«ወጣቶች መከላከያ ሰራዊትን መቀላቀላቸው ታሪክ ለክብር እንዳጫቸው ሊቆጥሩት ይገባል።» አቶ ክርስቲያን

ወጣቶች የአገር አንድነትና የሕዝብ ኅልውና የመጨረሻ ደጀን ወደ ሆነው የአገር መከላከያ ሰራዊት መቀላቀላቸው ታሪክ ለክብር እንዳጫቸው ሊቆጥሩት ይገባል ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ/አብን/ የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ክርስቲያን ታደለ ጥሪ አቀረቡ፡፡

አቶ ክርስቲያን ታደለ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ከውስጥ ባንዳዎችና ከውጭ ኃይሎች ጋር የሞት ሽረት ትግል እያደረገች በመሆኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ የልጆቿን አለሁ ባይነት የምትፈልግበት ወቅት ላይ ትገኛለች፡ ፡ከዚህ አኳያ ወጣቶች የአገር አንድነትና የሕዝብ ኅልውና የመጨረሻ ደጀን ወደ ሆነው የአገር መከላከያ ሰራዊት ታሪክ ለክብር እንዳጫቸው ሊቆጥሩት ይገባል ብለዋል።

ውትድርና ጥይት መተኮስ ብቻ ሳይሆን በርካታ የቴክኖሎጂና የምርምር ሙያ መስኮችን አካቶ የያዘ የሙያ ዘርፍ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ክርስቲያን፤ ወጣቶች የአገር መከላከያ ሰራዊትን ሲቀላቀሉ አገርን የማስጠበቅ የዜግነት ግዴታቸውን ከመወጣት ባለፈ ኅልሞቻቸውንም እውን የሚያደርጉበት የተሻለው አማራጭ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል ብለዋል፡፡

ያደጉትም ሆኑ በማደግ ላይ ያሉ አገራት ታፍረውና ተከብረው የሚኖሩት በመሰረቷቸው ጠንካራ ተቋማት በተለይም በመከላከያ ሰራዊታቸው ጥንካሬ ነው ያሉት አቶ ክርስቲያን፤ አባቶቻችን በመስዋዕትነት ያስረከቡንን ኢትዮጵያ ወደፊትም ታፍራና ተከብራ እንድትኖር የፀጥታ ኃይሉ የሰለጠነ፣ የተደራጄና ዘመናዊ ሜካናይዝድ የጦር ስልቶችን የተካነ ሆኖ የአገሩን ኅልውና የሚያስጠብቅ ማድረግ ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ ክርስቲያን ገለፃ፤ እኛ የአባቶቻችን ልጆች ነን ብለን በኩራት እንደምንናገረው ልጆቻችንም በተራቸው የአባቶቻችን ልጆች ነን የሚሉበትን ድል ማስመዝገብ ይጠበቅብናል፡፡ ማንም የውጭ ወራሪ ኃይልና የውስጥ ባንዳዎች ኅልውናዋን የማይፈታተኗት ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ወጣቶች ወደ አገር መካላከያ ሰራዊት በመቀላቀል የአገራቸው አለኝታ መሆናቸውን ማስመስከር እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በአደባባይ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚከፈለውን ሁሉ እከፍላሁ እስከ ሲዖልም እወርዳለሁ ብሎ ሲዝት መቆየቱን አስታውሰው፤ ዛቻውን በተግባር ተርጉሞ የአገር መከላከያ ሰራዊትን ለማፍረስ፣ ንጹኃን ዜጎች ላይ ጅምላ ጭፍጨፋዎችን በመፈጸምና ተቋማትን በማፍረስ አገረ መንግሥቱ ልፍስፍስና የውጭ ኃይሎች ገባሪና አፋሽ አጎንባሽ እንዲሆን ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አሸባሪው ቡድን ፍላጎቱን ለማሳካትም የሺህ ዓመታት የሥልጣኔ ባለቤት የሆነችውን ኢትዮጵያ ወደ ትናንሽ የመንደር መንግሥታት ለመቀየር እየታተረ ይገኛል ያሉት አቶ ክርስቲያን፤ አባቶቻችን መስዋዕትነት ከፍለው ያስረከቡንን አገር መከፈል የሚገባውን ሁሉ ዋጋ በመክፈል አንድነቷና ኅልውናዋ የተረጋገጠ አገር ለትውልድ ለማስረከብ መረባረብ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ እየተደረገ ያለውን የኅልውና ትግል ብዙዎች ከአሸባሪው ሕወሓት ቡድን ጋር ብቻ የሚደረግ ተጋድሎ አድርጎ የመመልከት ሁኔታ መኖሩን የተናገሩት አቶ ክርስቲያን ታደለ፤ ጭንብሉ ሲገፈፍ ግን ትግሉ የሚደረገው በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ኃብቶች ከሚቀኑ፣ ይህን ኃብቷን እንዳትጠቀም ከሚፈልጉና የራሳቸውን ጥቅም ብቻ ከሚያስከብሩ ኃይሎች ጋር ጭምር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የጥፋት ኃይሉና ባለፉት 27 ዓመታት ያዝረከረካቸውን የጥላቻ፣ የመለያየት፣ የመከፋፈል የሐሰት ተረኮች፣ ሕጎችና አሠራሮች ከነሰንኮፉ ተነቅለው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መሸኘት ይኖርብናል ብለዋል።

ፋንታነሽ ክንዴ – አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 9 ቀን 2014 ዓ.ም

Leave a Reply