Site icon ETHIO12.COM

የህወሃት ታጣቂ በሚንቀሳቀስበት አብይአዲ አካባቢ የ3 ደንበር የለሽ የሃኪሞች ተገደሉ

ዛሬ አሸባሪው የህወሃት ታጣቂ በሚንቀሳቀስበት አብይአዲ አካባቢ የ3 ደንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን ሰራተኞች መገደላቸውን የመከላከያ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮ/ል ጌትነት አዳነ ማምሻውን ገለፁ።

የበለጠ በራሳችን መንገድ የሚረጋገጥ ቢሆንም ፣ አሸባሪው የህወሃት ታጣቂ ፣ ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን ( MSF- Médecins Sans Frontières or Doctors Without Borders ) የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ሰራተኞችን ከመኪና አስወርዶ እንደገደላቸው ቅድመ መረጃ ደርሶናል ያሉት ኮ/ል ጌትነት ፣ ከሟቾቹ ውስጥ አንዷ ስፔናዊ ስትሆን ሁለቱ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ናቸው ብለዋል ።

በዚህ ቀጣና የረድዔት ድርጀት ሰራተኞችም ሆኑ የሚዲያ አካላት አይንቀሳቀሱ ስንል ከነበረን የስጋት ትንተና እና የጁንታውን ተፈጥሯዊ ጭካኔ ስለምናውቅ ነበር። ይህ ኃይል አብሮት ለታገለ ፣ በአንድ መለዮ ጥላ ስር ክፉ ደጉን ላሳለፈ ፣ ለራሱ ዜጎችና ጠባቂዎች እንኳን ያልራራ ለማንም እንደማይመለስ ስለምናምን እንዲሁም ስለምንጨነቅም ነበር አትንቀሳቀሱ ስትንቀሳቀሱም እናጅባችሁ ፣ እንጠብቃችሁ ስንል የነበረው ብለዋል።

የህዝብ ግንኙነት ሀላፊው እንዳሉት ፣ በየትኛውም መመዘኛ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚያደርጉ ሰዎችን መግደል ተቀባይነት የሌለውና ሰላም ወዳድ ሁሉ ሊያወግዘው የሚገባ ጭካኔ ነው። አሸባሪ ያልነው በምክንያት ስለሆነ መላው የሃገራችን ህዝቦችና የዓለም አቀፍ ማህበረሰቡም ይህን አረመኔ ለማጥፋት በምናደርገው ጥረት ከጎናችን እንዲሰለፍና ድርጊቱን በተገቢው አጣርቶ እንዲያወግዝ እንጠይቃለን ነው ያሉት።

ሰራዊታችን አስፈላጊውን መስዋዕትነት በመክፈል አሰከሬናቸው በክብር እንዲያርፍ እና ለሚያጣራ አካል ደጋፍ በማድረግ በራሱም በጠንካራ ማስረጃ አስደግፎ እንደሚያቀርብ እየገለፅን ፣ ለሟች ነብስ ይማር እያልን ለቤተሰቦቻቸው ፣ ለስራ ባልደረቦቻቸው እና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መፅናናትን እንመኛለን ፡፡ ወንጀለኞች ለህግ እሲኪቀርቡ እንታገላለን ብለዋል ።

ፎቶግራፍ ተሰማ ኡርጌሳ

Exit mobile version