Site icon ETHIO12.COM

አሸባሪው ህወሃትን ለማጥፋት ወታደራዊ ማሰልጠኛ ለገቡ ዘማቾች የኪነ ጥበባዊ ስራዎች ይቀርባሉ

አሸባሪው ህወሃትን ለማጥፋት ወታደራዊ ማሰልጠኛ ለገቡ ዘማቾች፣ ለአገር ፍቅር መዝመት ክብርና መታደል መሆኑን የሚሳዩ ኪነ ጥበባዊ ስራዎች ይቀርባሉ። የብሄራዊ የኪነጥበብ አስተባባሪ ኮሚቴ አባልና የኪነ ጥበብ ባለሙያው ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኪነ ጥበብ በረጅሙ የኢትዮጵያ ታሪክ አንድነታችንንና እና ሉዓላዊነታችንን ለመጠበቅ የማይተካ ሚና አበርክቷል።

ኢትዮጵያ በየዘመናቱ በገጠሟት ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች፣ በመከራም በደስታም ክስተቶች ከያኒያን ለአገራቸው ሕልውና እና ሉዓላዊነት መከበር በጥበባቸው ደጀን ሆነዋል።

በየብሄረሰቡ መልከ ብዙ ባህላዊ የስነ ጥበብ ስራዎች እንዳሉ ገልፀው፤ በዘመናዊት ኢትዮጵያም አገር ስትወረር፣ ሉዓላዊነቷ ሲደፍር ኪነ ጥበብ ማህበረሰቡን በማነቃቃትና ሠራዊቱን በማጀገን ትልቅ ሚና መጫወቱን ነው ያብራራሩት።

በአድዋ ጦርነት የአዝማሪዎች ሚና ከፍተኛ እንደነበር ጠቁመው፣ በፋሺስት ኢጣሊያ ሁለተኛ ወረራ የአገር ፍቅር ማህበር የነበረው አርበኞችን የማነቃቃት ሙያ አስተዋጽኦ እንዲሁም በሶማሊያ ወረራ ከያኒያን ደጀን በመሆን የሰሩትን ጀግንነት በአብነት ጠቅሰዋል።

በአሁናዊ የኢትዮጵያ ሁኔታም የአገሪቷን ሕልውና ለመታደግ መከላከያ ሰራዊታችንን በመቀላቀል ማሰልጠኛ የገቡ ወጣቶችን ለማነቃቃት ከያኒያን ደጀን መሆናቸውን በተግባር ለማሳየት ልዩ ልዩ ኪነ ጥበባዊ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ የገጠሟትን ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎችን ለመመከት ‘ለአገር እዘምታለሁ የትም፣ መቼም፣ በምንም’ በሚለው መሪ ሃሳብ በመመራት “የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችም ሚናቸውን እየተወጡ ነው” ብለዋል።

በዚህም በውጭ አገር የሚኖሩና ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን በአንድ ማዕከል የሚያስተባብር ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደስራ መግባቱን አውስተዋል።

ይህም ለኢትዮጵያ ሕልውና ለሚዋደቀው መከላከያ ሰራዊት አባላት ለአገር ፍቅር መዝመት ክብርና መታደል መሆኑን የሚሳዩ ኪነ ጥበባዊ ስራዎችን ለማቅረብና ደጀን መሆኑን ለማረጋገጥ በተለያዩ መንገዶች ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አብራርተዋል። በዚህ ተልዕኮም በነገው ዕለት በመጀመሪያ ዙር በርካታ ከያኒያን ወደ ተለያዩ ማሰልጠኛ ጣቢያዎች እንደሚሰማሩ ነው ያብራሩት።

በቀጣይም ተመሳሳይ ስምሪቶች እንደሚኖሩ ገልፀው፤ በወታደራዊ ማሰልጠኛ ጣቢያዎች ብቻ ሳይሆን አጥንት ለሚከሰክሱትና ደማቸውን ለሚያፈሱት የመከላከያ ሰራዊት አባላትና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች በሚገኙበት ግንባር በመዝለቅም ኪነ ጥበባዊ ስራዎች እንደሚቀርቡ ተናግረዋል።

ከያኒያኑ ወደ ግንባርና ማሰልጠኛ ጣቢያዎች ተሰማርተው ከማነቃቃትና ከማዝናናት ባሻገር በተናጠል እንደየመክሊታቸው ኪነ ጥበባዊ ስራዎችን እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።

በውጭም በአገር ውስጥም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን “አገር አትፈርስም” በሚል ለአገራቸው ህልውና ዘመቻ እያገዙ መሆኑን ገልጾ፤ ይህ በባህልና ቱሪዝም አደራጅቶ እስከ ቀበሌ ባለው መዋቅር ሊሰራበት እንደሚገባም አመልክተዋል።

ሌሎች የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችም በተደራጀ መልኩ አገር የገጠማትን ፈተና በየደረጀውና በተለያየ ኪነ ጥበባዊ ስልት እወነታውን ለማህበረሰቡ በማቅረብ ማነቃቃትና ማስገንዝብ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

(ኢ.ፕ.ድ)

Exit mobile version