Site icon ETHIO12.COM

የሩሲያና የኢትዮጵያ ወታደራዊ የቴክኒክ ትብብር ውይይት እየተካሄደ ነው

ሁለቱ አገራት ግንኙነታቸውና በወታደራዊ መስክ ያላቸው ውለታ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይና ምክትላቸው ደመቀ መኮንን ፕሬዚዳንት ፑቲንን ካናገሩ በሁዋላ ይበልጥ ማደጉ ተወስቷል። ውይይቱ ወታደራዊ ቴክኒክ ድጋፍ መስጠትን አስመልክቶ አጀንዳ አጽድቆ ውይይቱን መጀመሩን ኢቢሲ አስታውቋል።

የሁለቱን ሀገሮች ወታደራዊ ትብብር ማጠናከርን ዓላማ ያደረገው 11ኛው የኢትዮ – ሩሲያ ወታደራዊ የቴክኒክ ትብብር የጋራ ውይይት በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ነው። ውይይቱ 10ኛውን የወታደራዊ ቴክኒክ ፕሮግራም አጀንዳ በማጽደቅ መጀመሩን ተነግሯል።

በመኮንኖች ክበብ እየተካሄደ የሚገኘው ምክክር፣ የኢትዮጵያን እና የሩሲያን ወታደራዊ ቴክኖሎጂ ፣ ክህሎት እና እውቀት ማሳደግ ላይ ያተኮረ ነው፡፡

በመክፈቻው ስነ-ስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የመከላከያ ፋይናንስ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ ፣ ሁለቱ ሀገሮች ከ1898 ጀምሮ በዲፕሎማሲ፣ በወታደራዊ ፣ በኢኮኖሚ ፣ በፖለቲካ እና በማህበራዊ መስክ ታሪካዊና ጠንካራ ግንኙነት ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ተገናኝተው ከመከሩ ወዲህ የሁለቱ ሀገሮች ግንኙነት በጣም ጥብቅ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የህግ ማስከበር ዘመቻ ስታደርግ ሩሲያ የውስጥ ጉዳያችን እንደሆነ አቋም ይዛ በመንቀሳቀሷ፣ ባደረግነው 6ኛው ምርጫ፣ በታላቁ ህዳሴ ግድብና በሌሎችም ሀገራዊ ጉዳዮች ከኢትዮጵያ ጎን ቆማ ወዳጅነቷን በማሳየቷ ሚኒስትር ዴኤታዋ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የዚህን ስብሰባ ውጤትንም የሁለቱን ሀገሮች የጋራ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ ተግባራዊ እንደሚደረግ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

በሩሲያ ፌዴሬሽን የወታደራዊ የቴክኒክ ትብብር ምክትል ዳይሬክተር ፑንቹክ አናቶሊ፣ የቆየ ወዳጅነት አለን፤ በወታደራዊ መስክ ብዙ የኢትዮጵያ መከላከያ አባላት በሩሲያ ስልጠና ወስደዋል፤ ይህ ስብሰባም የሁለቱን ሀገሮች የቆየ ወዳጅነት የሚያሳድግ እንደሚሆን አመልክተዋል።

የመከላከያ ኢንዱስትሪ እና ደጀን አቭዬሽንን የቴክኖሎጂ አቅም ለማሳደግ እየተደረገ ያለውን ስራ በጋራ እንደሚያጎለብቱም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በኢትዮጵያ በኩል የመከላከያ ፋይናንስ ዘርፍ ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፣ አየር ሀይል እና የመከላከያ ኢንዱስትሪ ዘርፍ በውይይቱ ተሳታፊ ሲሆኑ ፣ በሩሲያ በኩሉ ደግሞ ፣ በኢትዮጵያ የሩሲያ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተሬከሂን ኢቭጌኒ እንዲሁም በሩሲያ መከላከያ ቴክኒካል ዘርፍ ላይ የሚሰሩ ተቋማት የስራ ሀላፊዎች፣ ኤክስፐርቶች እና ሌሎች አባላት መሳተፋቸው ታውቋል።


Exit mobile version