Site icon ETHIO12.COM

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ተኩስ አቁም እንዲደረግ የፌዴራል መንግስትን ጠየቀ

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የፌዴራል መንግስት ሰብዓዊነትን መሰረት ባደረገና ተጨማሪ ጉዳት በማያስከትል መልኩ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርግ ጥያቄ ማቀረቡን አስታወቀ።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አብርሃም በላይ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳስታወቁት፤ ክረምት እየገባ በመሆኑ የትግራይ አርሶ አደር ተረጋግቶ የእርሻ ስራውን እንዲያከናውን፣ የሰብዓዊ ድጋፍ ለተረጂዎች ያለምንም ችግር እንዲደርስ ወቅቱን የሚመጥን ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመስጠት የፌዴራል መንግስት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርግ ተጠይቋል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ባለፈው ሳምንት በይፋ ጥያቄውን ያቀረበው የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ከክልሉ ህዝብ ተወካዮች፣ ከቢሮና ዞኖች አመራር አባላት፣ በተለያየ ቦታ ከሚገኙ የትግራይ ተወላጆች፣ ከትግራይ ምሁራን፣ ከባለሀብቶችና ከሃይማኖት አባቶች ጋር ተከታታይ ምክክር ካደረገ በኋላ ነው።

አሸባሪው የህወሃት ቡድን በክልሉም ሆነ በአገሪቷ ላይ የፈጠረው ውስብስብ ችግር ወታደራዊ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መሆኑን ያወሱት ዶክተር አብርሃም፤ ለዚህም እስከ አሁን በፌዴራል መንግስትና በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የተለያዩ መፍትሄዎች ሲወሰዱ መቆየቱን አብራርተዋል።

እስከአሁን ህግ በማስከበር እርምጃ ከመውሰድ ባሻገር በህግ የሚታዩ ጉዳዮቸን በህግ መፍትሄ ለመስጠት ከጥፋት ሃይሉ ወንጀለኛ የሆነውን ለይቶ ወደ ህግ የመቅረብ ስራ ሲከናወን መቆየቱን ተናግረዋል።

በጊዜያዊ አስተዳደሩም ሆነ በፌዴራል መንግስት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎቸን አስታውሰው፤ በቀጣይም ፖለቲካ አማራጮችን ታሳቢ ማደረግና መፍትሄ እርምጃዎች የመውሰድ አስፈላጊነት ላይ እምነት መኖሩን ጠቁመዋል።

የክልሉ አርሶአደር በዚህ ክረምት ወደ እርሻ ካልገባ የዘር ወቅት ስለሚያልፍ፣ በቀጣይ ገበሬው ለዓመታት ተረጂ ሆኖ የመኖር እድል እንደሚገጥመው ነው ያወሱት።

በዚህም አሸባሪው ቡድን የዚህ ዓይነቱን ቀውስ እየፈጠረ እንደሚሄድ ጠቅሰው፤ “የኢትዮጵያ መንግስትና የመከላከያ ሰራዊት እዳውን እንዲሸከምለት ያደርጋል” ብለዋል።

እንደርሳቸው ገለጻ፤ መንግስትና የእርዳታ ድርጅቶች እርዳታ እንዳያደርሱ፣ ለገበሬው ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ እንዳያቀርቡ እያሰናከለ፣ ህዝብ ተራበ ብሎ ራሱ ይጮሃል፤ ምክንያቱም ህወሃት መኖር የሚችለው የትግራይ ህዝብ ሲሞትና መከራ ሲያገኝ ብቻ ነው።

እንዲህም ሆኖ የኢትዮጵያ መንግሰት ባለፉት ወራት ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ለእርዳታ፣ ለመንግስት አገልግሎት ማስቀጠልና ለመሰረተ ልማት ግንባታ አውሏል ነው ያሉት።

ይህም በአገሪቷ አጠቃላይ ኢኮኖሚ በተለይ በሌሎች ክልሎች የሚያደርሰው ጫና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ ክልሎች ከበጀታቸው ቀንሰው የትግራይ ክልልን ለማቋቋም ድጋፍ ማድረጋቸውን ለአብነት አንስተዋል።

እርዳታ እንሰጣለን ለሚሉ አካላትም ከሚፈለገው በላይ ተሂዶ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥሯል ብለዋል።

በቀጣይ ደግሞ ሰብዓዊ እርዳታው ወደ ሚፈለገው ቦታ ለማድረስ፣ እርሻ ሥራ እንዳያመልጥ ለማድረግ፣ የተፈናቀለውንም ተረጋግቶ ወደ የቤቱ እንዲመለስ ተጨማሪ የፖለቲካ አማራጭ በማስፈለጉ በተደጋጋሚ ከመንግስት ጋር ንግግር መደረጉን ነው ዶክተር አብርሃም የገለጹት።

ይህን መነሻ በማድረግ ለፌዴራል መንግስት ዘጠኝ ነጥቦች ያካተተ ጥያቄ ለፌዴራል መንግስት አቅርበዋል።

የተኩስ አቁሙ ስምምነቱ ገበሬው ተረጋግቶ እንዲያርስ፣ ለችግረኞች የሰብዓዊ ድጋፍና የእርዳታ ቁሳቁስ ለማድረስ፣ የተፈናቃዮችን ቤት ጠግኖ ወደ ቦታቸው ለመመለስ እንደሚያስችል አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት በረሃ ካለው ሃይል መካከል የሰላም መንገድ የሚፈልግ መኖሩን አመላክተው፤ ለዚህ ሃይል እድል መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል።

ዶክተር አብርሃም እንደሚናገሩት፤ አጥፊው የህወሃት ሃይል የተበተነ ቢሆንም ለብዙ ዘመናት በክልሉ በዘረጋው የፍርሃት መዋቅር በኩል ዜጎችን ያስፈራራል፣ ያስገድላል፤ ይገድላል።

“ለዜጎች የእርዳታ እህል እንዳይደርስ ያደናቅፋል፤ የእርዳታ ሰራተኞች ይገድላል፤ ዜጎች እርዳታ እንዳይቀበሉ ያስፈራራል፤ ከተቀበሉ በኋላ እንዲያካፍሉት ያስገድዳል” ብለዋል

የአጥፊው የህወሃት ቡድን ዋና አላማ ህዘቡን የጦርነት ጋሻ ማድረግ ነው” ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ ነገር ግን የህዝብን ጥቅም በማስቀደም የተኩስ አቁም ማድረግ ጠቀሜታ እንዳለው አብራርተዋል።

ችግሮቹን ለመፍታት የፖለቲካ መፍትሄ መውሰድ አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት ሰጥተዋል።

“ለትግራይ ህዝብ ፖለቲካዊ መፍትሄ መፈለግ ያለበት መንግስት እንጂ ለህዝቡ ግድ የሌለው የህወሃት ጥፋት ሃይል ሊሆን አይችልም” ያሉት ዶክተር አብርሃም፤ በመሆኑም መንግስት ይበልጥ ሆደ ሰፊ ሆኖ ፖለቲካዊ መፍትሄዎችን መስጠት እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል።

ለፌዴራል መንግስት የቀረበው የተኩስ አቁም ስምምነት ጥያቄ የህዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ መሆኑን አብራርተዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው

Exit mobile version