Site icon ETHIO12.COM

ሃብትና የገቢ ምንጭ “አናስመዘግብም” ያሉ 62 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራንና ሰራተኞች በህግ ሊጠየቁ ነው

ሀብትና የገቢ ምንጫቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ያልሆኑ 62 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራንና ሰራተኞች በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የፌደራል የሥነምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

በኮሚሽኑ የፀረ-ሙስና ህግ ምክር፣ ትግበራና ልምድ ቅመራ ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ ጋሻው እንደገለፁት ሀብትና የገቢ ምንጫቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ያልሆኑት 16 የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የኒቨርሲቲና 46 የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ሠራተኞች ናቸው፡፡

ማንኛውም የመንግስት ተሿሚ፣ የህዝብ ተመራጭ እና የመንግስት መስሪያ ቤቶችና የልማት ድርቶች እንዲሁም የህዝባዊ ድርጅት ሰራተኞች የቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ ሀብትና የገቢ ምንጫቸውን ማስመዝገብ እንዳለባቸው ቢደነገግም ህጉን የሚተላለፉ በመኖራቸው ተጠያቂ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ሀብትን አለማስመዝገብ እና ሆን ብሎ የተሳሳተ መረጃ መስጠት የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ ተሻሽሎ በወጣው አዋጅ 881/2007 አንቀጽ 19 ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት በሙስና ወንጀል ህግ ያስጠይቃል ብለዋል፡፡

ይህንን በማስመልከትም ኮሚሽኑ ከዚህ በፊት የሰጠውን የሀብት ማስመዝገብ የጊዜ ገደብ ተጠቅመው ለማስመዘገብ ፈቃደኛ ያልሆኑ አካላትን መረጃና ማስረጃ በማጠናቀር የመክሰስና የመመርመር ሥልጣን ለተሰጣቸው አካላት ለመላክ የማጣራት ስራ እየተሰራ ነው ማለታቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል። ምንጭ ፋና

Exit mobile version