Site icon ETHIO12.COM

አፋር ግንባር በመልሶ ማጥቃት ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ ደርሷል፤ የተኩስ አቁም ያለህ!!

“ስንት ለስንት አለቀ” በሚመስል፣ እንደ እግር ኳስ ውድድር ውጤት እየተገለጸ ያለው ጦርነት በየአቅጣጫው ጭንቀትን ወልዷል። ራሱን ” አክቲቪስት” የሚል አንድ የማህበራዊ ሚዲያ ፊት አውራሪ ” የድል ዜና” ብሎ አንድ ሃረግ ጽፏል። ከስሩ “በፎቶ ይረጋገጥ” ከሚለው አስተያት መሰል ጥያቄ ጀምሮ ሁሉም ማለት በሚቻል ደረጃ የሰው ልጆችን ህልፈት፣ስቃይና ደም ለማየት በመጓጓት ከሚሰጡት አስተያተ ውጭ፣ ይህ አስከፊ ጉዳይ እንዴት ያልቃል” እንዴት ያብቃ? በሚል የመፍትሄ ያለህ የሚሉ ድምጾች ብዙም አይታዩም።

“አሸባሪው ጁንታ ተመልሶ ይመጣል በሚል አበባ ገዝታችሁ ስትጠባበቁ የነበራችሁ ምን ተሰማቹህ? ለአገር መከላከያን፣ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ ክብር ስጡ። አሸባሪው አፈር እየጋጠ ነው” ሲሉ አቶ ታዬ ደንደአ በፊስ ቡክ ገጻቸው ገልጸዋል። አቶ ታዬ እንደመንግስት ሃላፊነታቸው ለጉዳይ ቅርበት ስላላቸው ይህን መስለ መረጃ ዝም ብለው ያጋራሉ ተብሎ አይታሰብም። እሳቸው ቃል በቃል ባይገልጹትም መከላከያ ትግራይን ለቆ ከወጣ በሁዋላ ታላቅ የተባለ ጉዳት በትህነግ ላይ መድረሱ ተሰምቷል።

አሸባሪ ተብሎ በገሃድ የተፈረጀውና ቀደም ሲል ጅምሮ መንግስትም ሆኖ አሜሪካ ከአሸባሪዎች መዝገብ ያልፋቀችው ትህነግ ከፍተኛ አመራር ጌታቸው ረዳ እንደወትሮው እያከታተሉ ባይሆንም ዛሬ “ድሉ ቀጥሏል” ሲል በቲውተር ገጻቸው አስቀድመው መረጃ አስፍረዋል። በዛው ጎን ለጎን አማራውን የማግባባት ፍላጎት አሳይተዋል። ሰሞኑንን ለአሜሪካና ጀርመን ጥቅም ተላላኪ ሪፖርተሮችን አሰማርተው የፈለጉትን አቋም የሚያሰራጩባቸው የአሜሪካና ጀርመን ራዲዮ ጣቢያዎች የትህነግን መሪ በማቅረብ ” ትህነግ ህዝብን በጠላትነት ፈርጆ አያውቅም” የሚል ቅሰቀሳም ሲያሰራጩ ነበር።

“ድሉ ቀጥሏል” የሚለው ዜና እየተሰማ ባለበት ተመሳሳይ ሰዓት “አዲስ አበባ ከተማ በቄሮ የተከበበ ነው። ለምን እንደትግራይ ወጣቶች ትግሉን ተቀላቅለው መስዋ ዕትነቱን ቀንሰው ድሉን አያፈጥኑትም። የቄሮው ትግል የት ገባ? ለምን አያግዝም?ይህን አስተያየት ስጥበት” ሲል ስታሊን የሚባለው የትግራይ ሚዲያ ሃውስ ቅሰቀሳ ሰራተኛ ለፕሮፌሰር ሕዝቄል ትዕዛዝ መስለ ጥያቄ ሲያቀርብ ተሰምቷል። ፕሮፌሰሩ ሲመልሱ ” የዛኔ ኢህአዴግን ለማውረድ የተሰራ ስትራቴጂ አሁን ላይ መጠበቅ አግባብ አይደለም” ሲሉ ተጠምደዋል። በዚሁ አስተያየታቸው ግርጌ ” ኦሮሞን መናቅ ነው” ከሚለው ጀምሮ በወቅቱ ትህነግ ኦሮሞ ላይ የፈጸመውን በመዘርዘር ሰፊ ውግዘት ተሰንዝሯል።

ቄሮ ድሉን ያጣድፍ ሲል ትህነግ ጥያቄ ማንሳቱን፣ ትህነግ አሁንም እንደቀድሞው ኦሮሞን መጠቀሚያ ለማድረግ እይቀሰቀሰ ጎን ለጎን አቶ ጌታቸው አሸባሪው ሃይል ድል እንደቀናው ባስታወቁበት የቲውተር ገጻቸው ተተኪ ሃይል ሲመጣ እየተደመሰሰ መሆኑንን አመልክተዋል። የትኞቹን አካባቢዎች እንደተቆጣጠሩ ግን አላብራሩም። በጽሁፋቸው ካለተብራራው የድል ዜናቸው ጎን ለጎን ” ከአማራ ሕዝብ ጋር ችግር የለብንም” ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይንና ምክትላቸውን ደመቀ መኮንን በመጥራት እነሱ እስከሚወገዱ ትግሉ እንደሚፋፋም ግን አስታውቀዋል። አቶ ጌታቸው ዛሬ ማለዳ ይህን ይበሉ እንጂ ቀደም ባሉት ጊዜያት “ወራሪ” እያሉ የሚጠሩትን ህዝብ ” ገና ከአማራ ጋር የምናወራርደው ሂሳብ አለ” ማለታቸው ይታወሳል። ዛሬ አቶ ጌታቸው “ድሉ ቀጥሏል” ባሉበት መልዕክታቸው ” ከአማራ ህዝብ ጋር ጠላት አይደለንም” ለማለት ያነሳሳቸውን ምክንያት ይፋ አላደረጉም።

የአፋር ክልል የሰላምና ደህንነት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ሁመድ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ” የትህነግ አሸባሪ ቡድን በኢትዮጵያ ጉዳይ ብቻውን ፈላጭ ቆራጭ መሆንን የሚሻና ይህም ካልተሳካ የህወሀት የበላይነት የሌለባት ኢትዮጵያ ትፍረስ የሚለውን የረጅም ጊዜ ህልማቸውን ለማሳካት በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የክህደትና አረመኔያዊ ተግባር ከመፈፀም ጀምሮ በተለያዩ አከባቢዎች በርካታ የክህደት ተግባራትን እያከናወነ ነው። ጁንታው በአፋር አርብቶ አደሮች ያደረሰው ጥቃት የሽብር ተግባሩ የለየለት ደረጃ መድረሱን ማሳያ ነው ” ሲሉ ድርጊቱ እንደተፈጸመ በይፋ አስታውቀዋል።

የህወሀት ጁንታ በፈንቲ ረሱ ዞን በያሎ ወረዳ በኩል የከፈተውን ጦርነት በሌሎች የክልላችን አካባቢዎችም ሊደግም ስለሚችል ህዝቡ አካባቢውን በንቃት ሊጠብቅ እንደሚገባ የአፋር ክልል ሰላምና ደህንነት ቢሮ ባስተላለፈው ጥሪ መሰረትና በክልልና የፌደራል ሃይል ጥምረት፣ የትህነግ ሃይል ጥቃት እንደደረሰበት መረጃዎች እየወጡ ነው። አቶ ጌታቸው ካሉት በተቃራኒ የህጻናት አስከሬን፣ የተማረኩ ልጆችና በሆስፒታል ህክምና ላይ ያሉ የትግራይ ህጻናት ምስል ከአፋር አክቲቪስቶች ማህበራዊ አምድ እየታየ ነው። እጅግ በርካታና ለመስማት የሚከብድ ቁጥር አስከሬን በገልባጭ መኪናዎች እታጨቀ ሲመላለስ እንደነበር፣ የአፋር ክልል ሃይል አስከሬን መቅበር እንዳቃተው ሳይቀር የአፋር አክቲቪስቶች ምስል አስደግፈው እየጻፉ ነው።

የትህነግ የፕሮፓጋንዳ አባል ከሆኑት መካከል አሉላ ሰለሞን የሚባለው መትረየስ የተጠመደባቸው ሄሊኮፕተሮች በማጥቃቱ ወቅት ስራ ላይ ውለው እንደነበር ያመነው የአብራሪዎቹን ስም በመጥቀስ ጥቃት መሰንዘሩን በማመልከት ነው። አሉላ ጥቃቱ ሲሰነዘር ተሳትፈዋል ያላቸውን አብራሪዎች ስም ጽፏል። የጠቀሰውና ያወገዛቸው ሰዎች ስም እርግጠኛ መሆኑ ባይታወቅም፣የትግራይን ክልል አልፎ አፋር ከ30 ሺህ ህዝብ በላይ ያፈናቀለ ጥቃት በአሸባሪው ሃይል ሲሰነዘር አሉላ ” አግባብ ነው” በሚል የድል ዜና ሲያሰማ ነበር።

በርካታ ወታጣቶች ተማርከውና ቆስለው፣ እንዲሁም ተገድለው በሚታይበት የአፋር ግንባር የአካባቢው የተፈጥሮ አቀማመጥ የአየር ጥቃት ለመሰንዘር ስለሚያመች ከመንግስት ወገን ይህ ሃይል ወደ ሜዳ እንዲወጣ ፍላጎት እንዳለ ስለወታደራዊ ጥቃት የሚያውቁ አስቀድመው መናጋእራቸውን ጥቅሰን ከቀናት በፊት ዘግበን ነበር። ከመንግስት ወገን ምንም ዓይነት ምላሽ ባይሰጥም የአፋር ክልል ሃይልና ረዳቶቹ ጥቃቱን ቀልብሰዋል መባሉ ተሰምቷል።

በዚሁ አቶ ጌታቸው ” የመንግስትን ሃይል ለማዳከም ነው” ሲሉ የገለጹት የአፋር ጥቃት እርዳታ የጫኑ መኪኖች መስተጓጎላቸውና አስር ካሚዮኖች ላይ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል። ይሁን እንጂ ጥቃቱን ማን እንዳደረሰ መግለጫውን ያወጡት የተባበሩት መንግስታት አካሎች ተጠያቂ ያደረጉት ሃይል የለም። መንግስት በበኩሉ አሸባሪው ሃይል እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ በረሃብ ለተጎዱ ወገኖች ለመድረስ ሲጓዙ በነበሩ ካሚዮኖች ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ወዲያውኑ አስታውቋል። አሸባሪ የሚባለው ቡድንም ይህን ክስ በኦፊሳል አላስተባበለም። ይልቁኑም መንግስትን ለማዛል በሚል ስትራቴጂ ጦርነት መክሰቱን በሮይተርስ በግልጽ አስታውቋል።

መንግስትና የመከላከያ ሃላፊዎች በየትኛውም ሰዓት አስፈለጊ የሆነውን እርምጃ ለመውሰድ በተጠንቀቅ ላይ መሆናቸውን በተደጋጋሚ እያሳወቁ ነው። እንደውም “አፍ የሚያሲዝ” እርምጃ በመውሰድ አሸባሪውን ሃይል መንቀል የሚችል ዝብጅት ላይ እንዳሉ እያስታወቁ ነው። በውልቃይት በኩል፣ በማይጽብሪ ጥቃት ተሞክሮ በመክሸፉ ፊቱን ወደ አፋር የመለሰው ትህነግ ይህንን ማስጠንቀቂያ እንዳልሰማ ሆኖ ያዋጣል ያለውን እርምጃ እየወሰደ ነው።

ዜጎች ይህ ስምንት ወር በላይ ያስቆጠር ግጭት እንዴት እላባት ያገኛል? በሚል ጭንቀት ውስጥ ናቸው። የአማራ ክልል ክተት ብሏል። ሌሎች ክልሎችም ሃይላቸውን ወደ ግንባር እየልላኩ ነው። ሁሉም ክልሎች በመግለጫቸው ትህነግን አሸባሪ በማለት በማውገዝ ሊነቀል እንደሚገባው እየተናገሩና በተግባር ድጋፍ እየሰጡ ነው። ይህ እየሰፋ የሄደው የጦርነት አካሄድ በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ የሚሰሩ የትግራይ ልሂቃን የሉም። ሌሎች ምሁራንም የሰላም አማራጭ ማቅረብ አልቻሉም። ከየአቅጣቻው የሚወጣው የጦርነት ዜና ብቻ ነው። ሕዝብ ለጭንቀት፣ ለመፈናቀል፣ ለችጋር፣ ለኑሮ ውድነት ተዳርጓል። አገሪቱን ነክሰው የያዟት ሃይሎች በማዕቀብ ጉዳቱን እያባባሱ ነው።

እነሱ ባሰቡት ሳይሆን አሁን ላይ የጦርነቱ መልክ መቀየሩን የሚያሳይ መረጃ እየተሰማ ነው። ምን አልባትም ይህ መረጃ በቅርቡ ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። እጅግ ሰፊ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ሰሞኑንን አልቀዋል። በአሸባሪው ሃይል ላይ በተወሰደ የሰማይና የምድር መልሶ ማትቃት የአፋር ሜዳዎች ላይ ምስኪኖች ረግፈዋል። ዜናው የሚያሳዝን እንጂ የሚያስጨፍር አይደለም። ሁሉም ወገን በሚችለው ሁሉ ወደ ልቡ እንደመለስ የሚወተውቱ ከዚህ የከፋ እንዳይሆን ሰግተዋል።


Exit mobile version