሎም እየጠበቀ ነው። እናም ለራስ ብቻ የተሳሳተ ግምት መስጠት አይገባም። ለአገራችንም ይህ አስተሳሰብ ይበጃልና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ይህንን ያስቡ ማለት እፈልጋለሁ።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2013

Exit mobile version