Site icon ETHIO12.COM

”የለውጥ ደጋፊ ናችሁ” በሚል በራያ አዘቦ ንጹሃን ተገደሉ፤ በሺህ የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል

አሸባሪ የህወሃት ቡድን በራያና አዘቦ ”የለውጥ ደጋፊዎች ናችሁ” በሚል ንጹሃን ዜጎችን እየገደለ መሆኑን የራያ ራዩማ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ጽህፈት ቤትና የውጭ ግንኙነት ሀላፊ ጌታቸው ከበደ ገለጹ፡፡

ባላቸው ስጋት ምክንያት ከአስር ሺህ በላይ ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውንም ገልጸዋል።

ኢዜአ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከትግራይ ክልል መልቀቅ ተከትሎ በራያ አካባቢ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ምን እንደሚመስል ከአቶ ጌታቸው ከበደ ቆይታ አድርጓል፡፡

የፌዴራል መንግስት በትግራይ ክልል የተናጠል የተኩስ ማቆም ውሴ መወሰኑን ተከትሎ አሸባሪ የህወሃት ቡድን ”የለውጥ ደጋፊ ናችሁ” በሚል ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ማድረሱን አቶ ጌታቸው ከበደ ተናግረዋል፡፡

ቡድኑ ንጹሃንን እየገደለ፣ ቤትና ንብረቶችን በማውደም ራያ አዘቦ ተብሎ በሚታወቀው መሆኒ፣ መቻሬ፣ ጨርጨር እና ሓደ አልጋ በታባሉ አካባቢዎች በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ከባድ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል፡፡

ሽብርተኛ ቡድኑ ቀደም ሲል መከላከያ ወደ አካባቢው በገባበት ወቅት አቀባበል ያደረጉ፣ ስንቅ ያቀረቡ፣ ለሰራዊቱም የባህል ልብስ ያለበሱ ናቸው በሚል በሻይ መሸጥ የሚተዳደሩ፣ የባህል ልብስ የሚሰሩ፣ በጫማ ማጽዳት ስራ የተሰማሩ ደሃ ሰዎችን በግፍ በመግደል የጥፋት ስራዎችን መስራቱን አመላክተዋል፡፡

በዚህም በአካባቢው እየተፈጠረ ባለው ችግር ስጋት ምክንያት ከአስር ሺህ በላይ የሚቆጠሩ ነዋሪዎች መከላከያ ባለባቸው የራያ የገጠር እና የከተማ አካባቢዎች በርታህላ፣ ታኦ፣ ዳዩ፣ አላማጣ፣ እንዲሁም ራያ ቆቦ ከተማ ጭምር ተጠልለው ይገኛሉ ብለዋል፡፡

አሸባሪው የህወሃት ቡድን ”እናስተምራችዋለን” በሚል ሰበብ በርካታ ወጣቶችን በሲኖ ትራክ መኪና ጭነው በመውሰድ ኢ ሰብዓዊ ድርጊት እየፈጸሙባቸው መሆኑንም ተናግረዋል።

የለውጥ ደጋፊዎች ናችሁ በሚል የጊዜያዊ አስተዳደር አባላት እና የነዋሪዎች መኖሪያ የሆኑ ከአራት መቶ በላይ ቤቶችን መቃጠላቸውን ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል መቀሌ እና በሌሎች ከተሞች ከጊዜያዊ አስተዳደሩ እና መከላከያን ተባብራችኋል ያላቸውን ንጹሐን ላይ ግድያ እየፈጸመ እንደሚገኝ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ ገልጿል።


Exit mobile version