Site icon ETHIO12.COM

“መከላከያ ሠራዊት ትዕዛዝ ሲሰጠው አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ በሚያስችል ቁመና ላይ ነው”

“መከላከያ ሠራዊት ትዕዛዝ ሲሰጠው አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ በሚያስችል ቁመና ላይ ነው ” የመከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ

መከላከያ ሠራዊት ትዕዛዝ በሚደርሰው ጊዜ አስፈላጊውን እርምጃ ሊወስድ በሚያስችል ቁመና ላይ እንደሚገኝ የመከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ አስታወቁ።

የመከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ እንደተናገሩት፤ አንዳንድ አሉባልተኞች ያላወቁት ነገር የተኩስ አቁም ርምጃ በክላሽና በመድፍ ብቻ አይደለም ። ከቃላት መወራወርም መቆጠብን ጭምር ያካተተ ነው።

መቼና ምን ማድረግ እንዳለብንም ጠንቅቀን እንውቃለን ያሉት ኮሎኔል አዳነ፤ መከላከያ ሠራዊት ትዕዛዝ በሚደርሰው ጊዜ አስፈላጊውን እርምጃ ሊወስድ የሚችልበት አቋም ላይ እንዳለ አስታውቀዋል።

ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ጭምር በሚያራግቡት ወሬ አንደናገርም ያሉት ኮሎኔል ጌትነት ፣ ከአወጣነው አዋጅ ጋር የሚጻረር ሥራ ላለመሥራት ስንል ብዙ ከመናገር ተቆጥበናል ብለዋል።

እንደ ኮሎኔል ጌትነት ገለጻ፤ ሠራዊቱ የት ላይ ምን ማድረግ እንዳለበት እና ምን አይነት እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ያውቃል፣ የተዛቡ መረጃዎች በተለቀቁ ቁጥር ምላሽ መስጠቱ አስፈላጊ አይደለም የሚል አቋም ተይዟል።

የተዛቡ መረጃዎች ቢሰራጩም በእነሱ ፕሮፓጋንዳ ልክ ወሬ ባለማብዛት ጨዋነታችንን ማሳየት ይጠበቅብናል ያሉት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ፤ችግሮች የሚባባሱ ከሆነ ግን የመንግሥትን ውሳኔ ተከትሎ የሚተላለፉ እርምጃዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ መግለጻቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version