Site icon ETHIO12.COM

በአፋር ጭፍጨፋ ማግስት ኦነግ ከትህነግ ጋር ጥምረት መፍጠሩን ይፋ አደረገ፤ “ሃጫሉ” ነብስ ይማር!!

ፎቶ – ኢሬቻ በሚከበርበት ወቅት የትህነግ ታጣቂዎች በለቀቁት ጭስና ተኩስ በመቶዎች ሲገደሉ በድንጋጤ ሲያለቅሱ የነበሩ እህቶች – አፍሪካን ሚዲያ ኤጀንሲ

በህቡዕ የማይታወቀው ቀደም ሲል የኦነግ ሸኔ፣ አሁን ደግሞ የኦሮሞ ጦር መሪ እንደሆነ የሚነገርለት ጃል መሮ ከአጃንስ ከኤፒ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ከትህነግ ጋር ግንባር ገጥሞ በጥምረት እየሰራ መሆኑንን በይፋ አስታወቀ። ዜናው ለመላው ኦሮሞ አስደንጋጭ ሆኗል። “ዜናው የሃጫሉ ትንቢት አስታውሷል” ያሉ ሃሜቱ በግልጽና በይፋ መነገሩ ለውሳኔ ያመቻል ያሉም አሉ።

ትህነግ እንደወትሮው በአማራ ክልልም ሆነ በኦሮሚያ ወደየትም ስፍራ እንዳሻው መንቀሳቀስ ስለማይችል፣ በኦሮሚያ ድሮ ሲያርደው፣ ሲጨፈጭፈው፣ ሲያሸማቀቀው፣ ሲያስረውና አካሉን ሲያጎለው ወደነበረበት ክልል ለመግባት የኦሮሞ ድርጅት ስለሚያስፈልገው ኦነግን እንደመረጠ፣ ከኦነግ የተከፈሉት ቡድኖች አስቀድመው ሲናገሩ መቆየታቸው ይታወሳል።

ዛሬ ጃል መሮ በይፋ እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የሚመሩትን መንግስት ለመጣል ከትህነግ ጋር ህብረት መፍጠራቸውን አስታውቀዋል። “ከተመሳሳይ ሌሎች ታጣቂዎች ጋር በተለይም በወታደራዊ ትብብር ላይ ለመረዳዳት በመግባባት ደረጃ ተስማምተናል” ብሏል። «ጥምረቱ የጋራ ጠላትን በጋራ መፋለም » የሚሰኝ ሲሆን “ትህነግን ወደ ስልጣን ለመመልስ የጃልመሮ ሰራዊት ኦሮሞ ላይ ይተኩሳል እንደማለት ነው። ኦሮሞ ኦሮሞን ገድሎ የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪን ሊያነግስ ዓለም ፊት ለኦሮሞ ህዝብ ያውጃል” ሲል ዜናውን ተከትለው አስተያየት የጻፉ አሉ።

ጃልመሮ አርቲስ ሃጫሉ በድንገት ሲገደል ከጫካ እሳቸው የሚመሩት ቡድን በስልክ ማስፈራሪያ እንዳደረገበት በይፋ መሰማቱን ይታወስዳል። ይህንኑ ተከትሎ በቪኦኤ ማስተባበያ እንዲሰጡ ሲደረጉ ከትህነግ ጋር ከቶውንም እንደማይተዋወቁ ገልጸው ነበር። ሃጫሉ ከትህነግ ጋር ዳግም አብሮ የሚሰራ ኦሮሞ ማንም ይሁን ማን ከሃጂ መሆኑንን በተደጋጋሚ በመናገሩና፣ ይህ ንግግሩ ለተጀመረው ህብረት ስለማይሆን ጥርስ እንዲጫንበት ማድረጉ ይታወሳል። በርካቶችም ይህንን በቁጭት አስታውቀዋል።

እድሜዎ ከ18 ዓመት በላይ ከሆነ ይህን ቪዲዮ ያድምጡ

ትህነግ በአፋር 240 ሰዎችን በግፍ መጨፍጨፉን ተከትሎ የተሰማው ዜና ኢህአዴግን ዳግም የማቋቋም ዓላማ እንዳለው ያስረዳል። ቃል በቃል ባይገለጽም ተመሳሳይ የብሄር ድርጅቶች ይህን ህብረት እንደሚቀላቀሉ ተመልክቷል።

ይህ ዜና ይፋ ከመሆኑ በፊት በኦሮሚያ ቁጥራቸው በርከት ብሎ የሚገኙ የአማራ ተወላጆች ባሉባቸው ስፍራዎች የጅምላ ጥቃት ለመፈጸም መታሰቡንና ይህንኑ የሚፈጽመው ደግሞ ጃል መሮ የሚመሩት ሃይል እንደሆነ የአማራ ክልል የወቅታዊ መረጃ ሲሰጥ ጠቁሞ አልፏል።

“የአፋር ህዝብ ሃዘን በተቀመጠበት ወቅት ጭፍጨፋውን ከማውገዝ ይልቅ፣ ጭፍጨፋውን ከፈጸመው አካል ጋር ግንባር መፍጠር እንደ ኦሮሞ አሳፋሪ ነው” ሲሉ አስተያየት የሰጡ ወገኖች ” ኦሮሞ ሆኖ ሸኔን የሚደግፍ ሸኔ ሳይሆን የትህነግ ባሪያ ነው። ሲቀጥልም የሃጫሉ ገዳይ ነው” ብለዋል።

“በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው ሸኔ ከሌላው አሸባሪ ህወሓት ጋር በጋራ እንደሚሰራ ዛሬ ይፋ ማድረጉ እስከዛሬ ሲፈጸሙ የነበሩትን ዘግናኝ ወንጀሎች ገሃድ የሚያወጡ ናቸው” ሲሉ ዜናውን ተከትሎ ሃሳብ የሰጡ ” የኦሮሞ ህዝብ በይፋ ምላሽ ይሰጥበታል” ብለዋል።

የፖለቲካ ችግር ካለ በሚቻለው ሁሉ በመነጋገር ለመፍታት ደደቢት ድረስ ሄዶ ራስን መሸጥ አስፈላጊ እንዳልሆነ ያመለከተው የዲሲ ነዋሪና የዘወትር የዝግጅት ክፍላችን ተባባሪ ሂርጳሳ ” ያንን ሁሉ ረስቶ ፣ማንም ሆነ ማን የኦሮሞ ልጅ ከኦሮሞ ወንድሞቹ ይልቅ ትህነግ በልጦበት በራሱ ልጆች ላይ ጥይት ለመተኮስ መማማሉን መስማት ባይሳካም ያሳዝናል” ብሏል። አያይዞም ” ኤርትራ እድሚያቸውን ያሳለፉት ወገኖችቻን በትህነግ የዲፖሎማሲ ማዕረግ ወደ አስመራ አላቀኑም። ትህነግ አገራቸውን ነፍጓቸው፣ ቤተሰባቸውን ገድሎ፣ የቻለውን አስሮ፣ ያሻውን ቶርቸር አድርጎና አካል አጉድሎ ስላስጨነቃቸው ወደ በረሃ መግባታቸውን ዘንግተው ዛሬ ከሱ ጋር ተመልሰው ግንባር መሆናቸውን ይፋ አድርገዋል። መንገዱን ጨርቅ ያድርግላቸው” ሲል አስተአየቱን ሰጥቷል።

ፕሮፌሰር ሼትል ትሮቭል የሚባሉት ኖርዌያዊ የትህነግ ስትራቴጂስት ኢህአዴግ ቁጥር 2 መመስረቱን ይፋ አድርጓል። ቅማንት፣ ጋምቤላ፣ አገው፣ ጉሙዝ፣ ሲዳማ እና ሌሎች የትህነግንና የኦነግን ህብረት እንደሚቀላቀሉ ዜናውን ተከትሎ አስታውቀዋል። ሼትል በቀጥታ “ከጌታቸው ሰማሁ” ሰማሁ በሚል አስቀድመው መረጃ በማሰራጨት ስትራቴጂክ ሚና ያላቸው መሆናቸውን ባለፉት ዓመታት በይፋ አሳይተዋል።

በቪኦኤ ከኦነግ ሸኔ ወደ ኦሮሞ ሰራዊት ስም ሲቀይሩ “ለምን? እንዴትና ለመሆኑ እርስዎ ማን ነዎት?” የሚል ጥያቄ ያልረበላቸው ጃል መሮ ስምምነቱን አሁን ያለውን መንግስት ለመታል የተደረገ መሆኑንን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን በመዝለፍ ገልጸዋል።

ሸኔ ባሉት የተለያዩ አደረጃጀቶች ሰፊ ቁጥር ያላቸው የኦሮሞ ልጆችን፣ በክልሉ የሚኖሩ የሌሎች ብሄረሰብ አባላትን፣ እንዲሁም የመንግስት ሰራተኞችን በመግደል የሚከሰስ ደርጅት እንደሆነ ያታወቃል። አንዳንዶቹን ጥቃቶች በቪኦኤ በኩል ሲያስተባብልም ነበር።

ይህን ዜና ተከትሎ ከኦሮሚያ ያለውን ምላሽ አሰባስበን እንመለስበታለን። ዛሬ ወይም ነገ ማምሻውን ቪኦኤና ቢቢሲ ጃል መሮን በስፋት ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል። አሜሪካ በኢትዮጵያ ያለውን የተመረጠ መንግስት ለመጣል እቅድ ነድፋ እየሰራች መሆኑ፣ ዳግም ትህነግን ለማንገስ አቋም እንደያዘች፣ ከኦሮሞና እዚህ ጋር ስማቸውን ለጊዜው ከማናነሳቸው አንዳንድ የድርጅት መሪዎች ጋር በተደጋጋሚ አዲስ አበባ ባለው ኤምባሲዋ አማካይነት ስትዶልት መቆየቷ የሚታወቅ ነው።

መንግስት ከጫፍ እስከ ጫፍ ክተት ጠርቶ ትህነግ ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ባወጀበት በአሁኑ ወቅት ኢህአዴግ ቁጥር ሁለት ስለመቋቋሙ ይፋ መሆኑ አነጋጋሪ ሆኗል።

Exit mobile version