ETHIO12.COM

አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቅጥፈት መግለጫ አወጣ፤ ቡድኑንን እየበጠበጠ ነው

“ሕዝባችንና መንግስታችን” የሚል ተደጋጋሚ ሃረግ በመጠቀም መገልጫ ያሰራጨው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አትሌት ለሜቻ ግርማ በ3000 መሰናክል እንዲወዳድር መደረጉ አግባብ እንዳልሆነ አስታወቀ። በመግለጫው የሰጠው ምክንያትና ቀደም ሲል ያቀረበው ሪፖርት አይሰማማም። ፌዴሬሽኑ በቶኪዮ ኦሊምፒክ አጠቃላይ ሂደት ላይ ያሰራጨው መግለጫ ” ከውዲሁ የለሁበትን” ዓይነት ሲሆን ውጤቱን አብዝቶ ሊጎዳ የሚችልና ኢትዮ 12 ባደረገው ማጣራት ማጭበርበር ይየተሞላበት ነው።

ለሜቻን በተመለከተ

ከኦሊምፒክ ሰፈር ባደረግነው ማጣራት “በጥር 8 ቀን 2013 በተደረገ የመጀመሪያ ማጣሪያና በ50ኛው የኢትዮጵያ ሻምፒዮና አልተሳተፈም” በሚል አትሊቲክ ፌዴሬሽን ያቀረበው ትክክል ሲሆን የቀረበበት አግባብ ግን ሸፍጥ ነው። በጥር ወር የመጀመሪያ ማጣሪያ ለሜቻ ኮቪድ ስለነበረበት ከሆቴል አይወጣም ነበር። ይህ በፌዴሬሽኑ የሚታወቅና ኮቪድን አስመልክቶ በህግ ደረጃ የሚሰራበት አግባብ ስለነበር ለውንጀላ አይበቃም።

ለሜቻ እግሩ በመታመሙ ምክንያት ከውደድሩ እንዲሰናበት መደረጉን ያመለክተው መግለጫ፣ በ50ኛው የኢትዮጵያ ሻምፒዮና አለመሳተፉን እንደ ጉድለት ያነሳል። በሄንግሎ ማጣሪያም አለመወዳደሩን ጉድለት አድርጎ ያያል። በዚህ ጉዳይ ባደረግነው ማጣራት ለሜቻ እግሩን በመታመሙ ጤናው ላይ ትኩረት እንዲደረግ በሃኪም በታዘዘው መሰረት ሆቴል ሆኑ ክትትል እያደረገ ነበር። እየተሻለውን ወደ ብቃቱ እየተመለሰ በመሆኑ ኦሊምፒክ በቂ ጊዜ ስላለ በደን እንዲዘጋጅ ቢጠይቀም ” ካሁን ብሁውላ ዋጋ የለውም” በሚል ለኦሊምፒክ ኮሚቴ በቀረበ ሪፖርት ተሰናብቷል። ይሁን እንጂ በተሰናበተ ሳምንት ጊዜ ለሜቻ በሞናኮ ዳይመንድ ሊግ 8፡07 በመሮጥ ሪኮርድ አስመዝግቦ ማሸነፍ ችሏል።

የሌሜቻ መቀነስ አገር እንደሚጎዳና እሱን እንዲተካው የተያዘው አትሌት ሚኒማ ለማሟላት የተቸገረ፣ ልምምድ የማይጨርስና ከውቅቱ የለሜቻ ብቃት ጋር ሊወዳደር ስለማይችል እነ ሃይሌ ገብረ ስላሴ ያሉበት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጭምር በለሜቻ መሳተፍ ያምናሉ። በቶኪዮ ኦሊምፒክ መንደር ያናገርናቸው እንዳሉን ” ጉዳይ ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ ከሆነ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ለሜቻ መመረጡ ፍትሃዊ ነው። ሌላ ችግር ካለ በሌላ አግባብ መነጋገር እንጂ ህዝብን ባልሆነ ወሬ ማደናገር አግባብ አይድለም” ሲሉ ነግረውናል።

ስለ ኮ/ል ደራርቱ፣ ዶ/ር በዛብህ ወልዴ ዶክተር አያሌው

አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ኮሎኔል ደራርቱና ዶክተር በዛብህ ወልዴ አትሌቶቹን ማግኘት በማይችሉበት ሁኔታ 38 ኪሎ ሜትር ርቀው እንደሚገኙ መግለጫው አስታውሶ ይህም የሆነው ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ችግር ምክንያት ስለሆነ መንግስትና ሕዝብ እንዲያውቅ ብሏል። ባደረግነው ማጣራት በቶኪዮ ኦሊምፒክ መንደር የራስዋ የጃፓን አትሌቶች አመራሮች ድርሽ አይሉም።

የተቀሩትም እዛ ያሉ የኦሊምፒክ አመራሮች እስከ 48 ኪሎሜር እርቀው እንደሚገኙ በስፋራው ያሉ ነግረውናል። ቡድኑ የህክምና ቲም እንደሌለው ተደርጎ የቀረበውና የዶክተር አያሌው ጉዞ በ27 መሆን በክስ መልኩ ውጤቱ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ተደርጎ በመግለጫው ለቀረበው ያነጋገርነው አትሌት ” አጠገባችን ዶክተር ቃልኪዳንና ዶክተር ሕይወት ዘላለም አሉ” የሚል ምስክርነት ሰጥቶናል። ጥያቄው “ዶክተር አያሌው ለምን አልሄዱም?” ከሆነ ፌዴሪሽኑ ለሌሎቹ ባለሙያዎች እውቅናና ሙያዊ ብቃት ክብር በመስጠት የዶክተር አያሌውንም እዛ መሆን አስፈላጊነት ማስረዳት ነበረበት። በደፈናው የኢትዮጵያ ቡድን ያለ ህክምና ባለሙያዎች ቶኪዮ እንዳለ አድርጎ መሳልና ” መንግስታችንና ሕዝባችን ይወቀው” ብሎ ከውድድሩ በፊት መጮህ “ጩኸቴን ቀሙኝ” ካልሆነ በቀር ሌላ ትርጉም የለውም። አደጋም አለው።

የኢትዮጵያ አትሌቶች እንደ ውድድራቸው ምረሃ ግብር በአራት ምድብ ተከፋፍለው ወደ ቶኪዮ ስለሚያመሩ፣ ይህም የሆነው ከከፍታ እንደመጡ ባላቸው ሄሞግሎቢን እንዲወዳደሩ ታስቦ መሆኑ ቅሬታ የሚቀርብበት ጉዳይ ባለመሆኑ ፌዴሬሽኑንን ምን እንዳስከፋው ግልጽ አይደለም። የሁሉም ተጓዦች የጉዞ ማረጋገጫ አክሪዲቴሽን በተመሳሳይ ቢሰጥ ተከፋፍለው የሚመጡትን አትሌቶች ማን ይዞ ይሄዳል? ለሚለውም መልስና መፍሄ የለውም። ባደረግነው ማጣራት በየምድቡ ከሚመጡት አትሌቶች ጋር የተመደቡ ሰዎች የጉዞ ፈቃዳቸውን እየወሰዱ በተያዘላቸው እቅድ መሰረት ወደ ቶኪዮ እንደሚሄዱ ነው።

ስለ አምስት ሺህ

በአምስት ሺህና በአስር ሺህ ሜትር ባልታወቀ ምክንያት ራሱን ከሆቴል ያገለለው ሃጎስ ገብረህይወት በተወዳዳሪ ሊስት ውስጥ መያዙን የፌዴሬሽኑ መግለጫ ያትታል። ባደረግነው ማጣራት ሃጎስ በየትኛውም የመሮጫ ርቀት ውስጥ አልተያዘም። ፍጹም ሃሰት ነው። መግለጫው ከኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር ያለን ልዩነትና አለመግባባት በቴክኒካል ጉዳዮች አዋዝቶ ውጤቱ እንደቀድሞው ባይሆን ” ከደሙ ነጻ ነኝ” የሚል ማመልከቻ ይመስላል።

ሞ ፋራህን አዳፍቶ ያሸነፈው ሙክታር እድሪስ ይህ እስከተጻፈ ድረስ ተወዳዳሪ የመሆኑ ጉዳይ እየተመከረበት ነው። የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የኦሊምፒክ አትሌቶችን ከተረጀበ በሁዋላ በራሱ የቴክኒክ ስታፍ ውሳኔ እንዲወስን በህግ ተቀምጦለታል።

ማሳረጊያ

የቶኪዮ ኦሊምፒክ መዳረሱን ተከትሎ በአትሌቲክስ ፌዴሬሽንና በኦሊምፒክ ኮሚቴ መካከል ገሃድ የወጣው ልዩነት ሚዲያዎች ከመርህ፣ ህግና አሰራር አንጻር ስለማያዩት ሕዝብ ተምታቶበታል። ይህ አሁን የወጣው መግለጫ በቀጥታ የሚያሳየው ” ዝም በሉና መንግስታችንና ሕዝብችን እያልን ሆዳችሁን እየበላን እንዝረፍ” አይነት ነው። ይህን መግለጫ ሲያዘጋጁ አንዱና ፊትለፊት ያሉት ተቀጥረው ፌዴሬሽኑን በጸሃፊነት የሚያገለግሉ፣ ከህግ ውጭ የዳርት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የሆኑ ሰው ናቸው። እኚህ ሰው በተሰበረ የህግ ሚዛን ላይ ቁጭ ማለታቸውን ዘንግተው ስለ ፍትህና ርትዕ መግለጫ ሲሰጡ ካሜራ ቀስሮ መቅረጽና ለቅሶውን ህዝብ ላይ መድፋት ሳይሆን ” እርስዎስ” ብሎ መሞገት አግባብ ነው።

በመግለጫው ከተነሱት ነጥቦች ውስጥ አብዛኞቹ የሁለቱን አካላት ልዩነት የሚያሳዩ ናቸው ይህ ለአገሪቱ ስፖርት መልካም አጋጣሚ ነው። ተሻርከው ከሚበሉ አንዲ አንዱን እየተቆጣጠር በልዩነት ቢኖሩ ችግሩ ምንም ነው። እንደውም ቸግሩን ያመጣው ከዚህ ቀደም የነበረው የፖለቲካ ማነቆ ሁለቱንም ድርጅቶች የቅፈደደ በመሆኑ በስም ይለያዩ እንጂ ደባሎች ነበሩ። አንዱ ሌላውን ” ለምን” ሊለው ቀርቶ ሳይጠራ ” አቤት” የሚባልበት ግንኙነት ነው የነበራቸው። ሁለቱም ጋር የነበሩት ባለጊዜዎቹ ስለነበሩ ምን ሲደረግ እንደነበር እናውቃለን። ዶላር የሚሸመትበትና ቤተሰብ ወደ አውሮፓ የሚጋዝባት ቤት ከጄ ወጣ ብለው ከዳር ሆነው እዪዪ የሚሉ አንዳሉም መዘንጋት አግባብ አይሆንም። በመሆኑም ይህን ልዩነት እንደ አሰራር አምኖ በመቀበል መቀጠሉ ይበጃል። ኦሊምፒክና አትሌቲክ ፌዴሬሽን ተቃቅፈው ከተኙ ነውና አደጋው ይህን ድንበርንና ሃላፊነትን አውቆ የመኖርን አሰራር እናበረታታ። ምክንያታዊ ያልሆነ ለቅሶ አናስተጋባ። ድግሱ የኦሊምፒክ ነውና ጨዋ እንግዳ መሆን ግድ ነው። መለመድም አለበት።


Exit mobile version