Site icon ETHIO12.COM

የፋሽን አምባሳደሯ

ኢትዮጵያ ባህላዊ ገፅታዋን ተላብሳ ፣የህዝቧ ስልጣኔ፣ ማንነትና የአኗኗር ዘይቤ በዓለም ደረጃ ይታይ ዘንድ እርስዋንና ህዝቧን በደንብ የሚያውቁ ልጆቿ ጥረት ወሳኝ ነው። በመላው ዓለም የኢትዮጵያን ባህላዊ አልባሳት በማስተዋወቅ ተፈላጊነታቸውና ተመራጭ መሆናቸው ከፍ እንዲል አዳዲስ ዲዛይኖች በመንደፍ እና በማዘጋጀት ጉልህ ሚና ያላቸው ኢትዮጵያዊያን ዲዛይነሮች በርክተዋል።

ዛሬ በፋሽን አምዳችን በጣሊያን አገር የምትኖር ወጣት ኢትዮጵያዊት ዲዛይነር እና በፋሽን ኢንዱስትሪው ሙያዋን ለማሳደግ የምትተጋ በጥረቷም በአገር ውስጥና በምትኖርበት ጣሊያን እያበረከተች ያለችውን አስተዋፅኦ እንዳስሳለን። የኢትዮጵያን ባህላዊ አልባሳት በውጭ ዓለም በማስተዋወቅና የተለያዩ ፋሽን ሾው መርሀ ግብሮችን በማዘጋጀት ዘርፉን ለማሳደግ ጥረት ከሚያደርጉ ታታሪ ወጣቶች ትመደባለች። ኑሮዋን ጣሊያን ያደረገቸው ዶክተር ሰናይት ማሪዮ።

በለምለሚቷ ደቡብ ክልል ወላይታ ሶዶ ከተማ ነው ተወልዳ ያደገችው። በልጅነቷ ቤተሰቦቿ ስኬቷን አብዝተው ይመኙ ነበርና በትምህርቷ ጥሩ ውጤት ታስመዘግብ ዘንድ ክትትል ያደርጉላት ነበር። ዛሬ ለፋሽን እንዱስትሪው ዕድገት የበኩሏን እየተወጣች ያለችው ዶክተር ሰናይት ትናንት ህይወት በብዙ ዘርፍ አስገኝታለች።

በልጅነቷ በትምህርቷ ጠንካራና የደረጃ ተማሪ የነበረችው ዶክተር ሰናይት፣ ልጅ ሆና የህክምና ዶክተር አልያም ደግሞ ጠበቃ የመሆን ብርቱ ፍላት ነበራት። ነገር ግን ትምህርቷን ስታጠናቅቅ ዕድል ያስገኛላት ለሌሎች የምታውቀውን የምታካፍል ቀለም የተጠሙ ተማሪዎችን ዕውቀት የምትቸር መምህርት ሆነች። በመምህርነት ሙያም በርካታ ዓመታት አገልግላለች።

ራሷን ሁሌም የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ ትተጋ የነበረችው ሰናይት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ትምህርቷን እየተከታተለች ሳለ በዩጋንዳ የትምህርት ዕድል(ስኮላር ሺፕ)አገኘች። ወደ ፋሽን ኢንዱስትሪው እንድትጋባ መንገድ የሆናትም ይህ አጋጣሚ ነበር። እዚያው ዩጋንዳ ትምህርት ቤት እያለች የተዋወቀቻት አንዲት ኬኒያዊት የሰናይትን ሁኔታ አይታ እሷ ባላት የሞዴሊንግና ያፋሽን ትምህርት ቤት አብራት እንድትሠራና ትምህርቷንም እንድትማር ጋበዘቻት። ሰናይትም ግብዣውን ተቀብላ ዛሬ ላይ እየሠራችበት ወዳለው የፋሽንና ሞዴሊንግ ሥራ ገባች።

በዚህም የተለያዩ አልባሳትን በመሥራት አዳዲስ ዲዛይኖች በመንደፍና በማዘጋጀት ማስተዋወቅና የተለያዩ መድረኮችን በመፍጠር ወደ ሙያው ይበልጥ መቅረብ ጀመረች። በዚህም እስከአሁን ድረስ ወደ ሙያው አዲስ የሚቀላቀሉ ኢትዮጵያዊያን ዘርፉን ማሳደግ እንዲችሉ፣የአገራቸውን ባህል ማሳደግና ለፋሽን እንዱስትሪው ያለቀ አስተዋፅኦ ማበርከት ይችሉ ዘንድ ያለ ስስት ልምዷን በማካፈልና ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው በመሥራት ላይ ትገኛለች።

በተለይም በአገር ውስጥ የተለያዩ መድረኮችን በመፍጠር የእሷና ሌሎች ኢትዮጵያዊያን አዳዲስ ዲዛይኖች እንዲተዋወቁ የፋሽን ሾው መድረኮችን በማዘጋጀት ለህዝብ አቅርባለች። በዚህም አዳዲስ ሞዶሌችና የፋሽን ዲዛይን ባለሙያዎች በማነቃቃት ለዘርፉ ዕደገት ትልቅ ሚና አበርክታለች። በአገር ውስጥ በተለያዩ ከተሞችና ባልተለመደ መልኩ ደግሞ ወደ ክልል ከተሞችና የተለያዩ አካባቢዎች በማምራት የፋሽን ዲዛይን ማስተዋወቂያ መድረኮችን በማመቻቸትና ለህብረተሰቡ በማስተዋወቅ ሙያውን ለማስተዋወቅ ብዙ ጥረቶችን አድርጋለች። በዚህም ብዙ ወጣቶች ሙያውን እንዲያውቁትና አገራቸውን ለዓለም ማስተዋወቅ እንዲችሉና ስለሙያው ግንዛቤ አንዲጨብጡ አድርጋለች።

የፋሽን ሾው ትርዒት በማዘጋጀት አዳዲስ የፋሽን ዲዛይኖችና ሙያውን ካስተዋወቀችባቸው ከተሞች መሀል አዲስ አባባ፣ወልቂጤ፣አርባ ምንጭ፣ ወላይታ ሶዶ ይገኙበታል። በከተሞቹ የሚገኙ ወጣቶችም ከዚህች ብርቱ ኢትዮጵያዊ ወጣት ጋር በመቀራረብ ልምድ ቀስመዋል።

የባህል አምባሳደሯ ወጣት ሙያዋን በማሳደግ ከኢትዮጵያ አልፋ በዓለም ዙሪያ የኢትዮጵያንና የአፍሪካዊያን ባህል የሚያንፀባርቁ ፋሽኖችን በተለየዩ የዓለም ከተሞችም አዘጋጅታ አስተዋውቃለች። በዚህም በአሜሪካና በአውሮፓ ትላልቅ ከተሞች ማለትም በአሜሪካ ኒውዮርክ፣ በጣሊያን ሚላን፣ በሮም በእንግሊዝ ሎንደን፣ በፈረንሳይ ፓሪስ እና ሌሎች በፋሽን ዲዛይን ያደጉ አገራትና ከተሞች በተጨማሪ በአፍሪካ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ፣ ጋናና ኬኒያ የወጣቷ ዶክተር ሰናይት ማሪዮ ልዩ የፋሽን ትርዒት መድረኮችና ፋሽን ሾው ዝግጅቶች የቀረበባቸው ከተሞችና አገሮች ናቸው።

ሰናይት ለአገሯ ፋሽን እንዱስትሪ እድገት ብዙ የመሥራትና የራሷን አሻራ የማሳረፍ ጥረት በማድረግ ላይ የምትገኝ ሲሆን ፣ አገራችን ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ ያላትን የሠራ ዕድል መጠቀም ብትችል የራስን ባህልና ማንነት ከማስተዋወቅ ባለፈ ዘርፉ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ በመሆን ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ትናገራለች። የፋሽን ኢንዱስትሪው በአገር ደረጃ ገና ብዙ የሚቀረውና እጅግ ሊሠራበት የሚገባ መሆኑንም ትናገራለች።

ሌሎች ዓለማት ለፋሽን እንዱስትሪው ዘርፍ ትኩረት በመስጠት ወጣቶች ወደዘርፉ እንዲገቡና ለአገራቸው ዕድገት ወሳኝ ሚና እንዲወጡ እንደሚያደርጉ ገልፃ፣ በአገራችንም ያለውን ሰፊ ዕድል ወደጠቀሜታ በመለወጥ ኢንዱስትሪውን በማሳደግ የወጣቶችን ሰፊ ህልም ማሳካትና አገራዊ ጠቀሜታን ማጉላት እንደሚያስፈልግ ታመለክታለች።

በተለይ በአገራችን በአዲሰ መልክ ወደ ሥራው የሚገቡ ወጣቶችና ተቋማት ዘርፉን ማሳደግ ይችሉ ዘንድ የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው ማድረግ፣ ሥራዎቻቸው የሚያቀርቡባቸውን መድረኮች ማመቻቸትና በገቢና ወጪ ንግድ ላይ ያለውን ሁኔታ ምቹ ማድረግ የሚገባ መሆኑን ትገልፃለች። ወጣቶች ሥራዎቻቸውን ለማስተዋወቅ ምቹ ሁኔታ ሊፈጠርላቸው እንደሚገባና በራሳቸውም ሙያውን በመውደድና በማክበር ለእድገቱ በህብረት የመሥራት ልምድ ሊያካብቱ አንደሚገባ ትመክራለች።

የፋሽን ኢንዱስትሪው ማደግ ከቻለ ለአገር ከፍተኛ ገቢ ሊያስገኝ እንደሚችል ትጠቁማለች። ዶክተር ሰናይት፣ የጣልያኗ ሚላን ከተማ በቱሪዝም ሀብቷ በዓመት ከምታገኘው ገቢ በዚያው ከተማ ውስጥ በአንድ ሳምንት ውስጥ ብቻ ተዘጋጅቶ የሚቀርበው ያፋሽን ትርዒት የተሻለ ገቢ የሚያስገኝ መሆኑን በማስረጃነት ታቀርባለች። ከዚህም ልንማርበት ይገባል ነው የምትለው። ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ ብንሠራ የሚያስገኘው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን ትጠቁማለች።

ዘርፉን በማሳደግ የአገርን ገፅታ መገንባት፣የውጭ ምንዛሬ ማግኘትና ለብዙ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ያስችላል በማለትም ለዘርፉ ሊሰጠው የሚገባውን ትኩረት ትጠቁማለች። ተቋማት የፋሽን ኢንዱስትሪው ሁሉም ጋ በቀላሉ የሚደርስበትና ከተሠራበት አትራፊ መስክ መሆኑን አውቀው ፋሽን ላይ ከሚሠሩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ጋር አብረው ሊሠሩ እንደሚገባም ታስረዳለች።

ወደፊት በዘርፉ ጠንክራ ሥራ ሠርታ ይበልጥ አገሯን ማስተዋወቅና ኢንዱስትሪውን ማሳደግ የምትፈልገዋ ዶክተር ሰናይት፣ አሁን ላይ እያደረገች ያለችውን ዘርፈ ብዙ አጋራዊ ጠቀሜታ ያለው ተግባሯን ይበል የሚያስብል ነውና በርቺ ማለት እንወዳለን። እኛም ከዚህች ትጉህ የፋሽን ዲዛይን ባለሙያና የባህል አምባሳደር ጋር የነበረን ቆይታ በዚሁ አበቃን፤ቸር ይግጠመን።

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 28/2013 ዓ.ም -ተገኝ ብሩ

Exit mobile version