Site icon ETHIO12.COM

“ከአማራ ሕዝብ እና ከሀገር መከላከያ ሠራዊታችን ጎን በመሠለፍ መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን” የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ የሰጠው መግለጫ ሙሉ ቃል!

በሀገራችን ኢትዮጵያ ከለውጡ ማግሥት አንስቶ የሕዝቦችን ፍትሐዊ የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ሥርዓት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሪፎርሞችን በማካሄድ ትርጉም ያላቸው ስኬቶች ተመዝግበዋል፡፡

በሀገራችን አዲስ የለውጥ ምዕራፍ ከተጀመረበት ማግስት አንስቶ ባለፉት ሦስት አመታት ውስጥ የተጀመረው ሁለንተናዊ የብልጽግና ጉዞ እጅግ የሚበረታታ ውጤት የተመዘገበበትና አካታች እንደነበር በተለይ ለክልላችን ማኅበረሰቦች ግልጽ ነው፡፡

በአንፃሩ በሸፍጥ እና በሴራ ፖለቲካ የረዥም ዓመታት ልምድ ያካበተው የሕወሓት ሽብርተኛ ቡድን ላለፉት ዓመታት ክልላችንን ጨምሮ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶችንና በንጹሐን ዜጎች ላይ የተፈፀሙ ጥቃቶችን ከማቀናበር፣ ከመደገፍ እና በቀጥታ ከመሳተፍ ባለፈ የሀገራችን መከታና የሕዝባችን አለኝታ በሆነው የመከላከያ ሠራዊታችን ላይ የክህደት ጥቃት በመፈፀም ሉዓላዊነታችንንም ጭምር አደጋ ውስጥ የጣለ የሽብር ተግባር ፈፅሟል፡፡

ህልውናውን ማቆየት የሚችለው በግጭት ብቻ እንደሆነ አጥብቆ የሚያምነው ይህ ጠብመንጃ አምላኪ ቡድን በቅርቡ ለሰላም ሲባል የተከፈተለትን በር ጥሶ በመግባት የሽብር ተግባሩን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትን የተለያዩ አካባቢዎች በመውረር በንጹሐን ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለው ግፍ ሳያንስ ሕጻናትን ጠብመንጃ በማስታጠቅ እና በጦርነት እንዲማገዱ በማድረግ እጅግ አስነዋሪ ተግባር በመፈፀም ላይ ይገኛል፡፡

ይህ የሽብር ቡድን ክልላችንን እንደሁለተኛ የሽብር ማስፈፀሚያ ግንባር በመቁጠር ተላላኪዎችን በማሰልጠንና በመደገፍ የበርካታ ንጹሐንን ህይወት እንዲቀጠፍና አለመረጋጋት እንዲሰፍን በማድረግ ሀገር የማፍረስ እና ሕዝብን ከሕዝብ የማጋጨት ዓላማውን በተጨባጭ ከማረጋገጥ ባለፈ ወደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሚወስደውን መንገድ ለማዘጋት እና የግንባታ ሂደቱን ለማስተጓጎል አበክሮ በመሥራት የተለመደ የተላላኪነት ተግባሩን ለመፈፀም ሲውተረተር ቆይቷል፡፡

በመሆኑን ይህ ሽብርተኛ ቡድን ራሱ በለኮሰው እሳት ተቃጥሎ ማለቁ የማይቀር የመሆኑ ዕውነታ እንደተጠበቀ ሆኖ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር እየተወሰደ ያለውን ሀገራዊ እርምጃ የክልላችን መንግሥትና ሕዝብ አጥብቀው ከመደገፍ ባሻገር ከአማራ ሕዝብ እና ከሀገር መከላከያ ሠራዊታችን ጎን በመሠለፍ የሚጠበቅባቸውን መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ያረጋግጣል፡፡

መላ የክልላችን ሕዝቦች በሕወሓትና በተላላኪዎቹ የተዛባ የፈጠራ ትርክት እና የሐሰት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ሳትበገሩ ወንድማማችነት አንድነታችሁንና ሀገራዊ ሕብረታችሁን ይበልጥ በማጥበቅ የአካባቢያችሁን ሰላም ከማስጠበቅ ባሻገር ሀገራዊ ኀላፊነታችሁን በላቀ ሀገራዊ ስሜት እንድትወጡ የክልሉ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የባንዳዎችን ሴራና ተንኮል በማክሸፍ ሀገራዊ አንድነታችን እና ሉዓላዊነታችን የበለጠ ይጠናከራል!!

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥት

ሐምሌ 9 ቀን 2013 ዓ.ም አሶሳ


Exit mobile version