Site icon ETHIO12.COM

የተኩስ አቁም ስምምነቱ በወልቃይትና ራያ ላይ የሚኖረው አንድምታ!

ትላንት ሰኔ 21/2013 ከስአት በኋላ ጀምሮ የፌዴራል መንግስት በትግራይ ክልል የተናጠል ተኩስ አቁም እርምጃ በመውሰዱ ምክንያት የመከላከያ ሰራዊቱ ከመቀሌ መውጣት መጀመሩን የተለያዩ መገናኛ ብዙሀን እየዘገቡ ነው፡፡ በምትኩም የመቀሌ ሕዝብ በነቂስ ወደ አደባባይ ወጥቶ ርችት በመተኮስ ጭምር ደስታውን እየገለጸ ይገኛል፡፡

የትህነግ ሀይሎችም ወደ መቀሌ ከተማ መግባታቸው ተነግሯል፣ ይኸ ነገር ለዘላቂ ሰላም ሲባል የተወሰነ ከሆነ ችግር የለውም፣ ውሳኔው የትግራይን ሕዝብ የሚጠቅም ሆኖ ከተገኘም እሰየው ያሰኛል፡፡ ሆኖም የትህነግ ሰዎች ከአሁኑ እንደሚያስወሩት እኛ አሸንፈን ነው መከላከያ የወጣው እያሉ የሰላም ስምምነቱን የሚያደናቅፉ ከሆነ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንዳያመዝን በጥንቃቄ መመልከት ይገባል፡፡

የመከላከያ ሰራዊቱ ከመቀሌ ወጥቶ የት ነው የሚቆየው? በአሁኑ ወቅት በትግራይ ውስጥ የሚገኘው ሰራዊት ከመቀሌ ብሎም ከመላው ትግራይ ጠቅሎ የሚወጣ ከሆነ ትህነግ ሒደቱን ለማደናቀፍ ቢሞክር ወይም ከሁለት አመት በፊት ወጣቶችን በመጠቀም ለማድረግ እንደሞከሩት መከላከያ ትጥቁን ይዞ መውጣት አይችልም ቢሉ ምን አይነት እርምጃ ሊወሰድ ይችላል? ከትግራይ ከወጣ በኋላስ ማረፊያው/መቆያው የት ይሆን? በኤርትራ በኩል ያለው ድንበርስ? የሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት ያለባቸው ይመስለኛል፡፡

ከዛ ውጭ ቀጥሎ የሚመጣው ነገር በህግ ማስከበር ተግባሩ ላይ ግንባር ቀደም ሚና የነበራቸው አጎራባቾቹ የአማራና የአፋር ክልሎች በትህነግ ከሚመራው የትግራይ ክልል አስተዳደር ጋር ሊኖራቸው የሚችለው የጉርብትና ግንኙነት ምን ሊመስል ይችላል የሚለውም ሌላኛው አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ ይህም ሆኖ በተለይም ከአማራ ክልል ጋር የሚኖረው ፍጥጫ መፍትሄ እስካልተበጀለት ድረስ ከዛም ያለፈ እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡

ለምን ቢባል የወልቃይትና የራያ ጉዳይ እስካሁንም ድረስ ገና እልባት ስላላገኘ ትህነጎችና ተባባሪዎቻቸው አቅማቸው እስከፈቀደ ድረስ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም አካባቢዎቹን መልሰው ለመቆጣጠር መሞከራቸው አይቀርምና ነው፡፡ በተቃራኒው የአማራ ክልልና ህዝብ በአጠቃላይና የወልቃይትና የራያ ህዝብ ደግሞ በተለይ የእነዚህን አካባቢዎች ሕዝብ ዳግም ለባርነት አሳልፈው እንደማይሰጡ የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡

ስለሆነም በሁለቱ ክልሎች መካከል ለጊዜው ሊኖር የሚችለው ግንኙነት በፍጥጫና በውጥረት ላይ የተመሰረት እንደሚሆን ይገመታል፣ በአካባቢዎቹ ከአሁኑ እየተስተዋለ ያለው ሁኔታም ይህን እውነታ ያመለክታል፡፡ እናም ይኸ ሁኔታ መልሶ ወደ ጦርነት እንዳያስገባ የፌዴራል መንግስት በአግባቡ ይዞ የሁለቱን ክልሎች ግንኙነት ማሻሻል የሚያስችሉና የህዝቡ ጥያቄ ህግና ስርአትን ተከትሎ ምላሽ እንዲያገኝ የማድረግ አካሄድ አንዱ የድርድር አካል እንዲሆን ማድረግ ይኖርበታል ባይ ነኝ፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን የአማራ ክልል መንግስትና ሕዝብ ራሱን አደራጅቶ አካባቢዎቹን መልሶ ላለማስወሰድና የጥቃት ሰላባም እንዳይሆኑ ለማድረግ የሚያስችል ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በእርግጥ አሁን ላይ በአካባቢዎቹ የተሰማራው ሀይልና የአካባቢው ታጣቂ አካባቢዎቹን ለመከላክል የሚያስችል ዝግጅት ስላደረጉ ያን ያህል የሚያሰጋ ነገር እንደሌለ ማረጋገጥ ችያለሁ፣ ሕዝቡም ከእነዚህ ሀይሎች ጎን በተጠንቀቅ ቆሟልና ያን ያህል የሚያሳስብ ጉዳይ አይሆንም፡፡

ሲሳይ መንግስቴ

Exit mobile version