Site icon ETHIO12.COM

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሕወሃት የሽብር ቡድን አባላት ሕንጻዎች በገለልተኛ አስተዳዳሪ ተይዘዉ እንዲተዳደሩ ወሰነ

የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት በተለያዩ የመዝገብ ቁጥሮች (በመ/ቁ 007198፣ 263719፣ 007109፣ 006060፣ 263591፣ 006914፣ 006059 እና 007029) ሰኔ 16፣ 17 እና 18 ቀን 2013 ዓ.ም በዋለዉ ችሎት ዋና ዋና የሕወሃት የሽብር ቡድን አባላት የንግድና የመኖሪያ ሕንጻዎች ላይ ገለልተኛ አስተዳዳሪ እንዲሾም ዉሳኔ ሰጠ፡፡

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በወንጀል የተገኘ ሀብት ማስመለስ ዳይሬክተር ጄነራል የሆኑት አቶ ዓለምአንተ አግደዉ እንደገለጹት፤ ፍ/ቤቱ ይህንን ዉሳኔ የሰጠዉ የሽብር ቡድኑ በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ የወንጀል ምርመራና የሀብት ጥናት እየተከናወነ መሆኑን መነሻ በማድረግ፤ ቡድኑ ከሕንጻዎቹ የሚያገኘዉን ገቢ የሽብር ተግባሩን ፋይናንስ ለማድረግ እንዳያዉል ለመከላከል፣ በተጠረጠሩበት የሽብር እና ሌሎች ወንጀሎች በፍ/ቤት ጥፋተኛ ሆነዉ ከተገኙ ሀብታቸዉ የሚወረስ በመሆኑ ተጠብቆ እንዲቆይ፣ የሽብር ቡድኑ በመከላከያ የሰሜን ዕዝ ሀብት፤ በተለያዩ መሰረተ ልማቶችና ስቪል ተቋማት ላይ ላደረሰዉ ዉድመትና ጉዳት ለማካካሻነት የሚዉል በመሆኑ እንዲሁም የተጠርጣሪዎችን ንብረት የያዙ አካላት የሚፈጽሙትን ምዝበራ ለመከላከል ሲባል በተጠረጠሩበትና በተከሰሱበት ወንጀል ፍ/ቤት የመጨረሻ ዉሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ገለልተኛ አካል እንዲያስተዳድራቸዉ ዐቃቤ ሕግ ለፍ/ቤት አቤቱታ ማቅረቡን ተከትሎ ነዉ፡፡

ፍ/ቤቱ የዐቃቤ ሕግን አቤቱታ ከመረመረ በኋላ ሕንጻዎችን የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሥር የሚገኘዉ ኮመርሽያል ኖሚኒስ ኃ/የተ/የግ/ማህበር እንዲያስተዳድር ዉሳኔ ሰጥቷል፡፡

በዚህ ዉሳኔ አስተዳዳሪ የተሾመላቸዉ የንግድና መኖሪያ ሕንጻዎች አጠቃላይ ብዛት ከ 30 በላይ ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል፡-

በ ጄ/ል ፃድቃን ገ/ተንሳይ ስም አዲስ አበባ የሚገኙ 2 (ሁለት ህንጻዎች) ፣

በ ጄ/ል አበበ ተክለሃይኖት ስም አዲስ አበባ የሚገኝ አንድ G+5 ሕንጻ (ወለላ ሕንጻ)፣

በ ብ/ጄ ምግበ ሃያለ ስም አዲስ አበባ እና መቀሌ የሚገኙ 2 (ሁለት) ሕንጻዎች፣

በ ብ/ጄ ታደሰ ወረደ ስም መቀሌ የሚገኙ 2 (ሁለት) ሕንጻዎች፣

በ ብ/ጄ ተክላይ አሸብር ስም አዲስ አበባ የሚገኝ G+5 ሕንጻ (ብሌን ሕንጻ)፣

በ ብ/ጄ ዮሀንስ ወ/ጅወርጊስ ስም መቀሌ የሚገኙ 3 (ሦስት) ሕንጻዎች፣

በሜ/ጄ ሕንጻ ወ/ጊወርጊስ ስም መቀሌ የሚገኝ 1 (አንድ) ሕንጻ፣

በሜ/ጄነራል ኢብራሂም አብዱልጄሊል ስም መቀሌ የሚገኝ 1 (አንድ) ሕንጻ እና በሃይለ ተስፋኪሮስ ገ/ሕይወት ስም መቀሌ የሚገኙ 3 (ሦስት) የነዳጅ ማደያዎች ይገኙበታል፡፡

በወንጀል የተገኘ ሀብት ማስመለስ ዳይሬክተር ጄነራሉ አክለዉ እንደገለጹት፤ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ከዚህ በተጨማሪ በዶ/ር አዲስአለም ባሌማና የሜ/ጄ ጻድቃን ባለቤት በወ/ሮ ኤልሳ አሰፋ ተክለሚካኤል ስም የሚገኙ ሕንጻዎችን ጨምሮ በሌሎች የሽብር ቡድኑ አባላት ሃብት ላይ አስተዳዳሪ ለማሾም እየተሰራ ነው።

በሀብት ምርመራ እና መለየት ሂደት የሽብር ቡድኑ አባላት ተሽከርካሪዎችን ከቆሙበት በማንሳት ጋራዥ ዉስጥ የመደበቅና አካላቸዉን ፈቶ የማስቀመጥ፣ ለዉጭ ዜጎች በማከራየት የኪራይ ገንዘብ ዉጭ አገር ለመቀበልና በማሸሽ ለሽብር አላማ ለማዋል፣ የኪራይ ዉሎችን በመንደር ዉል በማድረግ ግብር እንዲሰወርና የሽብር ቡድን አባላትን ንብረት በኪራይ መያዛቸዉ እንዳይታወቅ የማድረግ ተግባር መፈጸም፣ አንዳንድ ህንጻዎችን ለሌላ ሦስተኛ ወገን የባንክ ማስያዣ በማድረግ ገንዘብ የማሸሽ ሙከራዎች ስለማድረጋቸዉ መረጋገጡ ተገልጿል።

እነዚህን የወንጀሎች ተግባራትን አዲስ አበባ በሚገኙ ወኪሎችና ተከራዮች አማካኝት እየፈጸሙ መሆኑ በመታወቁ ከዚህ አንጻር ተጨማሪ ምርመራዎች በመጣራት ላይ ናቸዉ፡፡

የሕወሃት የሽብር ቡድን አባላትን ንብረት በኪራይ፣ በዉክልና፣ በጠባቂነት፣ በአደራና በሌላ ማናቸዉም መንገድ ይዘዉ የሚገኙ አካላት ልደታ ከፍተኛ ፍ/ቤት ግቢ ዉስጥ በሚገኘዉ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ህንጻ 1ኛ ፎቅ በወንጀል የተገኘ ሀብት ማስመለስ ዳይሬክቶሬት ጄነራል ቢሮ በአካል በመቅረብ ወይም በስልክ ቁጥር 0112733154 ወይም በEmail፡- assetrecovery@eag.gov.et በማሳወቅ ራሳቸዉን ከወንጀል ተጠያቂነት ነጻ እንዲያደርጉ አቶ ዓለምአንተ አግደዉ ጥሪ አቅርበዋል።

በሌላ በኩል ባንኮች ለሚሰጡት ብድር መያዣ የሚያደርጉት ንብረት የሕወሃት የሽር ቡድን አባላት አለመሆኑን ወይም ከእነርሱ ጋር ግንኙነት የሌለዉ መሆኑን አስቀድመዉ በቂ ማጣራት በማድረግ ማረጋገጥ ያለባቸዉ ሲሆን ይህንንም ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና ከሌሎች የሚመለከታዉ የሕግ አስከባሪ ተቋማት ጋር በቅርበት መረጃ መለዋወጥ እንዳለባቸዉ አስገንዝበዋል፡፡

ምንጭ፡- ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ

Exit mobile version