Site icon ETHIO12.COM

ሰብአዊ ዕርዳታ በአውሮፕላን እንዲሆን ጥያቄ ቀረበ

የተከዜ ድልድይ መውደሙን ተከትሎ የዓለም የምግብ ድርጅት ዕርዳታ በቀጥታ በአውሮፕላን እንዲሰራጭ ጥያቄ ማቅረቡ ተሰማ። ዝርዝር ሃሳቡና አውሮፕላኖቹ ከየት እንደሚነሱ መረጃው አላብራራም።

ይህ የተሰማው የትህነግ ታጣቂዎች ድልድዩን እንዳፈረሱት መረጃ ማግኘቱን መከላከያ በሚስጢር አግባብ ላላቸው ክፍሎች ማስታወቁን የሰሙ ምንጭ ሳይጠቅሱ መናገራቸውን ተከትሎ ነው። በረራው በቀጥታ ከሱዳን ወደ መቀለ ወይም ሌሎች ከተሞች ወዳሉ አየር ማረፊያዎች እንደሚሆን ግን ግምት አለ።

እንደ መረጃዎች ድልድዩ እንዲፈርስ የተደረገው አስቸኳይ ዕርዳታ ለሚፈልጉ ወገኖች የአውሮፕላን ትራንስፖርት እንዲፈቀድ ታስቦ ስለመሆኑ ማረጋገጫ አለ። መረጃው አድበስብሶ በመንግስት ሚዲያ ቢገልጽም፣ የትህነግ የቲውተር ተዋጊዎች ቀደም ሲል ነጻ ቀጠናና ኮሪዶር እንዲከፈት ሲወተውቱ እንደነበር ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል።ኽርማን ኮሆን ይህ በይፋ ከመባሉ በፊት ለትህነግ ሰዎች ወደ ሱዳን የሚያስገባ ነጻ መስመር እንዲፈቀድላቸው ጠይቀው እንደነበር አይዘነጋም።

በትግራይ አስቸኳይ እርዳታ ለሚፈልጉ መድረስ እንዳለበት፣ መጪው ክረምት ከመግባቱ በፊት ይኸው ተጋባር ሊጠናቀቅ እንደሚጋብው ማንም ሰብአዊ የሆነ ሁሉ ከማንም አካል መመሪያ ሳይቀበል ሊተገብረው እንደሚገባ ይፋ ያምናሉ። መንግስትም ሆነ በዘመናቸው ትህነግ የተጠቀመበትን ስልት የሚያውቁ ግን ዳግም ትህነግ ረሃብን ተጠቅሞ ክንዱን ሊያጠነክር እንደሆነ ይሰጋሉ። እርዳታ ሰጪዎችና ለጋሽ አገራትም መንግስት ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ይህንኑ ፍርሃቻቸውን ያሰፋዋል። በዚሁ መነሻ ሳቢያ እርዳታው ሲጓጓዝ ቁጥጥር ሊደረግ ይገባል ሲል መንግስት የያዘውን ጥብቅ አቋም ይደግፋሉ።

በሌላ በኩል የትህነግ ደጋፊዎች መንግስት ጭካኔ የተሞላበት ድርጊቱ የሚገለጸው እርዳታ እንዲሰራጭ ክፍትና ነጻ ኮሪዶር ባለመፍቀዱ ነው ሲሉ ያማርራሉ። በዚህ ሁለት አመላከት መካከል ነው እንግዲህ ይህ የአውሮፕላን ስምሪት ጥያቄ የቀረበው።

ቶምይ ቶምፕሰን የዓለም የመግብ ድርጅት አስቸኳይ እርዳታ አስተባባሪ ከመቀለ በሳተላይት ስልክ ለሮይተር እንዳሉት ስሙን ሳይጠቅሱ ” hot zone” ባሉት ስፍራ ጦርነት ስለነበር 35 የሚሆኑ ሰራተኞቻቸው መንቀሳቀስ አልቻሉም ነበር። ይሁን እንጂ ከ48 ሰዓት በሁዋላ በሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ እርዳታ ማድረግ የሚችሉበትን እንቅስቃሴ በፍጥነትና በተቀላጠፈ መልኩ እያከናወኑ መሆኑንን አመልክተዋል። ግን 40 ሺህ ለሚጠጉ አስቸኳይ ዕርዳታ ፈለጊዎች ለመድረስ የመንገድ ችግር መኖሩን አመልክተዋል።

ለጥያቄው የመንግስት ምላሽ ባይታወቅም፣ ለጊዜው 400 ሺህ ኩንታል ምግብ በመቀለ መጋዘን መኖሩ ተመልክቷል። ኦቻ እንዳለው አሁን ችግሩ የስልክ፣ የመብራትና፣ የነዳጅ እንዲሁም የገንዘብ እጥረት ማጋጠሙ ነው። ይህን አስመልክቶ ከመንግስት ወገን የተባለ ነገር የለም። ይሁን እንጂ ለጋሽ አገራት ለትግራይ እጃቸውን እንዲዘረጉ በይፋ ዛሬ ማለዳ በተደረገ ስብሰባ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካይነት ጥሪ አቅርቧል። በመቀለ በከፍተኛ ደረጃ የነበረውን ዘረፋ ተከትሎ መንግስት አከማችቶት የነበረው እህል ስለመዘረፉ ወይም እጥረት ስለማጋተሙ እስካሁን የተባለ ነገር የለም።

Exit mobile version