Site icon ETHIO12.COM

የህወሀት ሞግዚቶች ከያሉበት ተነቃንቀዋል።

የአፋር ወረዳዎች በህወሀት ታጣቂዎች ታምሶ ከ70ሺህ በላይ ወገኖች ሲፈናቀሉ ሞግዚቶቹ አላዩም። አልሰሙም። በአማራ ክልል አከባቢዎች ህዝብ ላይ ጦርነት ተከፍቶ ሰላም ሲደፈረስ ምዕራብውያኑ መንግስታት ዝምታቸው ያስደነግጣል። ለትግራይ ህዝብ የእርዳታ እህል እንዳይደርስ ሲደረግ ትንፋሻቸው እንኳን እንዳይሰማ መሆናቸው በጽኑ ያስፈራል። ከምንም በላይ ህጻናት ከእናታቸው እቅፍ እየተነጠቁ ለጦርነት ሲማገዱ የእነቢቢሲ ልሳን መዘጋቱ ስሜትን በጥልቅ ይጎዳል።

በእርግጥም ከአስራ አምስት ቀናት በላይ እነአሜሪካንን የበላ ጅብ አልጮህ ብሎ መክረሙ በብርቱ ያሳስብ ነበር። የእነሮይተርስና ኒውዮርክ ታይምስ የመሳሰሉ ሚዲያዎች አፍ መዘጋቱ ግርምትን ፈጥሮ ቆይቶም ነበር። የእነአምንስቲ ኢንተርናሽናል ብጣሽ መገለጫ እንኳን ናፍቆን ነበር የሰነበትነው። ህወሓት አዲስ አበባን እቆጣጠራለሁ ብሎ የገባላቸው ቃል እስኪፈጸም ጆሮአቸውን ደፍነው፣ አይናቸውን ሸፍነው፣ አንደበታቸውን ዘግተው ለመቆየት መወሰናቸው ለምን እንደሆነ አልጠፋንም። ካለፉት ሶስት ቀናት ወዲህ ግን ጆሮአቸው ተከፍቷል። አይናቸው ተገልጧል። አንደበታቸውም ተላቋል። ምክንያት አላቸው።

ዝምታቸው የተሰበረው እንደስለት ልጅ የሚንከባከቡት ህወሓት አዲስ አበባን እንደቋመጠ፣ ከቆቦ መሻገር አቅቶት የኋሊዮሽ በመፈርጠጡ ነው። አይናቸው የተገለጠው የጅቡቲን መስመር እዘጋለሁ ብሎ የገባላቸውን ቃልኪዳን መፈጸም ተስኖት በወረራ በያዛቸው የአፋር አከባቢዎች ታጣቂዎቹ በሺዎች የሚቆጠሩ ለወሬ ነጋሪ እንኳን እንዳይተርፉ ሆነው በመደምሰሳቸው ነው። በእርግጥ ሞግዚቶቹ ህወሀት አዲስ አበባ ይደርሳል ብለው ጠብቀዋል። ለአዲስ አበባ ባይበቃ እንኳን የኢትዮጵያን መንግስት ለድርድር እጁን እንዲሰጥ የሚያደርግ ወታደራዊ ድል እንደሚቀዳጅ እርግጠኞች ነበሩ። ከዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ ባሻገር በእርዳታ ስም መሳሪያ እስከማስገባት ሰፊ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ሰንብተዋል።

ያሳደጉት ልጅ፣ የለፉበትና ተስፋ ያደረጉበት የስለት ልጃቸው እንደጠበቁት ሳይሆን በአጭር ቀረባቸው። የኢትዮጵያ ልጆች ከአራቱም ማዕዘናት ተጠራርተው ከጦር ግንባር ከተቱ። የደጀኑ ህዝብ ተነቃነቀ። ኢትዮጵያ ወይም ሞት፣ ከየአቅጣጫው ተስተጋባ። ይህ የኢትዮጵያ ህዝብ ምላሽ ለህወሀት ቡድን አስደንጋጭ መርዶ፣ ለአሳዳሪዎቹ ያልተጠበቀ ዱብ እዳ ሆነ። በዘር፣ በጎሳ፣ በሃይማኖት የተሸነሸነ፣ በጎሪጥ እንዲተያይ በመሃሉ ግድግዳ የሰነቀርንበት ህዝብ እንዴት አንድ ሆኖ ይነሳል? የኢትዮጵያ አምላክ፣ የእናቶች ልመና፣ የሃይማኖት አባቶች ጸሎት፣ ምላሽ ነበረው። ኢትዮጵያ ታጎነብስ ይሆናል እንጂ አትሰበርም። በመጨረሻም ህዝብ መልስ ሰጠ። የህወሀትን የጥፋት ግስጋሴ በእንጭጩ ቀጨው። ረጅም መንገድ አቅዶ የተነሳውን ሃይል በአጭሩ አስቀረው። ይሄኔ ነው የተዘጋው አንደበትና የተደፈነው ጆሮ የተከፈተው ፣ የተሸበበው ዓይንም የተገለጠው።

ህውሀት ሁለተኛውን ሞት እንዳይጨልጥ ሞግዚቶቹ ከለንደን እስከ ዋሽንግተን ዲሲ ተነቃንቀዋል። ከብራስልስ- ኒውዮርክ በአንድ ቋንቋ መናገር ጀምረዋል። የስለት ልጃችን ተነካብን ብለው በጥፍራቸው ቆመዋል። ለቀናት የተዘጋው የእነቢቢሲ ማይክራፎን አስቀያሚ ጩኸቱን እየለቀቀው ነው። እነኒውዮርክ ታይምስ ብዕር ካንቀላፋበት ነቅቶ ሀሰተኛ መረጃዎችን ይቸከችክ ጀምሯል። እውነት ህወሀትን ከሁለተኛ ሞት ታስጥሉት ይሆን?

የኢትዮጵያ መንግስት ምርጫ የለውም። የትዕግስትን ልክ ለዓለም በሚገባ አሳይቷል። ለሰላም ያለውን እውነተኛ አቋም በተግባር አረጋግጧል። ለማያባራው የምዕራባውያኑ ጥያቄ በሚችለው አቅም ምላሽ ሊሰጥ ብዙ ርቀት ተጉዟል። ከእንግዲህ ቀይ መስመሩን ማለፍ አይችልም። ኢትዮጵያ እንደዩጎዝላቪያ እንድትሸነሸን በነጮቹን ድግስ ተሰናድቶላታል። ሰሞኑን የተሰራጨው ሰነድ እውነተኛ ስለመሆኑ ማረጋገጫ ባይገኝም፣ ምዕራባውያን ለኢትዮጵያ እየሳሉ ያሉት ካራ እንዳለ ለመረዳት ፍንጭ የሚሰጥ ነው። ሰነዱ እነአሜሪካና አውሮፓ ኢትዮጵያን በሚዲያ ጦርነት በማዳከም የዩጎዝላቪያ ዓይነት እጣ ፈንታ እንዲገጥማት እየዶለቱ መሆኑን የሚያጋልጥ ነው። እስከዚያ ባይደርሱ እንኳን ህወሀትን በጀርባ አዝለው፣ አዲስ አበባ በማስጠጋት ከሌሎች ብሄርተኛ ሃይሎች ጋር በማጣመር የመዋጮ መንግስት እንዲመሰረትና ለእነሱ ቀጥ ለጥ ብሎ የሚታዘዝ አሻንጉሊት አገዛዝ ከመተከል እንደማይመለሱ አሁን ላይ እርግጥ ሆኗል።

እናም የኢትዮጵያ መንግስት ወደፊት እንጂ ወደኋላ መመልከት የለበትም። የህወሀትን ፍጻሜ የሚያረጋግጠውን ወታደራዊ ኦፕሬሽን በተጠናከረ ሁኔታ ማካሄድ ምርጫ የሌለው ውሳኔ ነው። ነገሮችን የሚወስኑት፣ የምዕራብያውያንን ሩጫ የሚያስቆመው የጦር ሜዳው ድል ነው። ካሸነፍክ ትከበራለህ። ህወሀትን ከመቃብር አስገብቶ ዳግም እንዳይነሳ ማድረግ የኢትዮጵያ መንግስት ብቸኛ የጊዜው እርምጃ ነው። ያኔ፣ ያሸነፍክ ጊዜ እነሱም ይቀበሉሃል። ጉልበተኛ መሆንህን ካረጋገጡ አብረው ለመስራት ደጅህን ይጠናሉ። ለክብርህ የምትሞት መሆንህን ከተረዱ በርህን አንኳክተው ይጠሩሃል። ይኸው ነው። ህዝብ ከጎንህ ቆሟል። ለሀገሩ ክብር ህይወቱን ሊገብር እየተመመ ነው። ከዚህ በላይ ጉልበት ምድር ላይ የለም። ይህን የህዝብ ሃይል ይዘህ የማታሸንፍበት ምንም ምድራዊ ምክንያት አይኖርም።

Mesay Mekonnen

Exit mobile version