Site icon ETHIO12.COM

‹‹ ሸኔ ለዘመናት የኦሮሞን ትግል ያኮላሽ ነው›› ገላሳ ዲልቦ

“ነዲ ገመዳ የት ነው?” ጥያቄ ተጠየቀ። “ነዲ ገመዳ የት እንዳለ ነገሩን፣ ሞቷል?” ጥያቄ ተከተለ። የሊሎች የኦሮሞ አብሪ ኮከቦሽ ችም እየተነሳ ” የት ደረሱ?” የሚል ጥያቄ ሲነሳ እምባ ፈሰሰ። ይህ ሁሉ የሆነው አምቦ በተደረገ ስብሰባ ነበር። ጥያቄው አምቦ ብቻ ሳይሆን ሌላ መድረክም ላይ ቀርቦ ነበር።

ነዲ ገመዳ ማን እንደበላቸው የሚያውቁ አሉ። እነሱም ትህነግና ኦነግ ሸኔ ብቻ ናቸው። ለዚህም ይመስላል ዋና መስራችና መሪዎችን አግልሎ “ሸኔ” የሚል ስያሜ የውሰደው የኦነግ አምስተኛው ሽራፊ ዛሬ ከስትራቴጂካል ወዳጁ ጋር በይፋ ጋብቻውን ያወጀው። ኦነግ ሸኔ አመራሮቹ በምህረት አዲስ አበባ ሲገቡ ሰራዊቱን በመቀለ በኩል በቀይ ወጥ ግብዣ ሲያስገባ ነበር በርካቶች “ነገሩ ምንድን ነው?” ብለው የነበሩት።

ዛሬ ለአዲስ ዘመን መግለጫ የሰጡት ቱባው የኦነግ መሪ፣ የሃረርጌ ጫካና ዋርካ የሚያውቃቸው ገላሳ ዲልቦ ” ሸኔ ለዘመናት የኦሮሞን ትግል ያኮላሸ ነው፣ እንደነ ታጋይ ነዲ ገመዳ፣ ታጋይ ጉተማ ሀዋስ ያሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ብርቅዬ የኦሮሞ የነፃነት ታጋዮችን ገድሎ በውል ያልገለጸ ድርጅት ነው” ሲሉ የሚያውቁትን የተናገሩት። አዲስ ዘመን ገላሳ ዲልቦን ጠቅሶ የሚከተለውን ብሏል።

የአሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ጥምረት ዓመታት ያስቆጠረውን የተደበቀውን የጥፋት ወዳጅነታቸውን ይፋ ከማድረግ ያለፈ ውጤት እንደማያመጣ ሕዝቡ ማወቅ አለበት ሲሉ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ታጋይ የነበሩት አቶ ገላሳ ዲልቦ ገለጹ።

አቶ ገላሳ ይህን ጉዳይ በተመለከተ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ህወሓት ባለፉት ዓመታት የዴሞክራሲ ጭንብል ለብሶ በመምጣት ሕዝቡን እያታለለ በፍጹም አምባገነንነት ከአመለካከቱ በተቃራኒ የቆሙትን በእስርቤት ያጎረ፣ አፍኖ የገደለ ያሰቃየና ከአገር እንዲባረሩ ያደረገ ግፈኛ ቡድን ነው።

የሁለቱ ቡድኖች ግንኙነት አሁን ግልጽ ከመደረጉ ባለፈ ዓመታትን ያስቆጠረ ጉዳይ ነው ያሉት አቶ ገላሳ፤ አሸባሪዎቹ በይፋ ጥምረት መፍጠራቸው አያስደንቅም ብለዋል።

 ሸኔ ለዘመናት የኦሮሞን ትግል ያኮላሽ ነው፣ እንደነ ታጋይ ነዲ ገመዳ፣ ታጋይ ጉተማ ሀዋስ ያሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ብርቅዬ የኦሮሞ የነፃነት ታጋዮችን ገድሎ በውል ያልገለጸ ድርጅት ነው ሲሉም ጠቁመዋል።

ኦሮሞ እንደማንኛውም ወንድም ለነፃነቱ በመታገል የተጫነበትን የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጭቆና አሽቀጥሮ ለመጣል እልህ አስጨራሽ ትግል ያደረገ ሕዝብ መሆኑን አስረድተዋል።

አሸባሪው ህወሓት ከአፈጣጠሩ «ሥልጣን ያለኔ፣የብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ ያለኔ በአጠቃላይ ሁሉም ነገር ያለኔ» በሚል የሚያራምድ ድርጅት ነው። ለእዚህም እንደማሳያ የሌሎቹን አስተዋጽኦ መቀማቱን ይጠቅሳሉ፤ የኦነግ አስተዋጽኦ ለመቅበርም በሽግግር ጊዜ በስምምነት ስም የኦነግ ወታደሮች ካምፕ እንዲገቡ በማድረግ የፈጸመው ሸፍጥ በኦሮሞ ትግል ላይ ያስከተለው ጉዳትና ጠባሳ በታሪክ የማይረሳ ሴራ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የሽብር ቡድኑ የኦሮሞንም ሆነ የተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብን እንዳልጎዳ፣ ሀብቱን እንዳልዘረፈና ሕይወት እንዳልቀጠፈ አሁን ላይ ምላሱን በቅቤ አሽቶ ፊቱን በጨው ታጥቦ ብቅ ማለቱ ሀፍረት የማይሰማው ቡድን መሆኑን ያሳያል ብለዋል አቶ ገላሳ።

የአሸባሪው ህወሓት የግፍና የሽብር ድርጊት የቅርብ ጊዜ ድርጊት እንደመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁስሉ አልደረቀለትም፣ ክስተቱንም አልዘነጋም ብለዋል።

አሸባሪው ሸኔ የኦሮሞን ሕዝብ ያሰቃየና ከባድ ዋጋ ሲያስከፍል ከነበረው ቡድን ጋር ጥምረት እንዳደረገ መስማትም ይከብዳል ያሉት አቶ ገላሳ፤ የህወሓትን ገዳይነት ሸኔ ቢረሳ የኦሮሞ ሕዝብ አይረሳም፣ ከዚህም ባለፈ በርካታ የኦሮሞ ታጋዮች አስክሬኖችን ያስተናገዱት የኦሮሚያ ወንዞችና ጫካዎች አይረሱትም ሲሉም ተናግረዋል።

ከሁሉም በላይ ቡድኖቹ በፕሮፓጋንዳ ሕዝብን ማሸበር መቀጠላቸው አይቀሬ በመሆኑ የእነዚህን የሽብር ቡድኖች ዓላማ ለማምከን መገናኛ ብዙኃንን ጨምሮ በተለያየ መንገድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ተጠናክሮ በስፋት ሊሰራ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

Exit mobile version