Site icon ETHIO12.COM

ያልተደነቀው መሪ


ናይሮቢ ሎ መንዝሊ” የተባለ ድረገጽ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የለውጥ ጉዟቸውን የተመለከተ ሰፊ ዘገባ ይዞ ወጥቷል።

የምስራቅ አፍሪካ ሥትራቴጂክ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር እና የሳውዝሊንክ አማካሪ የሆነው አብዲዋህብ ሸኪ አብዲሰመድ የተባለው ጸሀፊ ባቀረበው ጽሁፍ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በልኩ ያልተደነቁት ጀግና መሪ ሲል ገልጿቸዋል።

ጸሀፊው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዴት በትረ ስልጣኑን ተረክበው ለውጡን እንደጀመሩ አብራርቶ ጽፏል።

ከለውጡ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሺዎች የሚቆጠሩ የፓለቲካ እስረኞችን እንዳስፈቱ፣ የሚዲያ ነጻነትን እንዳቀዳጁ፣ ከኤርትራ ጋር የነበረውን ጸብ እንደቋጩና ሰላም እንዳሠፈኑ በዚህም የኖቤል ሽልማት እንዳሸነፉ ገልጿል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ስኬት ደስታ የራቃቸውና አገሪቷን ለበርካታ አመታት በበላይነት ያስተዳደሯት ህወሓቶች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ሰላም መንሳት መጀመራቸውን የገለጸው ጸሀፊው፤ በዚህም የኢኮኖሚ አሻጥር በመስራት ቀውስ ለመፍጠር መንቀሳቀሣቸውን አብራርቷል።

በተለይም አገሪቷን በ30 ቢሊዮን ዶላር እዳ ውስጥ መጣላቸው ሳያንስ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በውጭ ምንዛሬ እንዲሁም ወርቅ ጭምር በማሸሽ ለግል ጥቅማቸው እና አሁን ላይ ለእነሡ ለሚጮሁላቸው አካላት (ወትዋች ድርጅቶች) መግዣ አውለውታል ነው ያለው።

ይህ ያልበቃቸው ህወሓቶች ተላላኪ መንግሥት እንዲኖር ከሚፈልጉ ምዕራባዊያን አገራት ጋር በመመሳጠር ህጋዊውን የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስት ለማስወገድ እየሠሩ ነው ሲልም አብራርቷል።

እነዚህ አካላት በሚያደርጉት የተቀናጀ ረፍት የለሽ ሁከት ጠቅላይ ሚኒስትሩን በአገር ውስጥ ጉዳዮች ላይ ጫና በመፍጠር ህወሓቶች በሀሠት ፕሮፓጋንዳ አለምአቀፉን መድረክ መቆጣጠርና በጥፋት መንገዳቸው መቀጠል ችለዋል ነው ያለው ጸሀፊው።

ህወሓት በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚፈጠሩ የብሄር ግጭቶች ሁሉ ዋናው ተጠያቂ እንደሆነ የአብዲ ኢሌን ሴራን በማስታወስ ጭምር ያብራራው ይኸው ጸሀፊ፤ በተለይም በቅርቡ በአፋር እና በሶማሌ መካከል ለተፈጠረው ግጭት ህወሓት እጁ አለበት ነው ያለው።

አለም አቀፉ ማህበረሰብ ህወሓት ሲሰራቸው የኖረውን ወንጅሎች በሙሉ ለአመታት ችላ ብሎ ቆይቶ አሁን ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ መንግሥት ላይ ጫና ማሳደሩ ፍትሃዊነት የጎደለው ነው ብሏል።

ህወሓትን ወደሥልጣን መልሦ ለማምጣት የሚደረገው ጥረትም ትክክለኛ መፍትሄ አይደለም ነው ያለው ጸሀፊው። Via – EPA

Exit mobile version