ETHIO12.COM

በ25 ሚሊዮን ብር ጉቦና የተጭበረበረ ደብዳቤ በደህንነት ስም በማዘጋጀት በፖሊስ የተያዘ ፌሮ ለማዘረፍ የተመሳጠሩ ተያዙ

ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የተፃፈ ደብዳቤ በማስመሰልና ጉቦ ለመስጠት የሚውል ገንዘብ በቼክ በማዘጋጀት በፖሊስ ቁጥጥር ስር የነበረ ፌሮ ብረት ክምችት ለማስለቀቅ የሞከሩ ተጠርጣሪዎችን መያዙን የፌዴራል ፖሊስ ገለጸ። ባሕር ዳር:ሐምሌ 25/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ሐሰተኛ ማስረጃ በማቅረብና ጉቦ በመስጠት በፖሊስ ቁጥጥር ስር የነበረ ፌሮ ብረት ክምችት ለማስለቀቅ የሞከሩ ተጠርጣሪዎችን መያዙን የፌዴራል ፖሊስ ገልጿል።

በተጠርጣሪዎቹ ለማስለቀቅ የተሞከረው በቦሌ ክፍለ ከተማ ቡልቡላ አካባቢ በአንድ መጋዝን ውስጥ በሕገ-ወጥ መንገድ ተከማችቶ በፌዴራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለና በምርመራ ሂደት ላይ ያለ የፌሮ ብረት ነው።

ተጠርጣሪዎቹ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የተፃፈ በማስመሰል “ሕጋዊነቱ ስለተረጋገጠ በቦታው የሚገኘው የፖሊስ ጥበቃ ተነስቶላቸው ወደ ፈለጉበት ማንቀሳቀስ እንዲችሉ ፈቅደናል” የሚል ሐሰተኛ ደብዳቤ አዘጋጅተው በመያዝና ጉቦ ለመስጠት የሚውል ገንዘብ በቼክ አዘጋጅተው ብረቱን በአምስት ተሽከርካሪ ጭነው ሊወጡ ሲሉ ሦስት ተጠርጣሪዎች በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ በአዲስ አበባ ፖሊስና በፋይናንስ ኢንተለጀንስ ጠንካራ ክትትል ሊያዙ ችለዋል።

ባለፈው ሳምንት የተያዘው ብረት ባለቤት ነኝ ከሚል ተክላይ ከሚባልና አሜሪካን ሀገር ነዋሪ ነው ተብሎ ከሚነገረው ግለሰብ ጋር ሦስቱ ተጠርጣሪዎች የጥቅም ትስስር በመፍጠር በኤግዚቢትነት ተይዞ በምርመራ ሂደት ላይ ያለውን የፌሮ ብረት በጥበቃ ላይ ላሉት የፖሊስ አባላትና አመራሮች 500 ሺህ ብር ጉቦ ለመስጠት በአቢሲኒያ ባንክ አዲስ አካውንት ከፈተው ያስገቡ መሆኑም ነው የተገለፀው።

በተመሳሳይ ለሌሎች የጸጥታ አካላት 400 ሺህ ብር በባንክ እና የ25 ሚሊዮን ብር ቼክ አዘጋጅተው ብረቱ እንደሚለቀቅ ከተስማሙ በኋላ የፖሊስና የጸጥታ አካላቱ ጉዳዩን ሚስጥራዊ በሆነ መንገድ ለበላይ ኀላፊ በማሳወቅ ሂደቱ እንዲቀጥል በመደረጉ፤ ብረቱን በአራት ሲኖትራክ እና በአንድ ክሬን ለመጫን ተስማምተው በሁለት ሲኖትራክ እንደተጫነ ባንክ የገባው ብር እና ቼኩ፣ እንዲሁም የተፃፈው ሐሰተኛ ደብዳቤ እና ሦስቱ ተጣርጣሪዎች ከተዘጋጁት ተሽከርካሪዎች ጋር ከነአሽከርካሪዎቻቸው በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል።

ተጠርጣሪዎቹ ለጸጥታ አካላት በርካታ ገንዘብ ሰጥተው በማማለል ለሕገ-ወጥ ድርጊት ፖሊስ ተባባሪ እንዲሆን ያደረጉትን ጥረት በማክሸፍና ለሕግና ለመንግሥት ፍፁም ታማኝ በመሆን ወንጀሉ ለሕግ እንዲቀርብ በማድረግ የአሸባሪው ጁንታን እኩይ ሴራ ማክሸፍ መቻላቸውን ፌዴራል ፖሊስ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል። ኅብረተሰቡ አሁንም በዚህ አይነት የወንጀል ተግባር ላይ ለመሳተፍ የሚጥሩ የአሸባሪው ጁንታና ከጁንታው ጋር ግንኙነት ፈጥረው ሀገሪቱ ላይ የሚያሴሩ ባንዳ ግለሰቦችን እየጠቆመ አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርግ ፌዴራል ፖሊስ ጥሪውን አቅርቧል።

ምንጭ አዲስ አበባ ዜና አገልግሎት



Exit mobile version