Site icon ETHIO12.COM

“ኢትዮጵያ የውጭ ኃይል ጣልቃ እንዲገባባት የማትፈቅድ ሀገር ናት” የቀድሞ የአሜሪካ የኮንግረስ እጩ አቶ ቴዎድሮስ ዓለማየሁ

አቶ ቴዎድሮስ ዓለማየሁ የመጀመሪያው ትውልደ ኢትዮጵያዊ የአሜሪካ ኮንግረስ እጩ ናቸው፡፡ የአሜሪካ ዶክተሮች ለአፍሪካ ማኅበር መስራችና ፕሬዚዳንት ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡

ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በመተባበር ባደረጉት እልህ አስጨራሽ ትግል በውስጥም በውጭም ጫና ለማሳረፍ ሲደረጉ የነበሩ ሩጫዎችን ማርገብ እንደተቻለም ጠቁመዋል።

አቶ ቴዎድሮስ እንደገለጹት፤ ዲያስፖራው ቀደም ባሉት ጊዜያት በተሳሳቱ መረጃዎች በሀገር ላይ ጫናዎችን ለመፍጠር የተደረጉ ጥረቶችን ለመቀልበስ በጋራ ተንቀሳቅሷል፡፡ በዚህም ውጤት መገኘቱን ጠቅሰው፤ጥረቱን በተሻለ ቅንጅትና ቁርጠኝነት አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ነው ያሉት።

አሜሪካን የሚያስተዳድሩ መንግሥታት በሌሎች ሀገራት ላይ ጣልቃ ሲገቡ ማየት የተለመደ ተግባር እንደሆነ ያመለከቱት አቶ ቴዎድሮስ፤ ሊቢያ፣ ግብፅና ሶማሊያን በማሳያነት አንስተዋል። ለዚህም የደኅንነት ስጋቶችንና ሰብዓዊ እርዳታዎችን በምክንያትነት እንደሚያነሱ አስታውቀዋል፡፡

አሁን ያለው የአሜሪካ መንግሥት አስተዳደርም እየሄደበት ያለው መንገድ በሌሎች ሀገራት ላይ ሲከተለው የነበረ ነው ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፣ ይህንኑ በኢትዮጵያ ላይ ለመድገም እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አመልክተዋል፡፡“ይህን ተግባሩን በኢትዮጵያ ላይ ለመፈፀም መንደርደሩ የሚያሳዝን ነው፣ የባይደን አስተዳደር ወደ ስልጣን ከመምጣቱ አስቀድሞ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳረፍ እንደሚፈልግ የሚያሳዩ ፍንጮች ነበሩ” ብለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ እንደማሳያ ማኅበራዊ ሚዲያውን በተለይ ደግሞ ትዊተር ላይ ኢትዮጵያን የተቃረኑ መረጃዎች ሲለቀቁ እንደነበር ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የውጭ ኃይል እንዲገባባት የማትፈልግና የማትፈቅድ ሀገር ናት ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፣ ይህን ባለመረዳት የተሳሳተ መረጃ ማሰራጨት መጀመራቸውን ገልጸዋል።

ቀደም ባሉት ዓመታትም የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት ያሳይ በነበረው አቋም ጥያቄ ስለነበረኝ በተለያዩ ጊዜያት ድምጼን አሰምቻለሁ ብለዋል፡፡

በተለይ የአሜሪካ መንግሥት የወቅቱ አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳረፍ ውሳኔ ከማርቀቁ አስቀድሞ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን ሳያወያይ እና በጉዳዩ ላይ ጥልቅ መረጃ ሳይኖረው በችኮላ ውሳኔ ለማሳለፍ መወሰኑ እንዳሳዘናቸው አመልክተዋል፡፡

በተለይ በኮንግረስ አባሏ ኬራን ባስ አማካኝነት የተረቀቀው ሪዞሉሺን 445 የተሰኘው ውሳኔ በጥልቅ ያልታየና ውስጡ ያልተፈተሸ የውሳኔ ረቂቅ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳረፍ የታቀደው ረቂቅ ውሳኔ መፍትሔ አመላካች እንዳልሆነ ያስታወቁት አቶ ቴዎድሮስ፣ የውሳኔ ሐሳብም ከአሜሪካ ኮንግረስ የማይጠበቅ ተግባር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ይህ ውሳኔ “ባሳለፍነው ሳምንት ለሴኔቱ መቅረብ የነበረበት ጉዳይ ቢሆንም ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ባደረጉት ርብርብ አሁን ጉዳዩ እንዲቆም ሆኗል፣ ኮንግረሱም ዳግም እንደሚያጤነው ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉ ገልጸዋል።

የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ጉዳይ የሚይዘው አቋም እውቀትና ሀብት እንዳለው ሀገር ሚዛናዊ መሆን ይጠበቅበታል ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፤ ለዚህም በግላቸው ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡“ይህን የማድረግም ኃላፊነት አለብኝ፤ በማለት ተሳስተው የኢኮኖሚም ኾነ ሌሎች እቀባዎች ቢያደርጉ” ሕዝብ ላይ ጉዳት ስለሚያስከትል አስቀድሞ ማሳወቅ ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በሀገሪቱ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ አነስተኛ መሆኑን የጠቀሱት የቀድሞው የኮንግረስ እጩ፤ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር በየትኛውም የሀገሪቱ የፖለቲካ መዋቅር ውስጥ መሳተፍ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡ ኢፕድ እንደዘገበው፡፡

Exit mobile version