Site icon ETHIO12.COM

የማንቂያ ደወል!

አንዳችን ለሌላችን ወታደር ሆነን አገርን ለማፍረስ የሚደረጉ ከንቱ ቅዥቶችን እስከ መጨረሻው ማምከን ይጠበቅብናል

ኢትዮጵያውያን አንዳችን ለሌላችን ወታደር ሆነን አገርን ለማፍረስ የሚደረጉ ከንቱ ቅዠቶችን እስከ መጨረሻው ማጥፋት ይጠበቅብናል።

አሸባሪዎቹ ህወሃት እና ሸኔ በይፋ “ትብብር ፈጥረናል” ማለታቸው በድብቅ ሲያከናውኑት የቆየው አገር የማፍረስ ተልዕኮ በመክሸፉ ተስፋ መቁረጣቸውን እንደሚያመላክትም ነው የተገለጸው።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚያዚያ 2013 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ “ሕወሓት” እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት መፈረጁ ይታወሳል። የሽብር ቡድኖቹ ቀደም ሲል በተለያዩ አካባቢዎች ግጭት፣ ግድያና መፈናቀል እንዲከሰት በማድረግ ኢትዮጵያን ለማተራመስ በስውር ተቀናጅተው ሲሰሩ ቆይተዋል። ከቀናት በፊት ደግሞ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን ይፋ አድርገዋል።

ኢዜአ ወቅታዊ አገራዊ ጉዳይን በሚመለከት የብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ከአቶ ታዬ ደንደዓ እና ከፍልስፍና ምሁሩ አቶ ዮናስ ዘውዴ ጋር ቆይታ አድርጓል።

አቶ ታዬ ደንደዓ እንዳሉት፤ አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን በመራባቸው 27 ዓመታት በየትኛውም የአገሪቱ ከፍል በሚኖሩ ዜጎች ላይ አሰቃቂ ግፍ ሲፈጽም ቆይቷል። ኢትዮጵያውያን ወጣቶች መስዋዕትነት በመክፈል የአሸባሪው ህወሃት የአፈና አገዛዝ እስከ መጨረሻው እንዳሰናበቱት አስታውሰዋል።

የሽብር ቡድኑ “ሸኔ” የሚባለውን ስብስብ የአፈና አገዛዙን ለመመለስ እንደ ጭንብል እየተጠቀመበት መሆኑን የተናገሩት አቶ ታዬ፤ ቡድኑ በስልጣን ላይ በነበረባቸው ዓመታት “ሸኔ ናችሁ” በሚል የኦሮሚያ ወጣቶችን ሲያሰቃይና ጥፍር ሲነቅል መቆየቱ የቅርብ ጊዜ ትውስታ መሆኑን አስረድተዋል። በድብቅ በማስታጠቅም የኦሮሞ ህዝብ ላይ ግፍ እንዲፈጸም ሲያደረግ መቆየቱንም አብራርተዋል።

በመሆኑም አሁን ላይ በይፋ “አብረን እንሰራለን” በማለት ማወጃቸው በድብቅ ሲያከናወኑት የቆዩት አገር የማፍረስ ተልዕኮ ባለመሳካቱ ተስፋ መቁረጣቸውን እንደሚያመላክት አስረድተዋል።

አሸባሪው ሸኔ የኦሮሞ ወጣቶችን ሲገድልና አካል ሲያጎድል ከነበረው አሸባሪው ህወሃት ጋር ትብብር መፍጠሩ የቡድኑ ጉዳይ አስፈጻሚ እንጂ ለኦሮሞ ህዝብ መብት የቆመ ድርጅት አለመሆኑን በተግባር ማስመስከሩን ጠቁመዋል።

“የኦሮሞ ወጣቶች የህወሃት ግፍ አንገሽግሿቸው ወደ ጎዳና ሲወጡ አሸባሪው ሸኔ የሚባለው ስብስብ የት ነበር፤ ይህም የሁለቱን የሽብር ቡድኖች የቀደመ ጋብቻ ያሳያል” ብለዋል።

በመሆኑም የሽብር ቡድኖቹ አሁን ላይ በይፋ በጋራ እንሰራለን ማለታቸው ለኦሮሞ ህዝብ የማንቂያ ደወል እንደሚሆን ገልጸዋል።

የፍልስፍና ምሁሩ አቶ ዮናስ ዘውዴ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ አገር ሳንፈልገው የምናፈርሰው ስንፈልገው የምንገነባው ቀላል ጉዳይ አይደለም። በአገር ህልውና ላይ አደጋ የሚጥል ጠላት በበዛ ቁጥር ኢትዮጵያዊያን በጋራ እንደሚቆሙ የኢትዮጵያ ታሪክ እንደሚያሳይም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያዊያን ሁሉም ነገር ከሀገር በታች መሆኑን ያስተማሩ ቀደምት ህዝቦች መሆናቸውንም ነው አቶ ዮናስ ያብራሩት።

ልማት፣ ብልጽግናና ክብር እውን የሚሆነው አገር ጸንታ ስትቆም መሆኑን የገለጹት አቶ ታዬ ደንደዓ፤ ይህ ጉዳይ በኢትዮጵያውያን አእምሮ ውስጥ መታሰብ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

አገር ከሚጸናባቸው ጉዳዮች መካከል የጸጥታ ተቋማት ዋነኞው በመሆኑ ኢትዮጵያውን ከመቼውም ጊዜ በላይ የመከላከያ ሠራዊት ደጀን እንዲሆኑ አመልክተዋል።

“ኢትዮጵያን የማይፈልጉ ጠላቶችን ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያዊያንን የማድረግ አቅም መመልከት ተገቢ ነው” ያሉት ደግሞ አቶ ዮናስ ዘውዴ ናቸው።

ኢትዮጵያውያን አንዳችን ለሌላችን ወታደር በመሆን “ሀገርን እስከ መጨረሻው የምናጸናበት ጊዜው አሁን ነው” ያሉት አቶ ዮናስ፤ “እያንዳንዳችን ለአገር ህልውናና ክብር መስዋእት ለመሆን ጭምር ቁርጠኛ መሆን ይገባል” ነው ያሉት።

(ኢ ፕ ድ )

Exit mobile version