Site icon ETHIO12.COM

በትግራይ የተለያዩ ከተሞች ንጹሀን ሰዎች ጭካኔ በተሞላበት መልኩ እየተገደሉ መሆኑ ታውቋል


በትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች ንጹሀን ሰዎች ከመንግስት ጋር ሰርታችኋልና ከኛ ጋር አለተባበራችሁም በሚል ምክንያት ጭካኔ በተሞላበት መልኩ እየተገደሉ መሆኑን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ምንጮች ገልጸዋል።

ምንጮቻችን ባደረሱን መረጃ መሰረት ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር ተባብራችኋል፣ የእርዳታ እህል አከፋፍላችኋል በሚሉና መሰል ምክንያቶች በመቐለ ከተማ ብቻ 38 ንጹሀን ሰዎች ተገድለዋል።

በግፍ ከተገደሉት ንጹሀን መካከልም በኩሓ ክፍለ ከተማ ሕሹ ኣዲሱ በአሰቃቂ መንገድ የተገደለበት መንገድ የአሸባሪው ቡድን ጭካኔ ማሳያ ነው ብለዋል ምንጮቻችን።

በተመሳሳይ በመኾኒ የሚኖሩ ሙስሊሞች ተገድለዋል ንብረታቸው ተዘርፏል ያሉት ምንጮቻችን፤ ንብረታቸው ከተዘረፈባቸው ግለሰቦች ውስጥ አቶ ዓብደልቃድር ወዳኞ እንደሚገኙበት አስታውቀዋል።

እንደ ምንጮቻችን መረጃ ይህ ገዳይ የህወሓት ቡድን ማንነት ላይ ያተኮረ ግድያ እየፈጸመ ይገኛል፤ በግጀት የሚኖሩ ሙስሊሞች ዋና ታርጌት በመሆናቸው እስካሁን ድረስ በርካቶች በግፍ ታርደዋል።

ለውጡን ደግፋችኋል የተባሉ ሰዎች ተሰብስበው በሶስት ሲኖትራክ መኪና ተጭነው ወደ ተንቤን እንደተወሰዱና ምን እንደተፈጸመባቸው እንዳልታወቀ ምንጮቻችን አስታውቀዋል።

ህዝቡን ከዘራፊዎች ለማዳን በሚል በበጎ ፍቃደኝነት ፀጥታ ሲያስከብሩ የነበሩ ወጣቶች በመቐለ፣ሽረ እና ዓዲግራት መረሸናቸው ታውቋል።

የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር የኢንቨስትመን ቢሮ ሃላፊ የነበረውን አመራር በአሰቃቂ መንገድ ገድለው አስክሬኑ ቆራርጠው ለጅብ ሰጥተው እንደነበርና ከጅብ የተረፈው አካል ተለቅሞ ባለፈው ሳምንት በመቐለ ገብርኤል ቤተክርስትያን ቢቀበርም በድጋሜ አስክሬኑ ከመቃብር አውጥተው ለጅብ በመስጠት አረመኔያዊ ድርጊት እንደፈጸሙ ምንጮቻችን ገልጸዋል።

ድንበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን የሀገር መከላከያ ሰራዊት በወጣ ማግስት በትዊተር ገጹ ላይ ባስተላለፈው መልዕክት፤ በትግራይ ክልል ባሉ የጤና ተቋማት ላይ ዝርፊያ ተፈጽሟል፤ ህዝቡም ለሰቆቃ ተዳርጓል ማለቱ ይታወቃል።

በተመሳሳይ አምንስቲ ኢንተርናሽናል በትግራይ ያሉ ንጹሀን ዜጎች የበቀል እርምጃ ሊወሰድባቸው ይችላል የሚል ስጋት እንዳለው መግለጹም አይዘነጋም።

(ኢ.ፕ.ድ)

Exit mobile version