Site icon ETHIO12.COM

የእልቂት ዳንኪራ – ስጋቱ ብዙ ነው

ባህላዊ እሴቶቻችን እጅግ ግዙፍና ጥልቅ ናቸው። ወጎቻችን፣ ልምዶቻችን፣ እምነቶቻችን ሚስጥራቸው ብዙ ነው። ግዙፉ ባህሎቻችንና መላው የሴቶቻችን ሚስጥሮች አንድ አድርገው ባይዙን ኖሮ ዛሬ ላይ ለመድረሳችን ማንም እርግጠኛ መሆን አይችልም። በተለይም ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በራሱ በግብር ከፋዩ በበጀት ተደግፎ፣ በስትራቴጂና በስልት ከተረጨው፣ ላለፉት ሶስት ዓመት ደሞ ከጠመቀው የሴራ ማተራመስ ጋር ተዳምሮ እነዛ ያስተሳሰሩን ሚስጢሮቻችን እንደ ዓለት ባያቆሙን ኖሮ መጽሃፉ እንዳለው ” … በጠፋን” ነበር። ግን አለን። እንኖራለን። ነበርን!!

ከላይ ያነሳሁት አሳብ ዛሬ ትዝ ያለኝ ሳይሆን ውስጤ ሲመላለስ የቆየ ጉዳይ ነው። ማንም ከፋው ደስ አለው እውነት እውነት ነውና በግልጽ ቋንቋ ስሜን ጠቅሼ ለማተም ወደድኩ። ባልደረቦቻቸው ሲታረዱ ካዩ፣ ሴት እህቶቻችን የሰራዊት አባላት ሲደፈሩ፣ ሲዘረፉ፣ ሲገደሏና በስለት ጉዳት ሲደርስባቸው ከነበሩ ጋር በስፋት አውርቻለሁ። በርካታ የመቃብር ቦታዎችን ምልክት አድርጎ ታሪክ ከሚጠብቅ ጀግና ጋር ሃሳብ ተለዋውጫለሁ። የሚያነባውን ስሜቴን ተቆጣጥሬና ትንፋሼን ውጬ የሰማሁትን ሰምቻለሁ። ሁሉን ለመጻፍ አቅሙ የለኝም። በማላውቀው አንድ ውስጣዊ ጫና ልጻፈው ብልም አልሆንልኝም። በተመሳሳይ በ1997 ምርጫ አንድ ታላቅ የዕልቂት ቅድመ ዝግጅት ድግስ ሰምቼ የሆንኩትን ዓይነት ስሜት ነበርና ለዛሬ ጊዜው ባለመሆኑ አልፈዋለሁ።

ልክ ከአገር ባለውለታዎቻችን ጋር ልቤ እያነባ እንዳወራሁት በተመሳሳይ ትግራይ ከኢትዮጵያ መገንጠል እንዳለባት፣ ኢትዮጵያን እንደሚበታትኗት፣ ይህን የማድረግ አቅም እንዳላቸው ” ቃል ለምድር ለሰማይ” ብለው የነገሩኝ አሉ። በተለይም አንድ እጅግ የመወደውና የማከብረው ጓደኛዬ “እናፈርሳችኋለን” ብሎ ሲፎክርብኝ ” እኔ እኮ አሰግድ ነኝ” አልኩት። እሱ ትግራይን የሚወዳትን ያህል እኔ ኢትዮጵያን እንደምወድ አለማሰቡ ሳይሆን ቢያንስ ወዳጅነታችን … ከጦርነቱ መጀመር በፊት ዝቶ ተለያየን። ወዳጄ ጋር በዛው አበቃን። ዛሬ ድረስ አዝናለሁ። እኔ የሱንና የህነግን ፍቅር ሳከበር እሱ ግን የአኔን ኢትዮጵያን መውደድ ሊፈቅድልኝ አለውደደም ነበርና መዝለቅ አቃተን። ወደፊት እንዲሁ እዛና እዚህ እንሆን ይሁን?

ይህን ሃሳብ ሳነሳ አንድ ትልቅ ነገር ታወሰኝ። ምን ያህሎቻችን አስተውለነው እንደሁ አላውቅም። አሁን የትህነግ፣ ድሮ ብርታም ድሮ የሻዕቢያ ደጋፊዎች ለሚወዱት ሲሰልሉ፣ ሲነግዱ፣ ሲመሰትሩ፣ ማህበር ሲጠጡ፣ ብር ሲያዋጡ፣ ሲያቀባብሉ ወዘተ ትክክል ነበሩ። ናቸው። ዛሬ ትህነግ ሰፈር ያለው ይህ ይመስለኛል። ድል አድርጎ መዝፈን ለነሱ፣ ተመታን ብሎ ማለቅስ ለነሱ፣ ትንሽ እውነት ይዞ ማለቀስ ለነሱ፣ በደል ሲኖር እነሱ ብቻ የሚበደሉ፣ ልማት ሲነሳ የልማት አርበኞች፣ ቋንቋ ሲነሳ የቋንቋ አከፋፋዮች፣ ዴሞክራሲ ሲባል የዴሞክራሲ በረከቶች እነሱ እንደሆኑ ተደርጎ ስለተሳለላቸው፣. ሌሎች ባሻንና በገባን መንገድ እንድንረዳቸው አይፈቅዱም። ለዚህም ይመስላል መስለኝ “ትህነግና ደጋፊዎቹን በምክንያት ማሳመን አይቻልም” ይባላል። ትህነግ ሰፈር አመክንዮ የለም። እንደውም አይታወቅም። የሚያውቅይ እንደ ጊታቸው ረዳ አይነት ሰዎች ከተገኙ በሚወዱት ጉዳይ እንዲበሰብሡ ተደርጎ ምክንያታማነታቸውን በሲሬንጅ ያልቡዋቸዋል።

የዕልቂት ዳንኪራ

እነ ስዩም መስፍን መገደላቸውን በምስል ሰዎች ሲልኩልኝ በግንባር ቀደምትነት ወጥቼ ” እንዲህ ያለ ምስል በማህበራዊ ሚዲያ ማሰራጨት ልክ አይደለም። እነዚህ ሰዎች ቢያንስ ልጆች አላቸው” በማለት ተቃውሜያለሁ። አሁን ድረስ በስህተም ይሁን አውቄ የሰውነትን ክብር የሚያቆሽሹ ምስሎችን በየትኛውም አውድ አልተጠቀምኩም። ወደፊትም አልጠቀምም። ይህን የማደርገው ለጥንቃቄ ነው። በተመሳሳይ ዕልቂትን ለዳንኪራ ማዋልን አጥብቄ እኮንናለሁ። ከጎንደሬው ጓደኛዬ ጋር በዚህ ጉዳይ ተሟግተናል። እንደውም በማይመጥነን መልኩ ተውቃቅሰናል።

ተወደደም ተጠላም አንዱ አስከሬን ላይ ቆሞ ዳንኪራ ሲረግጥ፣ ለፕሮፓጋንዳ ግብዓት ሲባል በወገኑ አስከሬንና ስቃይ ሲዛበት፣ሲፎክር በርካቶች በዛ ሃዘን ደረት ይመታሉ። ሃዘን ይቀመጣሉ። ዳንኪራው ባየለ ቁጥር ሃዘን የሚቀመጡትም እየጨመሩና ስሜታቸው እየተበላሸ ይመጣል። የሰሜኑ ዳንኪራ ወደ መካከል፣ የደቡቡ ወደ ሰሜን፣ ወደ ሌላው ዋልታና ጥግ ይጓዛል። ይጓዛል። መቆሚያ የለውም። መከላከያን ገድሎ መጨፈር ፕሮፓጋንዳ አይደለም። በአገሪቱ ሙሉ ያለው ህዝብ ደረቱን ይመታለታል። ይህ የተዘነጋ የተዘነጋ ይመስለል። የኤርትራ ተወላጆችን የልዩነት ፖለቲካ ሰለባ ያደረገው ውሳኔ ኖሮ ኖሮ ዋጋ ያስከፍለው በዚሁ መነሻ ይመስለኛል። በጦርነት መጎዳዳት ቢኖርም በትግራይ ሕዝብና ኢትዮጵያ መካከል ግን በዛ ደረጃ ሊሆን ባልተገባ ነበር። ከላይ እንዳልኩት ሁሉንም ባይወክልም አያስኬድም።

በተመሳሳይ የአገር መከላከያ ላይ ክህደት ተፈጽሞ በትግራይ በተፈጠረው ቀውስና የትግራይ ህዝብ መፈናቀል፣ እንዲሁም ስደትና ችግር እርካታ የሚሰማቸው ወገኖች ድርጊታቸው በምንም ሰውኛ መስፈርት ትክክል አይሆንም። ህጻናት፣ እናቶች፣ አዛውንቶች የችግሩ ሰለባ ሆነዋል። ያሳዝናል እንጂ አያስፈንደቅም። እንዴት ከችግሩ እንዲወጡ ማሰብ እንጂ በሰዎች ስቃይ ዳንኪራ ክብረ ነክ ነው።

ፕሮፓጋንዳና ገበያ

የህዝብን ስቃይና መከራ አንድም ለዩቲዩብ ገበያ፣ አንድም ለፖለቲካ ዳግም ትንሳኤ የመጠቀሙ ሌላው እጅግ የወረደና መረን የወጣው ጉዳይ ያሳስበኛል። አንድ ህዝብ እየተጫረሰ “ሰበር” ዜና እያሉ ገንዘብ መልቀም እጅግ ስንኩል የሆነ ተግባር ነው። ወንድማማች እየተገዳደለ በፎቶ ሾፕ ሬክላም እየሰሩ ወሬ መሸቀጥ እጅግ አሳፋሪ ነው። ሁሉም ሳይሆኑ አብዛኞች በዚህ ተግባራቸው የሚወቀሱ ናቸው። መከራከሪያ ማቅረብ የሚችሉም አይሆኑም።

“የመዋጊያ ዩኒፎርማቸውን እያወለቁ የሲቪል ልብስ እየለበሱ ስለሆነ በቀላሉ ከመሀበረሰቡ ጋር ይቀላቀላሉ።አብዛኞቹ ከሰራዊቱ የከዱት የአገሬው ተወላጆች አባላትም የሸሹት ወደቀዬቸው ስለሆነ ከህዝቡ ጋር በቀላሉ ለመቀላቀል ብዙ እንደማይቸገሩ ግልጽ ነው። እናም እዛ አድፍጠው ይቀመጡና ይተነኩሳሉ። እርምጃ ሲወሰድ ሲቪልና ሕጻናት ተነኩ ብለው ይጮሃሉ ”

ከላይ የተቀመጠው ቃል በቃል ከወር በፊት በግዳጅ ላይ ከነበረ የአገር መከላከያ ሰራዊት አባል የተሰጠኝ አስተያየት ነው። በርካታ ጉዳዮችም አሉ። ግን ለመጻፍ አስቸጋሪ ስለሆነ ለጊዜው አልፈዋለሁ። ግን ” ትግራይ ከይፋ ውጊያ ውጭ በኢትዮጵያዊያን ላይ የሚሆነው ሁሉ በሰራዊቱ ቤተሰቦችና መላው ኢትዮጵያዊያን ዘንዳ ሚስጢር አይደለም። ስሜታቸውም ይታወቃል” ሲል የተናገረውን መጥቀስ ዛሬ ላይ አስፈላጊ ሆኗል።

በውጊያ ህግና ጨዋታ የትህነግ ሃይል ችግር እንዳልሆነ ሁሉም ወገን ይስማማል። ችግር የሆነው ግን ከውጊያው ጨዋታ ውጭ ያለው ቁማር ነው። የሀገር መከላከያ ሰራዊት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ እንዳሉት ሲተኩሱ ወታደር፣ ሲመቱ ሲቪል መሆናቸው ትልቁ ፈተና የመሆኑን ጉዳይ ነው።

እስከሚገባኝ ” እኔ የወታደር ልብስ አውልቄ ልግደልህ” የሚሰራ አይመስለኝም። አሁን ከአዲስ አበባና ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የትግራይ ተወላጆ የሆኑ ወይም ትህነግን የሚደግፉ ” ሲቪል ተጠቃ” በሚል እየጮሁ፣ በተመሳሳይ ” መከላከያ ተደመሰሰ” በሚል እየጨፈሩ ነው። የንጽሃን ሞት አሳዛኝ መሆኑና ሊወገዝ የሚገባው ጉዳይ ቢሆንም፣ ከስፍራው ያሉ ወታደሮች እንደነገሩኝ ጉዳዩ ጭልጥ ያለ ፕሮፓጋንዳ ነው።

” ህጻናት እየላኩ ሊያስገድሉን ይሞክራሉ” ሲሉ ወታደሮቹ ነግረውኛል። “ሲዋጉና ሲመቱ መሳሪያ ጥለው ሲቪል መስለው ይቀመጣሉ” ያሉት ወታደሮች ” በትግራይ ክህደት የተፈጸመብን፣ የታረድንና፣ የተረሽን መሆናቸውን ይዘነጋሉ” ሲሉ ንዴታቸውን ይገልጻሉ።

ባልደረባዬ ሶስና አስራቴ ወንድሟ አገሩ የሰጠችውን ግዳጅ ለመወጣት ትግራይ ይገኛል። በምትሰማው ዜናና በሚለቀቁ ምስሎች ስሜቷ ጥሩ አይደለም። በቤቷን የተፈጠረውን ሰማሁና ደወልኩላት ” የኛ ልጆችም ቤትሰብና ወገን አላቸው” ስትል የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ በሚፈጸሙ እኩይ ተግባራት የሚሳለቁትን መታገስ የማትችልበት ደረጃ መድረሷን ነገረችኝ። አዲስ አበባ አብሮ አደጓ ከሆነው የትግራይ ልጅ ጋር ትዳራቸውን በዚሁ የአካባቢያዊነት ስሜት ጣጣ እንዳፈረሱ አቆአላምታ ስሙን ጠርታ ነገረችኝ። ” አልተግባባንም። በሰላም ተለያየን። ፍላጎቱን አከብራለሁ። ግን እዚህ ሆኖ ወንድሜ ላይ መዛበት እንደማይችል ነግሬው ነው የተለያየነው” አለችና ተለያየን።

በርካታ ሰዎች በውጭ አገር የሚኖሩ ጭምር ትዳራቸው ፈርሷል። ቀን ባመጣው አለመግባባት ልጆች ተበትነዋል። ከፍ ያሉት የማን ወገን እንደሚሆኑ አያውቁም። በትግራይ የተፈጠረው ቀውስ ፕሮፓጋንዳው ከጦርነቱ በላይ ጉዳት እንዳደረሰ ይታመናል። የዲስ ነዋሪ የሆነውና ለልጆቹ ሲል ስሙን የደበቀው ምስክር የሃያ ሁለት ዓመት ትዳር መፍረሱን፣ ልጆቹ ሲጠይቁት ማስረዳት እንዳልቻለ አመልክቷል። በትቅሉ ” ግራ ያጋባል” ነው ያለው።

ለሳንቲም ለቀማና ለስልጣን ፕሮፓጋንዳ የሚውለው ይህ ቀውስ 1977 ላይ የነበረውን ረሃብ ጎትቶ አየሩን በመላው ዓለም ተቆጣጥሮታል። በአዲስ አበባና በውጭ አገር አንዳንድ ዜጎች ጋብ ብሎ የነበረው ስሜታቸው መልሶ እየጎሸ መሆኑ ምልክት እየታየ ነው። ምርጫውን ማስተጓጎል ሳይቻል ሲቀር በሌላ ዜና ለዋጥ ሰሞኑንን ትህነግ ድል ማግኘቱ እያወራ ነው። ምርኮና የመጓጓዣ አውሮፕላን መምታቱን እያስታወቀ ነው። በተመሳሳይ የአየር ጥቃት በገበያ ቦታ ላይ ተፈጸመ ሲል እየከሰሰ ነው። ለክሱ መንግስት ምላሽ ሲሰጥ እንዳለው የሰማዕታት ቀን ለማክበር ተሰብስበው ሳለ በመረጃ ተደግፎ በጥናት የተካሄደ ምት ነው። ገበያ ከተበተነ በሁዋላ የሆነ መሆኑንን አስታውቋል።

አሁን አሳሳቢ የሆነው የሁለቱ ወገኖች መካሰስ ሳይሆን ከዛም ከዚህም ወገን ያለው ሰራዊት ላይ የሚወሰድ እርምጃ ” ማን ላይ ቆመሽ” እያሰኘ መሆኑ ነው። ድሮ አዲስ አበባ ተቀምጠው ለሽፍታው ቡድን የሚነግዱ ነበሩ። ከድሉ በሁዋላ እንደ ገድል ስራቸውን አደባባይ ወጥተው ነግረውናል። ዛሬ ያ አይሰራም። “አሸባሪ” የተባለ ድርጅት የሚያሰራጨውን መረጃና ፕሮፓጋንዳ አዲስ አበባ ቁጭ ብሎ በመንግስትና ህዝብ በጀት ማስተጋባት ችግሩን እንዳያሰፋው ፍርሃታቸውን የገለጹ ነግረውኛል።

የሚበጀው ” ለህዝብ የሚጠቅመው የቱ ነው” የሚለውን ከስሜት በመውጣት ማስተጋባት ሲቻል ነው። በትግራይ ክልል የወልቃይት ጉዳይ አለ። የራያ ጉዳይ አለ። የትህነግም ሆነ የትህነግ ደጋፊዎች ስለ ዴሞክራሲ ካሰቡ የወልቃይትና የራያ ጉዳይ እንዴት እንደሚፈታ አብረው ማሰብ ይገባቸዋል። ካሁን በሁዋላ የሁለቱን አካባቢ ህዝብ በሃይል ማስተዳደር አይቻልም። የራስን እድል በራስ የመወሰን ስልጣን አላቸው። የኔ ብቻ ድምጽ ይከበር፣ የሌሎች ባፍጢሙ ይተከል ማለት ብዙ ርቀት አያስኬድም። አምራ ክልልም ቢሆን እንዲሁ እንደ ድሮው ዝም አይልም። እንደሚወራው ከሆነ የወልቃይት ህዝብ ልክ ትግራይ እንደሆነው በነብስ ወክፍ ታጥቋል። በራያም እንደዛው ነው።

ሚዲያውም ሆነ ጤነኛ አዕምሮ ያለው ዜጋ ችግሩን አስፍቶ በመመልከት ከተራ ” ሰበር ዜና” አዋጅ በመውጣት መፍትሄ አመላክች ጉዳዮች ላይ ትክረት ሊያደርግ ይገባል።አንዱን ጋብዞ ሌላውን ማስጨፍጨፍ ሳይሆን፣ ወደ መፍትሄ አመላካች ሃሳብ የሚጎትቱ ፕሮግራሞችን ማሰራጨት አግባብ ይሆናል ብዬ አምናለሁ። ከሁሉም ወገን የሚረጭ ወገንተኛ እሳቤ አልጠቀመንም።

ይሉኝታን በመምረጥ አገርን መክሰር አይሆንም። አሁን የምርጫ አጀንዳ ተዘግቷል። የትግራይና የግድቡ ሁለተኛ ሙሌት ነው ቀሪው ጉዳይ። ከተራ ደመሰሰው፣ ተደምሰሰ ዝላይና ዳንኪራ በመውጣት እውነታን ታሳቢ አድርጎ መንቀሳቀስ ይሻላል። ዛሬ ሟችም ገዳይም፣ ጨፋሪም አልቃሽም አንድ ወገን ናቸው። ትናት የታረደውም ወገን ነው። ይህ አዙሪት ካልቆመ ወገን ወገኑን እያረደ … ዳንኪራውም እየበረታ ሲሄድ ለቅሶ የበዛባቸው አንብተውና ደረታቸውን ደቅተው በዛው ያበቁ ይሆን? ፍርሃቻዪ ከፍተኛ ነው ….

Exit mobile version