ETHIO12.COM

“መግደል ሲችል ከወደቅንበት አንስቶ በእንክብካቤ ስላቆየን ክብርና ምስጋና ይገባዋል”

ከሱዳን ሀምዳይት የስደተኛ ጣቢያ በመነሳት ሀገር ውስጥ ይገኝ ወደነበረው ምግበ ሀይሌ ከተባለው የሽብር ቡድኑ አመራር ጋር ለመገናኘት ዕቅድ እንደነበራቸውና ወደ ሀገር ውስጥ ለመግባት ሲሞክሩ በሰራዊቱ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።

ሐምሌ 6 ቀን 2013

በትህነግ የተሳሳተ ዓላማና የውሸት ፕሮፓጋንዳ በመታለል በሀገርና በህዝብ ላይ ታሪካዊ ስህተት መፈፀሙና የትግራይ ህዝብም ለመከራና ለስደት እየተዳረገ መሆኑን የተማረኩ የቡድኑ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ገለፁ።

በጥቅምት 24 በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ከተሰነዘረ በኋላ የመከላከያ ሰራዊቱ በወሰደው ህግ የማስከበር ዘመቻ ከፍተኛ ሽንፈት የደረሰባቸው የጁንታው አመራሮችና አባላት በስደተኛ ስም ወደ ሱዳን መሸሻቸው ይታወሳል።

በሱዳን ሀምዳይት በተባለው የስደተኛ ጣቢያ በመቆየት ከጁንታው ከፍተኛ አመራሮች ጋር ግንኙነት በመፍጠርና መመሪያ በመቀበል ከ300 በላይ የመገናኛ ሬድዮኖችና የህክምና መሳሪያዎችን እና መድሀኒቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ሲሞክሩ በሰራዊታችን የተማረኩት ኮሎኔል ባህረ ተበጀና ሻምበል ተክለወይኒ ታረቀ የተባሉት የቡድኑ አመራሮች የሽብር ቡድኑ በተሳሳተ መረጃ ህዝቡን ለስደትና ለችግር እየዳረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ከተማረኩት የሽብር ቡድኑ አመራሮች ውስጥ የትህነግ የምዕራብ ትግራይ ሚሊሻ አስተባባሪና በኋላም የብርጌድ አመራር በመሆን የተለያዩ የጥፋት ተልዕኮዎችን ሲፈፅሙ የቆዩትና በ2003 ከመከላከያ በጡረታ የተሰናበቱት ኮሎኔል ባህረ ተበጀ አንዱ ናቸው።

ኮሎኔሉ ከድርጅቱ ከፍተኛ አመራር በሆነው ፍስሀ ማንጁስ በተሰጣቸው መመሪያ መሰረት ከሱዳን ሀምዳይት የስደተኛ ጣቢያ በመነሳት ሀገር ውስጥ ይገኝ ወደነበረው ምግበ ሀይሌ ከተባለው የሽብር ቡድኑ አመራር ጋር ለመገናኘት ዕቅድ እንደነበራቸውና ወደ ሀገር ውስጥ ለመግባት ሲሞክሩ በሰራዊቱ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።

ጁንታው በሱዳን ከሚገኙ አራት የስደተኛ ጣቢያዎች ውስጥ ህፃናት ታጣቂዎችን በመመልመልና የሸሹትን የልዩ ሀይልና ሚሊሻዎችን የማደራጀት ስራ በድብቅ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።



በስደተኛ ጣቢያዎቹ በታጣቂዎቹ ስም ከተለያዩ ሀገሮች የሚላከው ገንዘብ በሽብር ቡድኑ አመራሮች ስለሚዘረፍ እርስ በእርስም ተደጋጋሚ ግጭትና ቅራኔ እንደነበር ሲታዘቡ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

በትህነግ የተሳሳተ ፕሮፓጋንዳና ዓላማ አራት ወንድሞቻቸውን ማጣታቸውን የሚናገሩት ኮሎኔል ባህረ ተበጀ በተለይም አውሮፓና አሜሪካ በመሆን የትግራይ እናቶችና ህፃናትን መከራ እያራዘሙ የሚገኙትን የውሸት ሚዲያዎችና ምሁራን ነን ባዮች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ጠይቀዋል።

ምርኮኞቹ በሰራዊቱ በሚያዙበት ወቅት እጅግ ተዳክመው የነበሩ መሆናቸውን ገልፀው በሰራዊቱ እጅ ከገቡ በኋላ እየተደረገላቸው ያለው ድጋፍ ከሚጠብቁት በላይ በመሆኑ “መግደል ሲችል ከወደቅንበት አንስቶ በእንክብካቤ ስላቆየን ክብርና ምስጋና ይገባዋል” ብለዋል።

በሚያዝያ 28 ከአሸባሪው የትህነግ ቡድን ተልዕኮ ተሰጥቷቸው 322 ታጣቂዎችን በመያዝ ወደ ሀገር ውስጥ በመግባት ለጥፋት ሊሰማሩ ከነበሩት የቡድኑ ታጣቂዎች አብዛኞቹ ሲማረኩ የተቀሩት መደምሰሳቸው ይታወሳል ።

ብዙአየሁ ተሾመ – የመከላከያ ፌስ ቡክ
ፎቶግራፍ ብዙአየሁ ተሾመ 

Exit mobile version