ETHIO12.COM

የአሸባሪው ጁንታ ግፍ በታዳጊዋ ሳራ አደም አደበት -ከአፋር ክልል ጦር ግንባር

ሳራ አደም ትባላለች፡፡ ትውልዷ አዲግራት ከተማ ነው፡፡ እድሜዋ 16 እንደሆነና ገና 10ኛ ክፍል እንዳልጨረሰች ገልፃለች፡፡ ከእናት እና አባቷ ቤት የወጣችው ስልጠና አለ ተብላ ነበር፡፡ ከ4 የቅርብ ጓደኞቿ ጋር ስልጠና ወደተባለበት የካቲት ከፍለ ጦር ውስጥ ታዳጊዋን ቀላቀሏት፡፡

በሰዓቱ በአንድ ሺ አለቃ ስር 60 ልጆች ነበርን፡፡ ከ60ዎቻችን ውስጥ መሳሪያ እኔን ጨምሮ ያልተሰጠን እንዳለ ሁሉ የያዙም ልጆች ነበሩ፡፡ አብዛኞቹ የኔ እኩዮች ናቸው፡፡ ከአዲግራት ከመጣነው ውስጥ የማውቃቸው 4ቱን ጓደኞቼን ነው፡፡ ከእነርሱ መካከል መካከል ሁለቱ በሌላ ግንባር ነው የተወሰዱት፡፡ ፌበን ገብሬ ከምትባለው ጓደኛዬ በአንድ ጦር ግንባር ነበርን፡፡ ሁለት ሳምንት ያህል በየካቲት ክፍለ ጦር እንድትቆይ ተደረግን ብላለች፡፡

ከሁለት ሳምንት ቆይታ በኋላ ምንም ወደማናውቀው አካባቢ ነበር ያመጡን፤ በኋላም አንድ ስፍራ አራገፉን፤ ከዚህ በኋላ ያለው አፋር ክልል ነው፡፡ ወደ ክልሉ ዘልቃችሁ በመግባት ትዋጋለችሁ ብለው ሰደዱን፡፡ ያመጡን ሰዎች ከኋላችን ቀሩ፤ ውጊያ ገጠምን በኋላ ግን ብዙም ሳንቆይ ተመታን፤ ጓደኛዬ ፌበን ገብሬ ወዲያው ህይወቷ አለፈ፡፡ ሌሎችም ሞተዋል፡፡

እኔ ግን እጄንና ዳሌ ላይ ነው በጥይት የተመታሁት፡፡ መንቀሳቀስ ከበደኝ፡፡ አብረውኝ የነበሩትን ከስፍራው እንዲያወጡኝ ስጠይቃቸው እጄን ብቻ አሰሩልኝና ሁሉም ጥለውኝ ወደ ኋላ ሸሽተው እሮጡ፡፡

ሲያዋጉኝ የነበሩ የምትላቸው ስሙን ግን የማታውቀው አንድ መሳሪያ የያዘ ሰውዮ አጠገቧ እንደነበረ ታስታውሳለች፡፡ ከዚህ አውጡኝ ብዬ ለመንኩት፤ ምንም ምላሽ ሳይሰጡኝ ጥለውኝ እሮጠው ሸሹ፡፡ ከዚያ ስፍራ ብዙ ደም ፈሰሰኝ፡፡ በኋላ አንድ መከላከያ ሰራዊት መጥቶ ደግፎኝ፤ ወጣና የሚጠጣም፤ ህክምናም እንዳገኝ አደረገኝ፡፡

ከተማረኩ በኋላ መከላከያ ሰራዊቱ ህክምና እየሰጠኝ ይገኛል፡፡ ለትግራይ እናቶች የምመክረው ልጆቻቸውን ጥቅም አልባ ለሆነው ጦርነት እንዳይሰጡ ነው፡፡ ከኢትዮጵያውያን ጋር ተጋጭተን በማንወጣውና ጥቅም በሌለው ጦርነት በየበረሀው እየቀረን፤ እየሞትን ነው፡፡ ይህ ጦርነት ቢቀርስ ስትል መልዕክት አስተላልፋለች፡፡

ገብረሚካኤል ሀፍቱ የተባለውም ታዳጊ ልክ እንደ ሳራ ሁሉ በጁንታው የውሸት ፕሮፖጋንዳ ተታሎ ነበር ከማይጨው ወደ ጦር ግንባር የከተመው፡፡ ገብረሚካኤል እንደ ሳራ የካቲት ክፍለ ጦር የመግባት እድል አላገኘም፡፡ ከማይጨው ከእናትና አባቱ ቤት ካስወጡት በኋላ በየ ተራራውና በየ ገደሉ ጁንታው ይዟቸው ይጓዝ እንደነበረ ተናግሯል፡፡

በየገደላ ገደሉ ለምን እንሄዳለን? ብለን ስንጠይቃቸው ስልጠና እኮ እየሰለጠናችሁ ነው ይሉን ነበር፡፡ ውጊያ ሊያስገቡን እንደሆነ ያወቅነው፤ አፋር ክልል ላይ ከደረስን በኋላ አሁን ትዋጋላችሁ ሲሉን ነው፡፡ እኛም ምርጫ አልነበረንም ወደ ጦርነት ገባን፤ እነርሱ ግን ወደ ኋላ ተመለሱ ይላል፡፡

በኋላም በጦርነቱ መቁሰሉንና በሀገር መከላከያ ሰራዊት መማረኩን ተናግሯል፡፡ በቂ ህክምና ማግኘቱንም ገልጧል፡፡

ሁለቱም ባለታሪኮቻችን ክፉኛ ስለቆሰሉ በህክምና ላይ ናቸው፡፡

(በደረሰ አማረ ከጦር ግንባር) walta

Exit mobile version