ETHIO12.COM

በአፋር ግንባር ትህነግ ሌላ ሽንፈት ደረሰበት፣ ሲያመልጥም ተደመሰሰ

ትህነግ ያሰለፈው ጭፍራ በአፋር ህዝብ ላይ ያደረሰው አሰቃቂ ግፍ በየትኛውም ዘመን የሚረሳ እንዳልሆነ ሆስፒታል ሆነው አስተያየት የሰጡ ይናገራሉ። በድንገት ገብቶ ምንም በማያውቁና ክምኑም ጋር ግንኙነት የሌላቸው ወገኖች ላይ ፈጸመ የተባለው ግፍ ” የጦር ወንጀል” እንደሆነ እየተነገረበት ነው። በጋሊኮማ መጠለያ ጣቢያ ከ200 በላይ የአፋር ህፃናት፣ እናቶችና አዛውንቶችን የጨፈጨፈው ትህነግ ለአፋር ህዝብ ” ከዓይንህ ይልቅ እኔን ስማና እመን” በሚል ቢናዘዘም ሰሚ ያገኘ አይመስልም።

በትምህርት ቤትና ጤና ጣቢያ በተጠለሉ ንጹሃን ላይ የትህነግ መሪዎች ባዘዙት መሰረት ጭፍራው የፈጸመው ጥቃት ” ኢትዮጵያ ዜጎቿን ለመጠበቅ የተኩስ አቁም አዋጇን ማንሳት አለባት” በሚል የአሜሪካ ፖሊስ አውጪዎች ሳይቀሩ መናገር ጀምረዋል። ለዚህም ይመስላል የአሸባሪው ቡድን ቃለ አቀባይና “የወቅቱ ፊት አውራሪ” ጌታቸው ረዳ ” ከደሙ ንጹህ ነን” ሲል አስታውቋል።

በድንገት ጭፍጨፋ ቢፈጸምበትም፣ በውል በማይታወቅ ምክንያት በድንገት ቢወረርም እንደ አንድ ነቅሎ የወጣው የአፋር ሕዝብ አኩሪ ጀግንነት እንደፈጸመ እየተሰማ ነው። በጊሌ እና በገጀራ ጭምር የጠላትን አንገት እየቀሉ ታንክ መማረካቸውን ይፋ ሆኗል። የአፋር ማህጸን ያፈራችው ሃመዱ በአሸባሪው ታንከኛ ላይ እንደ አራስ ነበር ዘሎ በመጣበቅ በጊሌ እንደሰየፈው ምስክሮች አስታውቀዋል። እንዲህ ያለው የአናብስት ምስያ ጀግንነት አፋር ላይ ስፍር ቁጥር እንደሌው የሚገልጹ ወደፊት በታሪክ እንደሚሰነድ እየጠቆሙ ነው።

ይህን ጀግንነት ደጄኔ አሰፋ ሲገልጸው ” ታሪክ ወደፊት ይዘከረዋል” ብሏል። አክሎም “የአፋር አባት በጁንታው የተገደለበትን ልጁን ሳያነሳ በቀጥታ ጠላትን ለመበቀል ወደ ፍልሚያ ገብቷል። የአፋር እናት የተገደለባትን ልጇን ከመቅበር ይልቅ የልጇን ገዳይ ለመግደል እንባዋን ዋጥ አድርጋ ዘምታለች።ሁሉም ወደፊት ብቻ ይገሰግሳል።ብዙ የሚነገሩ አፈ ታሪክ የሚመስሉ አንፀባራቂ ተጨባጭ ታሪኮች እየተመዘገቡ ነው… የአፋር ሕዝብ ክብር ይገባዋል” ሲል ብዙ ዘርዝሮ አወድሷቸዋል።

ህጻናት አሮጊት ሳይል የህዝብ ማዕበል አስነስቶ ውጊያ የሚከፍተውንና ወረራ የሚፈጽመውን የትህነግ ሃይል፣ በመጣበት መንገድ ነቅሎ በመውጣት እየመከተ ያለው የአፋር ሕዝብ ከመከላከያ ጋር በመሆኑ የትህነግን ወራሪ ሃይል አበራይቶታል። ህዝብን በማደራጀትና በማሰማራት ትልቅ ሚና የተጫወቱ የአፋር መሪዎች ከመከላከያ ጋር በቅንጅት በወሰዱት የመልሶ ማጥቃት እርምጃ የወራሪው ጭፍራ ይዟቸው የነበራቸውን ቦታዎች ማጣቱ ሲነገር ሰንብቷል። ዛሬ የሆነው ደግሞ ሌላ ነው።

“ነጩ ወንበዴ” በሚል ስያሜ የሚታወቀው እንግሊዛዊው ማርቲን ፕላውት ” ደብረጽዮን ነገረኝ” ሲል እንዳሟረተው ሳይሆን የአፋር ጀግኖች ከመከላከያ ጋር ግንባር ፈጥረው የጅቡቲን መንገድ ለመቁረጥ ያሰፈሰፈውን ጭፍራ አራግፈውታል።

ጽሁፍ የደረሰን መልዕክት እንደሚያስረዳው፣ ጀግናው የመከላከያ ሰራዊትና የአፋር ልዩ ኃይል ከድፍን ህዝብ ጋር ተጋምዶ፣ ደጀኑን ከኋላ ተማምኖ ባካሄደው ሰፊ ጦርነት ዛሬ ረፋዱ ላይ ድል አግኝተዋል።እንደመረጃው የትህነግ ጭፍራ እንደተለመደው የሰው ጎርፍ በማስለፍ፣ በከባድ መሳሪያ በመታገዝ፣ወደ ጭፍራ ለመረማመድና የጅቡቲን መንገድ ለማስተጓጎል ይረዳው ዘንድ መርጧት በነበረው ኡዋ ከተማ በተደረገ ውጊያ ተደምስሷል።በርካታ ሰው ገብሮ ኡዋን ለቅቆ ወደ አውራ ሸሽቷል።

ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ አንድ ክፍለጦር የተደመሰሰበት መሆኑ፣ ስራዊት ይዞ በከባድ ሚኪኖች ሲሸሸ ከአየር ላይ በተወሰደ ተከታታይ እርምጃ ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰበት ታውቋል። በከባድ መኪና ጭኗቸው ሲሸሽ እርምጃ የተወሰደባቸውን ሳይጨምር በጦርነቱ ብቻ 300 የሚጠጉ ቁስለኞችና ሃምሳ የሚሆኑ ምርኮኞች መመዘገባቸውም ተሰምቷል።

“እንደ ፍልፈል በሄደበት አፈር እየማሰ ፈንጂ የሚቀብረው ይህ ጭፍራ ህልውናው ማክተም ስላለበት እያሳደዱት ነው” ሲልም መልዕክቱ ያትታል።በሌላ ዜና በወልደያ ግንባር በርካታ ህጻናት የበዙበት የትህነግ ጭፍራዎች መማረካቸው ተሰምቷል።ምስላቸውም በማህበራዊ ሚዲያ ተሰራጭቷል። ከየግንባሩ ለመለከት የሚያም ቁስለኛና ሙት ምስል እየተሰራጨ ሲሆን፣ የአማራ ክልል ዘልቀው በገቡት ላይ የማጽዳት ዘመቻው በስፋት እየተካሄደ መሆኑ ተመልክቷል።

አሸባሪው ህወሓት አሜሪካ ያቀረበችውን ከአፋር እና ከአማራ ክልል ውጡ ጥያቄ ውድቅ ማድረጉን የአሸባሪው አፈቀላጤ ጌታቸው ረዳ ማስታወቁን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን መዘገባቸውን ተከትሎ አማራ ክልል ማጥቃት መጀመሩን ማወጁ አይዘነጋም። ረሃን የጦር መሳሪያና መጠቀሚያ በማድረግ ውጊያ የከፈተው ትህነግ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲነቀል እንደሚሰራም አስታውቆ ነበር።

ክልሉ ዛሬ እንዳስታወቀው የአሸባሪው ሃይል ወደ አማራ ክልል ዘልቆ በገባበት ሁሉ እየተደመሰሰ መሆኑንን አመልክቷል። ቦታና የጥቃቱን መጠን ግን አላብራራም። ክልሉ በኮሙኒኬሽን ሃላፊው አማካይነት ” አሸባሪው ከፍተኛ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ላይ በመሆኑ ህዝብ ይጠንቀቅ፣ አካባቢውን ይጠብቅ” ብሏል። አያይዞም ” ይህ ኢትዮጵያን ሊያፈርስ፣ አማራን ሊያጠፋ ያተነሳ ወንበዴ እስከነ አካቴው መንቀል የዘመቻው ዋና ግብ ነው” ሲል ቦታ በማስለቀቅ የሚቆም ጉዳይ እንዳልሆነ አመልክቷል።

በሌላ የሽብር ዜና

በአፋር ክልል በአሸባሪው የህዋሓት ቡድን ጥቃት የደረሰባቸው 48 ንጹሀን ዜጎች በዱብቲ አጠቃላይ ሆስፒታል ህክምና በመከታተል ላይ እንደሚገኙ የፋና የጋዜጠኞች ቡድን ከስፍራው ዘግቧል፡፡ንጹሀን ዜጎቹ ከቀላል እስከ ከባድ ጉዳት አስተናግደው መምጣታቸውን የሆስፒታሉ ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ኑሩ ሰይድ ለባልደረቦቻችን ተናግረዋል፡፡

ወደ ሆስፒታሉ ለህክምና ከመጡት ንጹሀን ዜጎች መካከል አራቱ ከባድ ጉዳት ስለደረሰባቸው ወደ አዲስ አበባ ለከፍተኛ ህክምና ተልከዋል ነው ያሉት፡፡ሽብርተኛው ቡድን በአፋር ህዝብ ላይ የፈጸመው ጥቃት የቡድኑን ከመጠን ያለፈ ራስ ወዳድነት እና ሴረኛነት ያሳዬ እንደሆነ ተጎጂዎቹ ተናግረዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ በሴቶች ህጻናት እና ሌሎች ንጹሃን ዜጎች ላይ የፈጸመው አሳፋሪ የፀብ አጫሪነት ተግባር የቡድኑን አረመኒያዊ ባህሪ ገሃድ ያወጣ ሰለመሆኑም ጣቢያችን ያነጋገራቸው እና በአፋር ዱብቲ አጠቃላይ ሆስፒታል የህክምና ክትትል እያደረጉ የሚገኙ ተጎጅዎች አብራርተዋል። ከአፋር ብዙሃን መገናኛ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው በዱብቲ ሆሲፒታል ህክምናቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ንጽሀን አርብቶ አደሮች እንደገለጹት÷ ጁንታው በለሊት በተኛንበት በህጻናት፣ በሴቶች እና በአዛውንቶች ላይ አሳፋሪና ዘግናኝ ጭፍጨፋ ፈጽሞብናል ብለዋል ፡፡

የተደረገብን ጭፍጨፋ በአፋር ታሪክ ውሰጥ መቼም ቢሆን የማይረሳ አሳፋሪ እና ክፉ ተግባር ነው ያሉ ሲሆን÷ ሆኖም ጁንታው መቼም እና በምንም ሁኔታ ቢሆን ወራሪነቱ አይሳካለትም ነው ያሉት ፡፡የአፋር ህዝብ ከውጭም ከውስጥም ኢትዮጵያን ለመውረር ሙከራ ያደረጉትን አሳፍሮ የመለሰ ጀግና ህዝብ መሆኑን ህክምናቸውን በመከታተል ላይ ያሉ ንጽሀን አርብቶ አደሮቹ ገልጸዋል ፡፡

Exit mobile version