Site icon ETHIO12.COM

ወደ አማራ ክልል የገባውን አሸባሪውን ህወሃት ለመደምሰስ ዝግጅት ተጠናቋል

ወደ አማራ ክልል የገባውን የአሸባሪው ህወሃት ታጣቂ በያለበት ለመደምሰስ የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁን የአማራ ክልል የህዝብ ሰላምና ደህንነት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮ ሃላፊው ዶክተር ሰማ ጥሩነህ ዛሬ ማምሻውን እንደገለጹት ለህልውና ትግሉ መላ የክልሉ ህዝብ በቁርጠኝነት ሊሰለፍ ይገባል።

ጠላት ኢትዮጵያን ለማፈራረስና የአማራን ህዝብ አንገት ለማስደፋት ከህጻናት እስከ መነኮሳት ወደ ግንባር በመላክ እንዲጨፈጨፉ በማድረግ ኢ-ሞራላዊ ድርጊት እየፈጸመ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በአማራና በአፋር ክልሎች ላይ ወረራ በመፈጸም በትግራይ ልጆች እልቂት አገር በማፈራረስ የራሱን ጥቅም ለማስጠበቅ አልሞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ተናግረዋል።

መንግስት የሰጠውን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም “በክልላችን መጠነ ሰፊ ወረራ በማድረግ ንጹሃንን በመግደል፣ ንብረት በመዝረፍና ሴቶችን በመድፈር አጸያፊ ድርጊት ፈጽሟል” ነው ያሉት።

ለዚህም ነው “ከአማራ ጋር ሂሳብ እናወራርዳለንና ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ሲኦልም ቢሆን እንገባለን” እያሉ የሚደነፉት ያሉት ዶክተር ሰማ “ወደ ክልላችን የመጣው የጠላት ታጣቂ በጸጥታ ሃይላችን እየተደመሰሰ ይገኛል” ብለዋል።

“የክልላችን ልዩ ሃይል፣ ሚሊሻና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎችም በየጊዜው ከላይ ከላዩ እየጨመረ የሚመጣውን ጠላት አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት ጀግንነታቸውን እያስመሰከሩ ይገኛሉ” ብለዋል።

የክልሉ መንግስት የተጋረጠውን የህልውና አደጋ በመገንዘብ የክተት ጥሪ መቅረቡን አስታውሰው፤ ለዚህም ሁሉም ፈጣን ምላሽ ማግኘቱን ተናግረዋል።

“መላ የክልሉ ህዝብም በስንቅና ትጥቅ ዝግጅት፣ በጉልበቱና በገንዘቡ ተከታታይነት ያለው ድጋፍ እያደረገ መሆኑ ለሚካሄደው ጠላትን በያለበት የመምታት ዘመቻ ትልቅ አቅም ነው” ብለዋል።

“ይህ ጦርነት በህልውናችን ላይ የመጣውን አደጋ ለመቀልበስ የሚካሄድ በመሆኑ ፍትሃዊ ነው” ያሉት ዶክተር ሰማ “ከመላ ህዝባችን ጋር በመተባበር ድሉን ሙሉ በሙሉ እጃችን ላይ እንደምናስገባ አልጠራጠርም” ብለዋል።

“ለዚህም አብዛኛው ጠላት ወደ ክልላችን የላከው ሃይል በመመታቱ አሁን ላይ ያልሰለጠነ አርሶ አደር እየላከ መሆኑ ለድሉ አይቀሬነት ማሳያ ነው” ብወዋል።

“የክልላችን ህዝብም በጠላት ፕሮፓጋንዳ ሳይደናገር በየአካባቢው የሚመጣውን ጠላት በመደምሰስ የአባቶቹን አኩሪ ገድል ዛሬም መድገም አለበት” ሲሉ ተናግረዋል።

“እስከ አሁንም በሰሜን ወሎ የጉራ ወርቄ፣ የሃራና የዋግ አካባቢ አመራሮች ህዝባቸውን በማሰለፍ ፊት ለፊት በመጋፈጥ ጠላትን ከመደምሰስ አልፎ ከባድ መሳሪያ በመማረክ አካባቢያቸውን በጀግንነታቸው አስጠብቀዋል” ብለዋል።

“በሌሎች የክልሉ አካባቢ የሚገኘው ህዝብም የነዚህ አካባቢዎችን ልምድና ተሞክሮ በመውሰድ ወደ አካባቢው የሚመጣውን ጠላት አሳዶ በመምታት ህልውናውን ማስጠበቅ አለበት”ብለዋል።

“ለዚህም ሁሉም የአማራ ፖለቲከኞች፣ ምሁራንና ሌላው ህብረተሰብ ልዩነታችንን ወደ ጎን ትተን በጋራ በመሰለፍ በአንድነት ወደ ጋራ ጠላታችን መዝመት ይገባናል” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

አሸባሪው ህወሃት በአማራ ክልል በራያ፣ በወልቃይት፣ ጠለምት፣ ሁመራና በአበርገሌ ግንባሮች ወረራ በመፈጸም ለንጹሃን ዜጎች ሞት፣ መቁሰል፣ መፈናቀልና ሌሎች ግፎች እንዲፈጸሙ አድርጓል።

(ኢዜአ)

Exit mobile version