Site icon ETHIO12.COM

የመዋጮ መንግስት

አሜሪካና አውሮፓ በዚህም በዚያም ብለው አዲስ አበባ ላይ የመዋጮ መንግስት እንዲቋቋም ውስጥ ለውስጥ እየሰሩ ነው የሚለውን ወሬ መናቅ አያስፈልግም። የሟሸሸውን የህወሀት ቡድን በጄሶና በቅስት ጠግነውና ቀና አድርገውት ለአቅመ ትንኮሳ ከማብቃት አልፈው ሌሎች ሃይሎችን በማደራጀት የሽግግር ዓይነት በመዋጮ የሚመሰረት ጊዜያዊ መንግስት እያሰቡ እንዳለ ከጭምጭምታ ያለፈ ነገር እየሰማን ነው። ክብራቸውን ያጎደፉ፡ ሰውነታቸውን ያረከሱ፡ ህሊናቸውን ያጡ ቆሞ ቀር ‘ፖለቲከኞችን’ በጀርባ ተደራጅተው ለአራት ኪሎ ቤተመንግስት የሚሆን መንግስት የሚመስል ነገር እንዲያዘጋጁ የቤት ሰራ እንደሰጧቸው በስፊው ይወራል። ይህን መረጃ በግሌ ትክክለኛነቱን ለማረጋገጥ ያልቻልኩ ቢሆንም ፈጽሞ ውሸት ነው ብዬ ላጣጥለውም ወኔ አጥሮኛል። ነጠብጣቦችን ገጣጥሞ አንድ ምስል ማየት ከተቻለ እነአሜሪካን ሀገር ለማፍረስ ያሰፈሰፉ ሃይሎችን በማደራጀት የጠሚ/ር አብይን መንግስት ስልጣን እንዲያጋራ አልያም እንዲወገድ የሚያደርግ እንቅስቃሴ ጀምረዋል።

እንግዲህ የኢትዮጵያ ጉዳይ ጎንበስ ቀና እያደረገን ቀጥሏል። በአባይ ግድብ ሙሌት ጮቤ የረገጠችዋን ልባችንን የሚያስከፉ ክስተቶች መምጣታቸው የማይቀር ነው። በእርግጥ ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው ከተነሱና ለእነአሜሪካን ወጥመድ ጀርባቸውን ከሰጡ ኢትዮጵያችን አዲሱን ዓመት በአዲስ ተስፋ ልትቀበለው እንደምትችል አምናለሁ። ከአንድ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ ባለፈው የሰማሁት መረጃ እነአሜሪካን ሊደርሱ ያሰቡትን ፌርማታ በግልጽ አመላክቶኛል። እንደመረጃው ከሆነ ኮረምና አላማጣ የተለቀቁበት ምክንያት ዳግማዊ ሀውዜን እንዲፈጠር የተቀናጀ መረብ መዘርጋቱን መንግስት በመድረሱ ነው። እቅዱ ህጻናት ወታደሮችንና እናቶች ያሉበት ሲቪል ሃይል ከፊት ተሰልፎ የኢትዮጵያን ጦር እንዲገጥም፡ በውጤቱም ህጻናቱና እናቶቹ በጦርነቱ በብዛት እንዲሞቱ፡ ይህንንም በእርዳታ ሰራተኛነት ስም ወደሀገር ቤት የገቡ ጋዜጠኞች ከህወሀት ሰዎች ጋር በመሆን በዘመናዊ ዲጂታል ካሜራ እንዲቀርጹትና ለዓለም እንዲያሰራጩት ነው። በውጤቱም የኢትዮጵያ መንግስት ህጻናትንና እናቶችን ጨፈጨፈ በሚል በዓለም ዓቀፍ የጦር ወንጀሎች ፍርድ ቤት ለመክሰስ ትልቅ ማስረጃ እንዲሆን ታቅዷል። የኢትዮጵያ የደህንነት መስሪያ ቤት እቅዱን አነፍንፎ በመድረስ የኢትዮጵያ ሰራዊት አከባቢውን በመልቀቅ ታላቁን እልቂት አስቀርቶታል። አሁንም መንግስት ሁኔትውን በጥንቃቄ ማየትና እርምጃውንም በሃላፊነት ለማከናወን እየሰራ ነው። ወጥመድ ውስጥ ላለመግባት የሚያደርገውን ጥንቃቄ እንደሚቀጥልበት ይታመናል። የህጻናት ወታደሮችን ጉዳይ እነአሜሪካን ዝምታን የመረጡት ያለምክንያት እንዳልሆነ ግልጽ ነው።

እንግዲህ ለህወሀቶች የድል ፌሽታ የሆነውና የኢትዮጵያ መንግስት በከፍተኛ ሀገራዊ ሃላፊነት የወሰደው እርምጃ ሌላ ታሪክ የለውም። ህወሀቶች በአደባባይ ይጨፍሩ እንጂ ህጻናቱና እናቶቹ ባለመጨፍጨፋቸው ብስጭት ውስጥ መከረማቸውንም ሰምተናል። አሁንም ይህን እቅድ እነአሜሪካ አልተዉትም። በሁሉም ግንባሮች ህጻናትና እናቶች እንዲሰለፉ ተደርጓል። ዓላማዉ ሁለት መንታ ግቦችን አስቀምጧል። የኢትዮጵያ ጦር ቦታዎችን ከለቀቀ፡ የድል ነጋሪት እየጎሰሙ በሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የስነልቦና ሽንፈት እንዲደርስበትና መንግስቱ ላይ ተቃውሞ እንዲያነሳበት ነው። ሁለተኛ መንታ ግብ የኢትዮጵያ ጦር ወጊያውን ገጥሞ ህጻናቱንና እናቶቹን ከገደለ እነአሜሪካን ላዘጋጁት የጦር ወንጀል ፍርድ ቤት የክስ ዶሴ ማቅረብ ነው። በአጭሩ በተዘዋዋሪ እየተፋለምን ያለነው ከአሜሪካንና አውሮፓ ጋር መሆኑን በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል።

አሜሪካን ሀገር ቢፈርስ ጉዳይዋ እንዳልሆነ በእኛ እድሜ ያፈረሰቻቸው አምስት ሀገራት ምስክር ናቸው። ከ20ዓመት በላይ አፍጋኒስታን ቆይታ፡ ሀገሪቱን አወላልቃና ብትንትኗን ካወጣች በኋላ ህዝቡን ለአውሬዎች ትታ እብስ ያለችበት የቅርብ ጊዜው እርምጃዋ የአሜሪካን ፍላጎት እስከየት ጥግ ሊደርስ እንደሚችል እንገነዘባለን። ኢትዮጵያ ተሸንሽና ቁርጥራጭ ሀገራት ምስራቅ አፍሪካ ላይ ቢፈጠሩ ምርጫዋ ላይሆን ይችላል። ብሄራዊ ጥቅሟን እስካስጠበቀ ድረስ ግን አይኗን ሳታሽ እንዲፈጸም ልታደርገው ትችላለች። አውሮፓዎች አፍቃሪ ህወሀት የሆኑትንና አዲስ አበባ የገቡትን የምስራቅ አፍሪካ ተወካይቸውን ወይዘሮ ሲመድቡ ኢትዮጵያ ላይ ምን እንዲመጣ እንደፈለጉ በግልጽ የሚያሳይ ውሳኔ ነው። ወይዘሮዋ ዓመታትን የዘለቀ፡ በፍጹም ታማኝነት የቆየ የህወሀት ወዳጅነት ያላቸው፡ ስለኢትዮጵያ መንግስት የሚጻፉ አሉታዊ ነገሮችን እየለቀሙ በግል የማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው የሚያጋሩ ዓይን ቀቅለው የበሉ አፍቃሪ ህወሀት ናቸው። እኚህን ወይዘሮ ለምስራቅ አፍሪካ ተወካይ የመደመበው የአውሮፓ ህብረት ዙሩን ለማክረር እንደወሰነ የሚያመላክት ነው።

ከእንግዲህ ተስፋችን ማን ነው? የኢትዮጵያ ህዝብ አይደለምን? እነአሜሪካ ሀገር ለማፍረስ ሲዶልቱ፡ ህወሀትን እንደትሮይ ፈረስ ተጠቅመው የኢትዮጵያን አንድነት ሲያወላልቁ በዝምታ የማይመለከተው የኢትዮጵያ ህዝብ ከድብታና ውዥንብር ውስጥ በመውጣት ሀገር ለማዳን ጉዞ ላይ ያለውን ባቡር መሳፈር ግድ ይላል። በአፋር የአፋር ህዝብ ክተት ብሏል። በምዕራብ የአማራ አርሶ አደር ነፍጥ አንስቷል። በራያም የኢትዮጵያ ውድ ልጆች ደማቸውን ሊያፈሱ፡ አጥንታቸውን ሊከሰክሱ በቀበሮ ጉድጓድ ገብተዋል። ከአራቱም የኢትዮጵያ አቅጣጫዎች የኢትዮጵያን አድን ሃይል በአንድ ልብ ግንባር ዘምቷል። ይህ ታሪካዊ ሀገር የማዳንን ትንቅንቅ ሁለት ምርጫዎችን ከፊታችን አስቀምጧል። እንደልማዳችን እንደታሪካችን ጠላትን አደባይተን፡ ትምህርት ሰጥተን፡ ኢትዮጵያን ዳግም እንዳይነኩ አድርገን ፋይሉን እንዘጋለን፡ አልያም በከፋፋይ አጀንዳዎች ተሸንፈን፡ በሀሰተኛ ፕሮፖጋንዳ ተወናብደን፡ ሀገራችንን ለአውሬዎች ሲሳይ በማድረግ ሀገር አልባ ዜጎች ሆነን እንቀራለን። ምርጫው የእኛው ነው።

Via መሳይ መኮንን

Exit mobile version