Site icon ETHIO12.COM

አሸባሪው ህወሃት የሚፈጽመው የሰብዓዊ ድጋፍ የማደናቀፍ ድርጊት በዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ሊወገዝ ይገባል … ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት

በአሸባሪው ህወሃት የሚፈጽመው የሰብዓዊ ድጋፍ በማደናቀፍ የፖለቲካ ትርፍ የማግኘት ጥረት በዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ሊወገዝ እንደሚገባው ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አመለከተ።

ጽህፈት ቤቱ በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ የሚገኝበትን ሁኔታ የተመለከተ መግለጫ አውጥቷል።

በመግለጫው የኢትዮጵያ መንግስት አርሶ አደሩ እንዲያርስና የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲቀላጠፍ በማሰብ የተናጠል የተኩስ አቁም ማድረጉን ተከትሎ የአሸባሪው ህወሃት ትርፍራፊዎች የሰብዓዊ ድጋፍ ሂደቱን ችግር ውስጥ እንደከተቱት አመልክቷል።

የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔው ከተላለፈበትና የኢፌዴሪ አገር መከላከያ ሰራዊት ከመቀሌና ሌሎች የክልሉ ከተሞች እንዲወጡ ከተደረገበት ከሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም በፊት በነበረው ሁኔታ የብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ኮሚቴ በሶስት ዙር የሰብዓዊ ድጋፍ ሲያደርግ እንደነበር አስታውሷል።

ከዚያ በተጨማሪም ለስርጭት የተዘጋጀ 400 ሺህ ኩንታል ስንዴ እና 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት ተከማችቶ እንደነበር ገልጿል።

በተጨማሪም 14 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ ህዝቡ እንዲጠቀምበት በሚል በክልሉ ዲፖዎች ውስጥ ተከማችቶ እንደነበር ጠቅሷል።

አጋሮችና አለም ዓቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች በክልሉ ድጋፍ ማድረግ እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ በመንግስት መፈጠሩን ያወሳው መግለጫው፤ መንግስት አሁንም ቢሆን ለህዝቡ የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እንዲሆን የብሔራዊ ደህንነት ለአደጋ በማያጋልጥ መንገድ በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ አመልክቷል።

ከአዲስ አበባ ተነስተው እንዲሁን ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው እንዲያርፉ በማድረግ የተሟላ የሰብዓዊ ድጋፍ በረራ ፈቃድ መሰጠቱን የጠቀሰው መግለጫው፤ በአዲስ አበባ በኩል የማለፍ ቅድመ ሁኔታ የተቀመጠው የማይጣስና የሚከበረውን የአገር ደህንነትን ለመጠበቅ በማሰብ እንደሆነ አመልክቷል።

ባለፈው ሳምንት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሁለት በረራ ማድረጉንም ገልጿል።

በከባድ መኪና የሰብአዊ ድጋፉ በአፋር ክልል በኩል እንዲጓጓዝ እየተደረገ መሆኑን የገለጸው መግለጫው፤ መዘግየትን ለማስቀረትና የተቀላጠፈ የፍተሻ ስራ እንዲከናወን ለማድረግም ጥረቶች እንዳሉ ጠቅሷል።

ከቀናት በፊት የሰብዓዊ ድጋፍ ከሰመራ አባላ መስመር ሲያጓጉዙ የነበሩ መኪናዎች ላይ በአሸባሪው ህወሃት አማካኝነት የተፈጸመውን ጥቃት በድጋሚ ያወገዘው መግለጫው፤ በቡድኑ አማካኝነት እየተፈጸመ ያለው የሰብዓዊ ድጋፍን በማደናቀፍ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚደረገው ጥረት በዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ሊወገዝ እንደሚገባው አመልክቷል።

አሸባሪው ህወሃት ህጻናት ወታደሮችና የታጠቁ ሲቪሎችን በመጠቀም በአገር መከላከያ ላይ ትንኮሳ እየፈጸመ መንግስትን ከዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ጋር ያልተገባ ንትርክ ውስጥ ለመጨመር እየተፍጨረጨረ እንደሚገኝ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከአጋሮች ጋር ያለመታከት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጾ፤ ምግብና መድሃኒት ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ተደራሽ እንዲሆን እንደሚሰራ አረጋግጧል።

ከሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪዎች ጋርም በትብብር መስራቱን እንደሚቀጥል ገልጿል።ENA

Exit mobile version