ETHIO12.COM

“ወርቅ ያበደረ ሰራዊታችን ጠጠር እየሰበሰበ መኖር የለበትም”

ጋዜጠኛ ሃይሌ ሙሉ

… የትግራይ ክልል መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ሽፍታዎቹ ከተደበቁበት ቦታ ወጥተው ድንገተኛ ጥቃት አድርሰው እንዲመለሱ ረድቷቸዋል። ወንበዴዎቹን ተከታትሎ መያዝ እንዳይቻል ደግሞ የአካባቢው ማህበረሰብ ተባባሪ አልሆነም። ሲፈልግ ይደብቃቸዋል ሲያሰኘው ከእነሱ ጋር ተባብሮ ሰራዊቱን ይወጋል። አፀፋዊ እርምጃ ሲወሰድበት ደግሞ “ሰላማዊ ሰው ነኝ” ብሎ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ውንጀላ ያቀርባል።


ቻይናዊው የሚሊተሪ ስትራቴጂስትና ፈላስፋ ሰን ትዙ ( Sun Tzu) Art of war በተሰኘው መፅሀፉ እንዲህ ሲል ይመክራል –

” የተቀናቃኞቹን ፊውዳል ጦር አበጋዞች እቅድ የማያውቅ የጦር መሪ ለጦርነት ዝግጁ ሆኖ የሚጠባበቅ ህብረት መፍጠር አይችልም። ጠላት የመሸገበትን ጋራና ተራራ፣ጫካውን ፣ ስርጥ መንገዱን ፣ ሸለቆውን ፣ አሮንቃውን፣ ጉብታውንና የመሳሰሉትን መልክዓ ምድራዊ አቀማመጦች የማያውቅ የጦር መሪ ሰራዊት መምራት አይችልም። ጦርነት የሚካሄድበትን አካባቢ ጠንቅቆ የሚያውቅ የአካባቢ ሰው በመንገድ መሪነት መያዝ ያልቻለ የጦር መሪ ለውጊያ ወሳኝ የሆኑ ቦታዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል አይችልም። ከላይ የተጠቀሱትን ነጥቦች የማያውቅ የጦር መሪ ደግሞ ታላቅ መሪ ሊሆን አይችልም ” ይላል። ( Sun Tzu, Art of War, translated with a Historical Introduction by Ralph D. Sawyer, page 119)

ባለፉት ስምንት ወራት ትግራይ ውስጥ የተፈጠረው ክስተት ሰን ትዙ ከሶስት ሺህ አምስት መቶ አመታት በፊት የተናገረውን ነገር የሚያረጋግጥ ነው ። በኮንቬንሽናል ጦርነቱ በሶስት ሳምንት ውስጥ ብትንትኑ የውጣው የወያኔ ሰራዊት በየዋሻውና በየገበሬው ጎጆ ቤት ከተደበቀ በኋላ የጦር ሰራዊታችን ረፍት ነስቶት ከርሟል። የጦር መሪዎቻችን መንገድ ሊመራና ሽፍታው ቡድን የተደበቀበትን ቦታ ሊጠቁም የሚችል የአካባቢ ሰው ባለመኖሩ ሰራዊታችን በጥሻና በገደሉ ሲንከራተት ከርሟል። የመከላከያ ጄነራሎቻችን የጠላትን እንቅስቃሴ ባለማወቃቸው የህወሓትን ርዝራዥ ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መደምሰስ የሚያስችል የጦርነት እቅድ ማውጣት አልቻሉም ነበር። ለጦርነት አመች ያልሆነው የትግራይ ክልል መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ሽፍታዎቹ ከተደበቁበት ቦታ ወጥተው ድንገተኛ ጥቃት አድርሰው እንዲመለሱ ረድቷቸዋል። ወንበዴዎቹን ተከታትሎ መያዝ እንዳይቻል ደግሞ የአካባቢው ማህበረሰብ ተባባሪ አልሆነም። ሲፈልግ ይደብቃቸዋል ሲያሰኘው ከእነሱ ጋር ተባብሮ ሰራዊቱን ይወጋል። አፀፋዊ እርምጃ ሲወሰድበት ደግሞ “ሰላማዊ ሰው ነኝ” ብሎ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ውንጀላ ያቀርባል።

የኢትዮጵያ መንግስት ባለፉት ስምንት ወራት ለትግራይ ሰብአዊ እርዳታ ከመቶ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ አድርጓል። ይሄ ገንዘብ ለልማት ውሎ ቢሆን ኖሮ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ምን ያህል ለውጥ ሊያመጣ ይችል እንደነበር መገመት አያዳግትም። ከመቶ አመት በላይ የተገነባው የኢትዮጵያ ቴሌኮሚዮንኬሽን ባለስልጣን የሀብት መጠን 80 ቢሊዮን ብር መሆኑን ትናንት ሰምቻለሁ። እንግዲህ በአገሪቱ ቁጥር አንድ ተብሎ የሚጠቀሰው ይህ አትራፊ ድርጅት ከያዘው የሃብት መጠን በላይ ነው ባለፉት ጥቂት ወራት እንደዋዛ ትግራይ ላይ የተበተነው። ለዚያውም ወርቅ ላበደረ ጠጠር እንዲሉ ሰራዊታችን “ወራሪና ደፋሪ” ተብሎ እየተወነጀለ።

የተጠቀሰው መጽሐፍ ሽፋን

የመከላከያ ሰራዊታችን በማያውቀው መልክዓ ምድር እየተንከራተተ አላስፈላጊ መስዋዕትነት ከሚከፍል፣ መንግስት ከዚህ መከረኛ ህዝብ ሰብስቦ ያገኘውን ገንዘብ በየቀኑ እየበተነ አገሪቱ ለኢኮኖሚ ችግር ከሚያጋለጥ ፣ “የተኩስ አቁም ስምምነት አድርጉ” ብለው ወጥረው የያዙን የአሜሪካና የአውሮፓ መንግስታት የኢኮኖሚ ማዕቀብ ከመጣላቸው በፊት ሰራዊቱ ትግራይን ለቆ መውጣቱ ተገቢ ቢሆንም ሰራዊቱ በድንገት አካባቢውን ለቆ የወጣበት አካሄድ ግን ትክክል አይመስለኝ። ጠቅላይ ሚንስትር አብይም ሆኑ ሌሎች የመንግስት ባለስልጣናት በሚሰጧቸው መግለጫዎች የትግራይ ህዝብ ከመከላከያ ሰራዊቱ ጋር የማይተባበር ከሆነ የመከላከያ ሰራዊቱ ትግራይን ለቆ ሊወጣ እንደሚችል ቀደም ብለው ጠቁመው ቢሆን ኖሮ አሁን የተረበሸው የህብረተሰብ ክፍል በስነልቦና ተዘጋጅቶ ሊጠብቅ ይችል ነበር። ከዚያ በተረፈ ግን መከላከያው ትግራይን ለቆ በመውጣቱ ያተርፋል እንጂ የሚያጣው ነገር አይኖርም።

በሌላ በኩል የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ከመከላከያ ሰራዊት ጋር ሆኖ ህወሓትን በመዋጋቱ አላስፈላጊ መስዋዕትነት እንደከፈለ አድርገው የሚያወሩ ሰዎች የማስታውስ ችግር ያለባቸው ይመስለኛል። እስኪ የተገኙ ድሎችን አንድ ሁለት ብለን እንጥቀስ –

-ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት የዘረፈውን ከባድ መሳሪያ ተማምኖ አማራን እወራለሁ እያለ ሲፎክር የነበረው ህወሓት በጦርነቱ ከተሸነፈ በኋላ ሁሉንም መሳሪያ አስረክቦ ክላሽና ዱላ ይዞ የሽፍትነት ህይወት ለመምራት ተገዷል።

-አማራን በጠላትነት ፈርጀው ሲያስፈጁት የኖሩት የህወሓት አመራሮች ግንባር ግንባራቸውን ተመትተው በየዋሻው ወድቀዋል (አንገታቸው ተቆርጠው የተቀብሩት ደግሞ እነማን እንደሆኑ በቅርቡ እናውቃቸዋልን። በህይወት ካሉ ክብ ሰርተው መጨፈራቸው አይቀርም።

-“አማራንና ኦርቶዶክስን ጉድጓድ ምሰን ቀብረንዋል ” ብሎ የተዘባበተው ስብሀት ነጋ ከግብረ አበሮች ጋር እስር ቤት ተወርውሮ ዋጋውን እየከፈለ ነው።

– በውይይትና በድርድር ወይም በሽምግልና በመጪዎቹ አስር አመታት ጊዜ ውስጥ ለመመለስ እንኳን አስቸጋሪ ሊሆኑ ይችሉ የነበሩት የወልቃይትና የራያ መሬቶች ለባለርስቱ ህዝብ ተመልሰዋል። እና ይሄ ቀላል ድል ነው? ኸረ ጎበዝ አንዳንዴ የትናንቱንም እናስብ!

አንዳንድ ሰዎች የአሁኑን የመከላከያ ሰራዊት ትግራይን ለቆ መውጣት ደርግ ወስዶት ከነበረው ተመሳሳይ እርምጃ ጋር እያመሳሰሉ ወያኔ ተጠናክሮ በመውጣት ጥቃት ሊፈፅም ይችላል በማለት ስጋታቸውን ሲገልፁ እሰማለሁ። ወዳጄ ሁለቱ ክስተቶች አይነፃፀሩም። ያኔ ወያኔ በወልቃይት በኩል ወደሱዳን የመውጫ ኮሪደር ስለነበረው እንዳሻው እየተንቀሳቀሰ የሚፈልገውን ሲያወጣና ሲያስገባ ኖሯል። ከኤርትራው አማፂ ቡድን ሻዕቢያ ጋር የጦርነት ትብብር ከማድረግ ጨምሮ በተለያየ መንገድ ይተጋገዙ ነበር። ደርግን አምርሮ ይጠላ የነበረው አማራውም “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” በሚል ብሂል ህወሓትን አቅፎና ደግፎ ለስልጣን አብቅቶት ነበር።

የአሁኑ ሁኔታ ግን ይለያል። ህወሓት በአሁኑ ሰአት ጠላቶቼ ናቸው በምትላቸው በኤርትራና በአማራ ክልል ነው ተከባ የምትገኘው። ሱዳንን ማየት እየናፈቃት ይቀራል! አልፎ አልፎ ልትፈፅመው ከምትችለው የሽፍትነት ተግባር ውጪ ኮንቬንሽናል ጦርነት የማካሄድ አቅሙም ፍላጎቱም አይኖራትም። ታንክና ሞርታር ይዛ ያልቻለችውን ጦርነት ክላሽ ይዛ ትጀምራለች ተብሎ አይጠበቅም። ያም ሆኖ ግን የአማራ ክልል ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በትጥቅም ሆነ በስንቅ ሁሌ ዝግጁ ሆኖ ድንበሩን በተጠንቀቅ ሊጠብቅ ይገባል።

ከዚህ በተረፈ የትግራይ ህዝብ ከህወሓት ትርፍራፊ ቡድን ጋር መልካም ቆይታ እንዲኖረው እመኛለሁ። ወርቅ ያበደረ ሰራዊታችን ጠጠር እየሰበሰበ መኖር የለበትም እላለሁ።

ጋዜጠኛ ሃይሌ ሙሉ በፊስ ቡክ የግል ገጹ ካሰፈረው የተወሰደ

Exit mobile version