Site icon ETHIO12.COM

“እምቢተኝነት ከሌለ ነፃነት አይገኝም ” የወልድያ ከተማ ወጣቶች

“እምቢተኝነት ከሌለ ነፃነት አይገኝም፣ ሁልጊዜም እሺ ከሆነ ባርነትክንም እሺ ብለህ ትቀበላለህ” የወልድያ ከተማ ወጣቶች

እምቢ ማለት ለነፃነት፣ እምቢ ማለት ለእኩልነት፣ እምቢ ማለት ለኢትዮጵያዊነት፣ እምቢ ማለት ለክብር፣ እምቢ ማለት ለፍቅር፣ እምቢ ማለት ለሀገር፣ እምቢ ስትል ትከበራለህ፣ እምቢ ስትል ታሸንፋለህ፣ እምቢ ስትል ፍትሕ ታመጣለህ፣ እምቢ ስትል ነፃ ትሆናለህ።

እምቢ ማለት ነው ያስከበረ፣ እምቢ ማለት ነው ሀገር ያሻገረ፣ እምቢ ማለት ነው ታላቅ ታሪክ ያሰፈረ፣ እምቢ ማለት ነው ወራሪን ያሳፈረ፣ ባርነትን ያስቀረ። ኢትዮጵያውያን እምቢ ባይሉ፣ ወራሪን በድንበር ማዶ ባያስቀሩ ኖሮ ዛሬ ላይ ባፈርን ነበር።

አሸባሪው ትህነግ ኢትዮጵያን ለማጥፋት ከሁሉም አስቀድሞ ደግሞ የአማራን አንገት ለማስደፋት መፍጨርጨር ላይ ነው። በአማራ ሕዝብ ላይ በተለያዩ ግንባሮች ውጊያ ከፍቷል። የአማራ ጀግኖች ከሌሎች የኢትዮጵያ ጀግኖች ጋር አሸባሪውን ቡድን በየደረሰበት እየመቱ፣ እየማረኩና እያሰደዱ ነው።

አሸባሪው ትህነግ ወልድያን ለመያዝ ተደጋጋሚ ጥቃት እየፈፀመ ነው። ወልድያ ግን በእምቢተኝነቷ ቀጥላለች፣ በጽናት ቆማለች፣ ዳሯን እሳት አድርጋለች።

አሚኮ በወልድያ ከተማ በሕልውና ዘመቻው ዘርፈ ብዙ የሕልውና ዘመቻ እያደረጉ ከሚገኙ ወጣቶች ጋር ቆይታ አድርጓል። ቴዎድሮስ አያሌው እና ድምፃዊት ስንዱ አሌ ከሌሎች የከተማዋ ወጣቶች ጋር በመሆን በወልድያ ከተማ ዙሪያ እየተዋደቀ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻ፣ ፋኖና ከሌሎች ክልሎች ለተውጣጡ ኀይሎች ስንቅ በማቀበል፣ የከተማዋን ሰላም በማስጠበቅና ሌሎች ተግባሮችን በመከዎን ላይ ናቸው። የአሸባሪውን ቡድን ወረራ ለማስቆም ወጣቶች በሚችሉትና ትግሉ በሚጠይቃቸው ሁሉ እየታገሉ ናቸው። የተጋረጠብንን ወረራ ለመጋፈጥ በቁርጠኝነት እየሠራን ነውም ነው ያሉት።

ለሁሉም መሠረቱ አንድነት ነው ያለው ቴዎድሮስ በሕይወት የተለያየ አመለካከት ሊኖረን ይችላል፣ ለሕልውና ግን የተለያየ አመለካከት ሊኖረን አይችልም ብሎናል። እኛነታችንን የሚያጠፋና በማንነታችን የመጣ በመሆኑ ሁሉም በሚችለው ልክ እየሠራ ነውም ብሏል። እኛ አንደነግጥም፣ አንፈራም፣ የመጣብንን ነገር መክተን እናልፈዋለንም ነው ያለው።

አካባቢያችን ለቅቀን የትም አንሄድም፣ ሁሉም አንድ ይሁን ሲልም ጽናታቸውን ነግሮናል። መደራጀት ኀይል ነው ያለው ቴዎድሮስ ወጣቶች ነቅተው አካባቢያቸውን ይጠብቁ፤ እነርሱ ያልጠበቁትንም ማንም ሊጠበቅ እንደማይችልም ተናግሯል። ማንም መጥቶ ነፃ አያወጣህም፣ ራስህን ነፃ የምታወጣው አንተ ነህ፣ ጉልበትህ ተቀናጅተህ ስትሠራ ነው፣ ከቅንጅትህ ላይ እውቀትና ገንዘብ ስትጨምርበት ደግሞ ስኬትን ያመጣል ነው ያለው ቴዎድሮስ።

አንድ በመሆን ያሉብንን ቀዳዳዎች ደፍነን ጠላትን መመከት እንችላለንም ብሏል። ከፊታችን ተስፋ አለን፣ በሀገራችን ተስፋ ከቆረጥን እንበተናለን፣ የሚያኮራህ የራስህ ማንነት ነው፣ አባቶች አጥንታቸውን ከስክሰው፣ ደማቸውን አፍስሰው የሰጡንን አደራና ማንነት ላለማስነጠቅ መታገል አለብን፣ አባቶች ደም ያፈሰሱበት፣ አጥንት የከሰከሱበት በእኛ ትውልድ ደርሷል፣ ነገ ለልጄ ሀገር ያቆየውልህ ከመጣ ወራሪ ጋር ታግዬ ነው ልል ታሪክ ከፊቴ ቆሟል፣ አሁን ላይ ታሪክ ሠሪ ስለሆንኩ እድለኛ ነኝ፣ ብሞት እንኳን ነብሴ ደስ እያላት ታልፋለች፣ የሞትኩት ሀገር ክጄ ሳይሆን ለማንነቴ ስታገል ነው ብሏል።

አማራ ነኝ የሚለውን በተግባር መግለፅ እንደሚገባም ተናግሯል። ሁሉም ተደጋግፎ አቅም ሊሆን ይገባልም ነው ያለው። ስንቅና ትጥቅ በበቂ ሁኔታ ከቀረበ ሚሊሻው ለወያኔ በቂ ነው፣ ለወያኔ የሚገዛ ሰው የለም፣ ነፃነቴን የማገኘው በራሴ ነው፣ እምቢተኝነት ከሌለ ነፃነት አይገኝም፣ ሁልጊዜም እሺ ከሆነ ባርነትክንም እሺ ብለህ ትቀበላለህ ነው ያለው።

በሌሎች ከተሞች የሚገኙ ወጣቶች በአሉባልታ ባለመፈታት ፊት ለፊት የሚመጣውን ቡድን መታገል ይገባቸዋል ብሏል። ከማኅበረሰቡ የሚደረገውን ድጋፍ በፍትሐዊነት እያደረሱ መሆናቸውን እና ሠራዊቱ በረሃብና በጥም እንዳይጎዳ የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ መሆናቸውንም ተናግሯል። ለሠራዊቱ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ ከሠራዊቱ ጎን ለመሰዋእት ዝግጁ ነንም ነው ያለው።

የመጣው ጠላት የግዴታ አንድ እንድንሆን የሚያደርግ ነው፣ ከተነጣጠልን የምንከፍለው ዋጋ ከፍ ያለ ነው ብሏል። እኛ ለወያኔ አንበረከክም፣ እጅ አንሰጥም፣ ወያኔ መድኃኒቷን እያገኘች ነውም ብሏል። ምንም የማያውቁ ንጹሐን ተጎድተዋል፣ በአንድነታችን ወራሪውን ከምድረ ገፅ አጥፈተን ኢትዮጵያ ሰላም መሆን አለባትም ብሏል ቴዎድሮስ።

እንደ ሕዝብ ወጥ የሆነ አቅም ሊኖር እንደሚገባም ገልጿል። ያለውን እውቀት በአግባቡ መጠቀም፣ በመደራጀት እና በማደራጀት ራስን መከላከል እና ማስከበር ይገባል ነው ያለው።

ጥሩ ነገር ሲመጣ ኃላፊው እኔ ነኝ፣ መጥፎ ነገር ሲመጣ ደግሞ ኀላፊነቱ የእርሱ ነው የሚባል ነገር የለም፣ አሁን ኀላፊነቱ የሁላችንም ነው፣ ሀገር የማዳኑ ኀላፊነት ለአንድ አካል ብቻ የሚሰጥ አይደለም ብሏል። ዘመኑን የዋጄ አንድነት፣ ትግልና አደረጃጀት ሊኖረን ይገባል፣ በዓይን ጥቅሻ የሚግባባ ሕዝብ አለን፣ በአንድነት በመቆም፣ ዓድዋ ላይ እንዴት እንደዘመትንና እንዳሸነፍን፣ ቴዎድሮስ ለሀገር፣ ለክብር፣ ለፍቅርና ለኩራት ሽጉጡን የጠጣበትን ምስጢር በመገንዘብ ለሕልውናችን መታገል ግድ ይለናል ሲልም መልእክቱን አስተላልፏል። የጠቢባን ልጆች ነን፣ በጥበብ እንሻገር፣ በአንድነት እናሸንፍም ብሏል።

ድምፃዊት ስንዱ አሌ ለሁሉም ነገር መሠረቱ አንድነት ነው ብላለች። ወልድያ አካባቢ ያለው ወጣት በመግባባት እና በአንድነት ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ገልፃለች።

የከተማዋ ከንቲባ ብርታት ወጣቶቹም እንዲበረቱ እንዳደረጋቸውም ነግራናለች። ኅብረተሰቡን ትቼ አልሄድም በማለት ያሳዩት ጽናት አስገራሚ መሆኑንም ነው የገለጸችው። የማያልፍ ነገር የለም፣ ሁሉም ያልፋል፣ ሀገራችንን ለማንም ባንዳ አሳልፈን አንሰጥም ብላለች። ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው እንዲሉ አሸባሪው ትህነግ ከጦር ይልቅ በወሬ ሀገር ለመፍታት ጥረት እያደረገ በመሆኑ ለወሬ ጀሮ ባለመስጠት በፅናት መታገል እንደሚገባም ተናግራለች።

በአሸባሪው ቡድን ወረራና ዝርፊያ የተጎዱ ንጹሐን ዜጎችን መንግሥት እንዲደርስላቸውም ጠይቃለች።

የጥበብ ሰዎች ሀገር እንድትኖር የሚቻላቸውን እንዲያደርጉም መልእክት አስተላልፋለች። ሀገር ሲፈርስ ቆሞ ያዬ ሰው ከሀገር አፍራሹ ለይቼ አላዬውም፣ ኢትዮጵያ ስትኖር ነው እኛም የምንኖረው፣ ሁሉም ለሀገሩ የድርሻውን መወጣት አለበት ነው ያለችው። አሸባሪው ትህነግ ከገባበት አካባቢ ተጠራርጎ እንደሚወጣ አንጠራጠርም ብላለች።

በአሸባሪው ትህነግ መሸነፍ የማይታሰብ ነገር ነው፣ ጀግና ሕዝብ እያለ መሸነፍ የለም፣ በአንድነት አሸባሪውን ቡድን ማጥፋት አለብን ነው ያለችው።

ለሀገር ፍቅር ካለ ትግል አይገድም፣ በዚህ ወቅት ከሁሉም ነገር በላይ ሀገርን ማዳን እንደሚገባ ገልጻለች፡፡

አማራ ኩሩና ጀግና ሕዝብ ነው፣ ኩራቱንና ጀግንነትን ለማስቀጠል በሁሉም ነገር ዝግጁ መሆን አለበት ስትል መልእክት አስተላልፋለች።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ – ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 04/2013 ዓ.ም (አሚኮ)

Exit mobile version