Site icon ETHIO12.COM

ከሱዳን የተነሳ የትህነግ ሃይል (ሳምሪ) ሳይዋጋ ሙሉ በሙሉ ተማረከ

“ሁሉም የጸጥታ ኃይሎች ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የተነሳውን የክህደት ኃይል ለመደምሰስ ብርቱ ክንዳቸውን እንዲያነሱ ታዟል” በተባለ ቅጽበት ውስጥ ሱዳን ሰለጥኖና ታጥቆ ሲጠባበቅ የነበረው የትህነግ ሃይል ሳይዋጋ መማረኩ ተሰማ።

ሱሌማን አብደላ እንዳስታወቀው በትናንትናው ዕለ ከቀኑ አስራ አንድ ሰዓት፣ እንዲሁም ለሊት ስምንት ሰአት ላይ፣ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ሊገባ የነበረው የሳሚሪ ቡድን በዝቅተኛ መሰዋእትነት ሙሉ በመሉ ተማርኳል። ከሱዳን በባህረ ሰላም በሚባል የሁመራ ግዛት ውስጥ ሾልከው ወደኢትዮጵያ ለመግባት ሲሞክሩ የተማረኩት የትህነግ የሽብር ሃይል ብዛት አንድ ሺህ ሰባት መቶ ሃምሳ እንደሚደርሱ ታውቋል። ሁለት መቶ ዘጠኝ የሚሆኑት ደግሞ ሴቶች ናቸው።

ፎሪን ፖሊሲ በደቂቃዎች ውስጥ ሁለት ጊዜ በቀያየረው ዜናው ትህነግን ለመቀላቀል ሰላሳ ሺህ የታጠቁ ታማኝ ወታደሮች ሱዳን ድንበር ላይ መግቢያ ቀዳዳ እየፈለጉ እንደሆነ በቅርቡ ዘግቦ ነበር። የትህነግን አፈ ቀላጤ ጌታቸው ረዳን ጠቅሶ የዘገበው ፎሪን ፖሊሲ ” ታማኝ የታተቀ ወታደር” ሲል የዘገበውን በደቂቃዎች ልዩነት ” ታማኝ ያልታተቁ ደጋፊዎች” በሚል ቀይሮ የዘገበውን በማስረጃ ዘግበን ነበር።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ኤታማዦር ሹም ጻድቃን ” ደርመስን እናስከፍተዋለን” ሲሉ በቅርቡ የዛቱለት የሱዳን ድንበር ጉዳይ አስራ አንድ ጊዜ በሙሉ ሃይል ተሞክሮ እንደከሸፈ መንግስት ማስታወቁ ይታወሳል። በዚህም ውጊያ ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ እንደደረሰበት ተገልጿል።

በጦርነት ተከታታይ ሙከራ፣ በውጭ አገራት ጫናና በረሃብ ስም ይህንን ኮሪዶር ለማስከፈት የተሞከርው ሙከራ ባለመሳካቱ ትህነግ “ለማስገደድ” ሲል ምክንያት ሰጥቶ ጦርነቱን በራያና አፋር ግንባር አስፍቶ ነበር። በሁለቱም አቅጣጫ በመግፋት የጅቡቲን መንገድ እንደሚቆርጡም አመልክተው ነበር።

ከሁለት ቀን በፊት ጌታቸው ረዳ ” መንግስት መጥበሻ ላይ ነው” በሚል ምጸት የግንባሩ ውጊያ በድል ታጅቦ እየሄደ መሆኑን ሲያስታውቅ፣ ቪኦኤ አማርኛን በመጠቀም ዶክተር ደብረጽዮን መንግስት ቅድመ ሁኔታዎቹን ተቀብሎ እንዲደራደር ጥሪ አቅርበው ነበር።

“ከአሸባሪ ጋር አንድ ጠረጴዛ ላይ አልቀመጥም” ሲል ምላሽ የሰጠው መንግስት አፋር ክልል በትምህርት ቤትና እጤና ጣቢያ ተጠልለው በነበሩ ህጻናትና ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጭፍጨፋ መፈጸሙን፣ ቅዱስ የሃይማኖት ስፍራዎችን መውረሩንና ሰላዊ ዜጎች ላይ በከባድ መሳሪያ ጥቃት መፈጸሙ ሊቀጥል እንደማይገባው ሕዝብ በተቃውሞ መግለጹን ተከትሎ መንግስት የተኩስ ማቆሙን እንዳነሳ ይፋ አድርጓል።

“ሁሉም የጸጥታ ኃይሎች ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የተነሳውን የክህደት ኃይል ለመደምሰስ ብርቱ ክንዳቸውን ያንሱ” ሲል መንግስት በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ጦርነቱ ከመከላከል ወደ ማጥቃት መዛወሩ ታውቋል።

በየግንባሩ ጀግናው የአማራ ፋኖ፣ ልዩ ሃይል፣ ሚሊሻ በተሰጣቸው ስምሪት መሰረት የትህነግን ሃይል ከበው እያጠቁት እንደሆነ እየተሰማ ነው። የሚያሳዝን ሰብአዊ ቀውስ ደርሶበታል። በርካታ ሕሳንናትን ጨምሮ ተዋጊዎች ተማርከዋል። ቆስለዋል።

ከወልደያ ህዝብ ጀግንነት በተጨማሪ ለምሳሌነት የተጠቀሰው የጋይንት ህዝብ ነው። “የጋይንት ገበሬ መሳርያ የሌለው መጥረቢያ ይዞ ልዩ ሀይሉን፣ ፋኖውን፣ መከላከያውን ደጀን ሆኖ ተከተለው። ክላሽ ይዞ የዘመተው ፋኖ ዲሽቃ ቀምቶ ያዘ። ጀሌ ሆኖ የሄደው የጋይንት ወጣት የትህነግን ኃይል መሳርያ ይዞ ጦሩን አገዘ። ትህነግ ይዞት የመጣው ከባድ መሳርያ መካከል ብዙው ወድሞ ቀሪው ተማረከ። መውጫ ያጣው የትህነግ ጦር የእሳት ራት ሆኗል” ጌታቸው ሽፈራው ምስክርነቱን ሰጥቷል።

በሱዳን በኩል ዘመናዊ መሳሪያ ታጥቆ በመጠባበቅ ላይ ያለውና በማይካድራ ጭፍጨፋ ፈጽሞ ያመለጠው የሳምሪ ሃይል ሰላሳ ሺህ እንዳልሆነ፣ ቁጥሩ እንደሚታወቅና ሲገባም ሆነ ሊገባ ሲሞክር ምን እንደሚደረግ ቅድሚያ ዝግጅት መኖሩን አቶ ሙሉነህ ፎሪን ፖሊሲ የዘገበውን ተክትሎ አስታውቀው ነበር። ሱሌማን እንዳለው በርካታ የሳተላይት ስልኮችን፣ ሲም ካርዶችን፣ የመገናኛ መሳሪያዎችና ዕጽ ተሸክሞ ድንበር ሲጥስ ሙሉ በሙሉ የተማረከው ሃይል አሁን ምርመራ ላይ ነው።

የነብስ ወከፍ፣ የቡድንና በቂ ሎጂስቲክ ይዘው የተማረኩት የአሸባሪው ሃይሎችን አስመልክቶ መንግስት በይፋ ያስታወቀው ነገር የለም። የትህነግ አፈ ቀላጤ ጌታቸው ረዳም ይህ እስከታተመ ድረስ ያለው ነገር የለም። አቶ ጌታቸው የብልጽግና ቀብር መቃረቡን፣ የትህነግ ሃይል መንገድ አማርጦ ወደ አዲስ አበባ ከመገስገስ የሚያግደው አንዳች ሃይል እንደሌለ ደጋግመው ከዘገቡና፣ “ጀግና” በሚል ከተወደሱ በሁዋላ የአዲስ አበባው ጉዞ ምን ያህል እንደተጋመሰ አልገለጹም። ደጋዊዎቻቸውና አድናቂዎቻቸው ግን ጉዞው የት እንደደረሰ ለማወቅ ፍላጎት እንዳላቸው ” ጌታቸው ዝም አለ” በሚል እየገለጹ ነው። መንግስትና ክልሎች በበኩላቸው ” ትህነግን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንነቅለዋለን” በሚል ተቀናጅተው ዘመቻውን እያካሄዱ ነው። ህዝብ የዘመቻውን ውጤት ደጀንነቱን እያከናወነ በመተባበቅ ላይ ነው።

ጦርነት እጅግ ክፉና አውዳሚ በመሆኑ ድርድር እጅግ ወሳኝ መሆኑንን የሚያስታውቁ ወገኖች፣ አሁንም የሰላም በር እንዳልተዘጋ እየሰበኩ ነው።

Exit mobile version