ETHIO12.COM

በአላማጣና ሃራ – ትህነግ የፈጸመው ግፍ

”አሸባሪው የህወሃት ቡድን በሰው ልጅ ላይ ሊፈፀም ይችላል ተብሎ የማይጠበቅ ዘግናኝ ግፍና በደል ፈፅሞብናል” ሲሉ ከሰሜን ወሎ ዞን ተፈናቅለው በደሴ ከተማ የተጠለሉ ዜጎች ተናገሩ። የደሴ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች ከሰሜን ወሎ ዞን ተፈናቅለው በከተማው የተጠለሉ ዜጎች የእለት ምግብ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።

የአላማጣ ከተማ ነዋሪ የነበሩት ወይዘሮ ትርሃስ ከበደ አሸባሪው ህወሃት በከፈተው ጦርነት ተፈናቅለው በደሴ ከተማ ቅዳሜ ገበያ ትምህርት ቤት ተጠልለው እንደሚኖሩ ተናግረዋል፡፡

ቡድኑ በማንነታቸው ብቻ አሰቃቂ ግፍና መከራ እንደፈፀመባቸው ጠቁመው፤ ሃብት ንበረታቸውን ትተው ነፍሳቸውን ለማትረፍ ጥረት ቢያደርጉም የ16 ዓመት ልጃቸው የት እንደገባ እስካሁን እንደማያውቁ ገልፀዋል፡፡

ቡድኑ በደረሰበት አካባቢ ሁሉ ወጣቱን እያፈነ በመውሰድ ወደ ጦርነት ከመማገዱ ባለፈ ሃብት ንብረት እየዘረፈና እያወደመ መሆኑ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡

አንድ ልጃቸውን ይዘው እስከ ውጫሌ ድረስ ጫካ ለጫካ በእግራቸው እንደመጡ የሚናገሩት ወይዘሮ ትርሃስ የደሴ ህዝብ ላደረገላቸው ድጋፍና አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ሌላው የሃራ ከተማ ነዋሪ የነበሩት ተፈናቃይ አቶ ይመር ጌታቸው በበኩላቸው አሸባሪው ቡድን ያልፈፀመው ግፍና መከራ የለም ብለዋል፡፡

ወደ ከተማችን እንዳይገባ ተደራጅተን ለ15 ቀን ከፍተኛ ትግል ብናደርግም በከባድ መሳሪያ ጭምር ጭካኔ ክንዱን አሳርፎብናል፤ በርካቶችን ጨፍጭፏል፤ የተወሰኑ ወጣቶችን አፍኖ ወስዷል፤ ሃብት ንብረታችንን ዘርፏል ሲሉ ተናግረዋል።

ከጦርነቱ የተረፉ 6 ልጆቼንና ነፍስ ጡር ባለቤቴን ይዤ ጫካ ለጫካ እንደምንም ተሽሎክልኬ ደሴ ከተማ መድረስ ችያለሁም፤ ያሉት አቶ ይመር ወጣቱ ከመንግስት ጋር ተቀናጅቶ የእለት ደራሽ ምግብ እያቀረበልን በመሆኑም መደሰታቸውን ገልፀዋል።

የግብርና ስራቸውን በሚያከናውኑበት በዚህ ወሳኝ ወቅት ያላሰቡት መከራ እንደደረሰባቸው ጠቁመው፤ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የሚፍጨረጨረውን ቡድን ተረባርበን ለመጨረሻ ጊዜ መቅበር አለብን ይላሉ።

”አሸባሪው ቡድን ሴቶችን በመድፈር፣ ወጣቶችን በመረሸን፣ ሃብት ንብረታችን በመዘርፍ የጭካኔ ለምዱን በተግባር አሳይቶናል” ያሉት ደግሞ ጉባ ላፍቶ ወረዳ የተፈናቀሉት ወይዘሮ በለጡ አስማረ ናቸው፡፡

የሚገድላቸውን ንጹሃን ዜጎች እንኳ እንዳንቀብር በመከልከል ለአውሬና ለአሞራ በመስጠት ለአማራ ያለውን ጥላቻ በተግባር እንዳሰየ ተናግረዋል።

”አንድ ልጃቸውንና ደካማ ባለቤታቸውን ይዘው በደሴ ጊዜያዊ መጠለያ ነን” ያሉት ወይዘሮ በለጡ የደሴ ህዝብ፣ ወጣቱ፣ ነጋዴውና አመራሩ ያደረገልን ትብብር የወሎን ባህልና እሴት ከማስጠበቁም ባለፈ ተስፋ ሰጥቶናል”ብለዋል።

ቡድኑ ወጣቱን እያፈነ ወደ ማይታወቅ ቦታ ከመውሰዱም ባለፈ ሴቶችን አሰገድዶ እየደፈረ እንደሆነም ተናግረዋል።

ከደሴ ከተማ ወጣቶች መካከል ብርሃኑ ይመር በሰጠው አስተያየት ለተፈናቃዮች የእለት ደራሽ ምግብና ቁሳቁስ ለማቅረብ ወጣቱ ተደራጅቶ ከመንግስት ጋር እየሠራ ነው፡፡

ህብረተሰቡንም አስተባብረው ሽሮ፣ በርበሬና እንጀራ በማሰባሰብ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው የመጡ ሰዎችን እየመገቧቸው መሆኑንም ተናግሯል፡፡

የደሴ ከተማ አስተዳደር መንግስት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ምሳየ ከድር በበኩላቸው አሸባሪው ቡድን በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት እየፈጸመ በመሆኑ ለመጨረሻ ጊዜ በጋራ ማጥፋት ይጠበቅብናል”ብለዋል።

በሰሜን ወሎ ዞን ንጹሃን ዜጎች ላይ በከፈተው ጦርነት ህይወታቸውን ካጡት በተጨማሪ ከቤት ንበረታቸው ተፈናቅለው ደሴ የተጠለሉ ተፈናቃዮች ቁጥር ከ55 ሺህ ማለፉን ገልጸዋል፡፡

ትምህርት ቤቶችን ለጊዜያዊ መጠለያነት በማዘጋጀት የእለት ደራሽ ምግብ ህብረተሰቡን፣ ወጣቱን፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችንና ሌሎችን በማስተባበር ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የተፈናቃች ቁጥር በየስዓቱ በመጨመሩ ከፍተኛ መጨናነቅ መፍጠሩን ጠቁመው፤ ሁሉም በሚችለው የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከተፈናቃዮች መካከል አብዛኞች ሴቶችና ህጻናት እንደሆኑ ጠቁመው፤ የአሸባሪው ህወሓት ቡድን አባላት ከተፈናቃዮች ጋር ሰርገው እንዳይገቡም ከፍተኛ ቁጥጥርና ክትትል ከመድረጉም ባለፈ የሰዓት ገደብ መጣሉን ሃላፊዋ ጨምረው አስታውቀዋል። ምንጭ – ኢዜአ

Exit mobile version