Site icon ETHIO12.COM

“… በብረት ድስት አንመስለም”

የአማራ ክልል ውስጥ ሆን ብለው ሃሳት የሚያራቡ፣ የጦርነት ተለዋዋጭ ገጽታን፣ ያጋጠመውን ፈተናና ከፈተናው ጀርባ ያሉትን እጆች ብዛት በቅጡ ካለመረዳት የተነሳ እዛም እዚህም የሚወረወሩትን አስተያየቶች አስመልክቶ ይመስላል መረጃው የተላለፈው።

በጦርነት መቶ በመቶ ለድል ያበቃል የተባለ ስልት በጥቃን ስህተት ሊበላሽ ይችላል። ያልተገመቱና ድንገት ሁኔታዎችን ሊቀይሩ የሚችሉ አጋጣሚዎች ልያጋጥሙ ይችላሉ። ባለሙያዎች በተደጋጋሚ እንደሚሉት ጦርነት በየሰዓቱ ተለዋዋጭ ባህሪያቶች አሉት። ወደ ትህንግ ሲመጣ ደግሞ አሁን እያደረገ ያለው የሞት ሽረት ትግል ነው። በሱዳን ኮሪዶር አግኝቶ መታጠቅና ድጋፍ ማሰባሰብ ካልቻሉ ዝለው የሚጠፉበት ወቅት ላይ ናቸው።

በዚህ መነሻ በነጭ ወያኔዎችና በሚታወቀው የዓለም ዓቀፍ ድርጅት፣ በሃያላኑ አገራትና በግብረሰናይ ድርጅቶች ታጅበው ያለ የሌለ ሃይላቸውን አሰባስበው ነው ዘመቻ የከፈቱት። ያሰለፉት የሰው ሃይል ወደ ጥያት እየተንጋጋ ሲገባ ለማመን ይከብዳል። በውጊያ ላይ የተሳተፉ እንደሚሉት ትህነግ ያሰለፈ ሃይል ባዝቱ ብቻ ሳይሆን ለመሞት ወደ ጥይት አፍ እየተንጋጉ ሲገቡ የጤና አይመስልባቸውም። እና እንደዚህ እየተግተለተለ ከሚርመሰመስ ሃይል ጋር ነው በየአውዱ ያለው ውጊያ። የአማራ ክልል የኮሙኒኬሽ ጉዳዮች ጽህፈት ቤትን ጠቅሶ ኢዜአ የሚከተለውን ዘግቧል። እንዳለ ቀርቧል።

“ህልውናችንን ለማስጠበቅ ከሚያስፈልጉን ሥነ ልቦናዊ፣ አካላዊ እና ቁሳዊ ዝግጅቶች መሳ ለመሳ እየተደማመጡ የመስራት ልምዳችንን ማጎለብት ያስፈልገናል” ሲሉ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ የአማራ ክልል የመንግስት ኮምንኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዋና ዳይሬከተር ተናገሩ።

“አሁን የምንገኝበት ሁኔታ የህልውናችንን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሚያስፈልገንን መስዋእትነት ሁሉ እየከፈልን ያለንበት ወቅት ነው፡፡ የህልውናችን ቀጣይነት የሚረጋገጠው በህልውናችን ላይ የመጣውን ትህነግና ከትህነግ ጀርባ የሸመቁ የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችንን አራግፈን ስንጨርስ ብቻ እንጂ በአንዲት ጀንበር በሚገኝ የጦር ሜዳ ድል አይደለም” ብለዋል።

አክለውም “በአንዲት ጀንበር ውስጥ የሚከፈል የጦር ሜዳ መስዋእትነትን ነጥሎ በማውጣት ተሸነፍን ብሎ እምቧከረዩ ማለት የገጠመንን የህልውና አደጋ መጠን በቅጡ አለማወቃችንን እንጂ ነባራዊ ሁኔታውን አያሳይም” ሲሉ አቶ ግዛቸው ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

ህልውናችንን ለማስጠበቅ የገባንበት ትግል መልከ ብዙ፤ ቅጥልጥል እና ብዙ አይነት ፍላጎት ያላቸው በርካታ አካባቢያዊ እና ዓለም አቀፋዊ ቡድኖች፣ ተቋማት፣ መንግስታት ጭምር ተዋናይ የሆኑበት የሞት ሽረት ትግል ነው፡፡ ይህ ደግሞ የተደራጀ፣ የተቀናጀ እና በትንሽ ድል የማይኩራራ በገጠመው ፈተና የማይዝልና የማይደነግጥ መንፈሰ ጠንካራነትን ይጠይቃል፡፡ ተጋድሏችን በእሳት ቃጠሎ ውስጥ ማለፍን በብርቱ ወጀብ ላይ መቅዘፍን ይጠይቃል፡፡

በዚህ ሂደት እየተፈራረቀ የገጠመንን የሀሩር ሙቀት ወይም ከቁር የከፋ ብርድ የስኬታችን ወይም የውድቀታችን መለኪያ ልናደርገው አይገባም፡፡ እኛ ህልውናችንን ለማስጠበቅ የሞት ሽረት ትግል የገጠምን ህዝቦች እንጂ በጥቂት ሙቀት የምንግል፤ በትንሽ የንፋስ ሽውታ የምንበርድ ብረት ድስት አይደለንም፡፡ ህልውናችንን ለማስጠበቅ የገባንበት ፍልሚያ መውጣት መውረድን ፤ መውደቅ መነሳትን፤ መራብ መጠማትን፤ ማጥቃትም ሆነ ማፈግፈግን ይጠይቃል፡፡ በትግላችን ውስጥ የሚፈራረቁት ሁነቶች የትግላችንን ሂደት እንጂ ውጤቱን አያረጋግጡም ፡፡

እነዚህን እውነታዎች ታሳቢ በማድረግ ከተለዋዋጩ የትግል መድረክ ጋር ራሳችንን ማላመድ፤ በጠንካራ አደረጃጀት መጋመድ እና እየተደማመጡ መሥራት የግድ ይላል፡፡በዚህ አግባብ ራሳቸውን ያዘጋጁት የወልደያ፤ የሠቆጣ እና የጋይንት ህዝብ የትህነግን ወረርሽኝ እንዴት አድርገው እንዳራገፉት ማስታወሱ ጠቃሚ ትምህርት ለማግኘት ይረዳል፡፡ ከከተማዋ መሪዎችና ከፀጥታ ኃይሎች ጋር እየተናበበ ለህልውናው የቆመው የወልድያ ከተማ ህዝብ ራሱን ከመከላከል አልፎ ከተማውን እንዳስከበረ ጠላቱን ባለበት ለመቅበር ጫፍ ላይ ደርሷል፡፡

በሠቆጣ ዙሪያ አሰፍስፎ ከተማዋን እየተሽከረከረ በተደጋጋሚ የማጥቃት ሙከራ በማድረግ የሠቆጣ ወጣቶችን ጥሶ ለመግባት የሞከሩት የትህነግ ታጣቂዎች ውጥናቸው መሬት የማይነካ ሁኖ በመቅረቱ እጣ ፋንታቸው ማፈግፈግ ብቻ ሁኗል፡፡ ከዚህ እልቂት ትምህርት መቅሰም ያልቻለውና ወደ ጋይንት ምድር የተመመው ተረኛ ሟች በጋይንት ከተማ መግባት ቢችልም መውጣት ግን አልሆነለትም፡፡

አሁን ላይም ተቆርጦ የቀረውን የአሸባሪውን ኃይል ለመምታት የወዳጅ ኃይል ብርቱና ውጤታማ ትግል እያደረገ ይገኛል። ይህ የጥፋት ቡድን በከተማዋ በቆየባቸው የሠዓታት እድሜ ውስጥ ያደረጋቸው ሆስፒታል እና የግለሰቦችን ሀብት የመዝረፍ፤ የዱቄት ፋብሪካ የማቃጠል፣ ቤተ ክርስቲያን በከባድ መሳሪያ መምታት እና በንጹሃን ላይ የፈጸማቸው ግድያዎች የአሸባሪውን ቡድን ትክክለኛ ማንነት ያሳያሉ፡፡

ይሁን እንጂ ጋይንቴዎችም ልክ እንደ ወልድያና የሠቆጣ ህዝብ ሁሉ በፈጠሩት ቅንጅት እርስ በእርሳቸው እንዲናበቡ እና እንዲደማመጡ ስላስቻላቸው የሽብር ቡድኑ ሊዘርፈው የነበረን ባንክ ተፋልመው ከማስጣላቸው ባሻገር ከወዳጅ ተዋጊ ኃይሎች ጋር ትስስር እየተመሩ ከሞት የተረፈውን የትህነግ መንጋ እያሳደዱ ከጋይንት ወደ ደብረ ዘቢጥ እንዲሸሽ አድርገውታል፡፡ስለሆነም የአሸናፊነት ድል የሚገኘውና እየተገኘም ያለው ከመደራጀት፤ ከመቀናጀት እና ከመደማመጥ የመነጨ መሆኑን በመገንዘብ ህልውናችንን ለማስቀጠል በፍልሚያ ላይ የምንገኝ ሁሉ የነዚህን ከተሞች አኩሪ ገድል አብነቶቻችን አድርገን ልንከተል ይገባል፡፡ ህልውናችንን ለማስጠበቅ ከሚያስፈልጉን ሥነ ልቡናዊ፣ አካላዊ እና ቁሳዊ ዝግጅቶች መሳ ለመሳ እየተደማመጡ የመስራት ልምዳችንን ማጎለብት በእጅጉ ያስፈልገናል፡፡

Exit mobile version