Site icon ETHIO12.COM

“እንደ ህውሃት እድል የተሰጠው በዚህ ምድር የለም” ያሉት አቶ ግዛቸው

የህልውና ትግሉ ከአሸባሪው ጋር ብቻ ሳይሆን ከጀርባ ካሉ ሃይሎች ጭምር ነው

የህልውና ትግሉ ከአሸባሪው ቡድን ጋር ብቻ ሳይሆን ከጀርባ ካሉ የውስጥና የውጭ ሃይሎች ጭምር መሆኑን ህዝቡ ሊያውቅ ይገባል ሲል የአማራ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ።

የአማራ ክልል አመራርና ከሁሉም ህብረተሰብ የተውጣጡ አካላት የተሳተፉበት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሚመክር ጉባኤ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ጉባኤውን አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት ፤ጉባኤው በህልውና ትግሉ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትና በቀጣይ ስራዎች ላይ ያተኮረ ነው።

ዋና ዓላማው የህልውና ትግሉ የአማራን ህዝብ ከጥፋት ለመታደግ ነው ብለዋል።

የህልውና ትግሉ ከአሸባሪው ቡድን ጋር ብቻ ሳይሆን ከጀርባ ካሉ የውስጥና የውጭ ሃይሎች ጭምር መሆኑን ህዝቡ ሊያውቅ ይገባል ብለዋል።

አሸባሪው ህውሃት ከምስረታው ጀምሮ በሀገሪቱ ቀውስ እየፈጠረ የእሴት መዛባት፣ የቁሳዊና መንፈሳዊ ሃብቶቻችን ላይ ጉዳት በማስከተል ታሪክ ይቅር የማይለው ግፍና በደል ፈጽሟል።

ይባስ ብሎም ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በመከላከያ ሰራዊታችን ላይ ከጀርባ ጥቃት በመፈጸምና በክልላችን ጎንደር አካባቢ ቅራቅር ተብሎ በሚጠራው ቦታ ላይ ወረራ በመፈጸም አረጋገጦልናል ብለዋል።

አሸባሪው ቡድን በህግ ማስከበር ዘመቻው የወገን ጦርን ጠንካራ ምት መቋቋም ባለመቻሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተፈጠረበት ዋሻ ውስጥ እንዲገባ መገደዱን አቶ ግዛቸው በመግለጫቸው አውስተዋል።

መንግስት የሰጠውን የተናጠል ተኩስ ውሳኔ ወደ ጎን በመተው በአማራና አፋር ክልሎች ላይ ወረራ በመፈጸም ላይ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

“እንደ ህውሃት እድል የተሰጠው በዚህ ምድር የለም” ያሉት አቶ ግዛቸው ፤ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የተሰጡትን መልካም እድሎች መጠቀም ያልቻለ ለኢትዮጵያ ነቀርሳ ሆኖ የቀጠለ አሸባሪ ቡድን መሆኑን አስረድተዋል።

አሸባሪው ቡድን በሚያካሂደው ወረራ ህዝብን በመግደል፣ ንብረት በመዝረፍ እና ሴቶችን በመድፈር ግፍ እየፈጸመ በመሆኑ የህልውና ትግሉ ፍትሃዊ እንደሚያደርገው በጉባኤው መግባባት እንደተደረሰ አስታውቀዋል።

እስካሁን በተካሄደው ጦርነት የአሸባሪው ህዋሃት ሃይል በገፍ እያለቀ አሁን ላይ አርሶ አደሩንና የመንግስት ሰራተኛውን በግድ እያሰለፈ መሆኑ ተደርሶበታል ብለዋል።

አቶ ግዛቸው በመግለጫቸው እንዳመለከቱት፤ የትግራይ እናቶች የህውሃት ጁንታ ልጆቻቸውን፣ ባሎቻቸውንና ወንድሞቻቸውን በመላክ ትርጉም በሌለው ጦርነት እየላከ ያስጨፈጨፋቸው መሆኑን በመገንዘብ አቁም ሊሉት ይገባል።

የአማራ ክልል ህዝብም አቅም ያለው ወደ ግንባር በመሰለፍ፣ አቅም የሌለው በስንቅና ትጥቅ አቅርቦት የህልውና ትግሉን ለመደገፍ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ማስቀጠል አለበት።

በተለይም ወጣቱ ወደ መከላከያ፣ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ በመግባት በሚፈለገው መስክ መሰልጠንና ወገኑን ከማንኛውም አደጋ ለመጠበቅ ዝግጁ መሆን እንዳለበት ተመልክቷል።

በጉባኤው የተሳተፉ አካላትም ወጣቱ ወደ መከላከያ ሰራዊት በመቀላቀል ክልሉ የሚኖረውን የተዋጽኦ ሚዛን ለመጠበቅ እንዲነሳሳም ጥሪ አቅርበዋል።

ለዚህም በጉባኤው የተሳተፉም ሆነ ያልተሳተፉ የአማራ ልሂቃን ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ወደየአካባቢያቸው በመሄድ ለህብረተሰቡ የህልውና ትግሉን ዓላማ በማስረዳትና ወጣቱ ትግሉን እንዲቀላቀል በማድረግ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርባል።

በተጨማሪም በየአካባቢው ያሉ ችግሮችን በመፍታትና ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ላይ ያሉ የአስተዳደር አካላትን በማማከር ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጉባኤው ማሳሰቡን አስታውቀዋል።

የማህበረሰብ አንቂዎች በግንባር አካባቢዎች በተለይም በምስል የተደገፉ መረጃዎችን በመልቀቅ የጠላት ተባባሪ ከመሆን እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

እስከ ነገ በሚቀጥለው ጉባኤው የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምሁራን፣ ባለሃብቶች፣ የማህበረሰብ አንቂዎችና ወጣቶች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተመልክቷል።

ሐምሌ 24/2013(ኢዜአ)

Exit mobile version