ETHIO12.COM

ትህነግ በሰሜን ወሎ የፈጸመው ጭፍጨፋ የሳተላይት መረጃ

ከሰሞኑን በእንግሊዙ የቴሌግራፍ ጋዜጣ የወጣው የምርመራ ሪፖርት መነጋገሪያ ሆኗል። ሪፖርቱ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ አከባቢ አጋምሳ ተብላ የምትጠራ ከአፋር ክልል የጥቂት ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ መንደር ሙሉ በሙሉ መውደሙን በሳተላይት ምስል በታገዘ ሁኔታ ቀርቧል።

ሪፖርቱን ያዘጋጀው ጋዜጠኛ ዘካሪያስ ዘላለም፥ በተደረገው የምርመራ ስራና ከአከባቢው ወደ ደሴ የተፈናቀሉት ንጹሃኖች በማነጋገር የጦር ወንጀል የተፈጸመው በአከባቢው ይንቀሳቀሱ የነበሩት የ “ትግራይ ሃይሎች” መሆኑን ደርሰንበታል ብሏል።

በተጠቃው አከባቢ ላይ አብዛኛው ነዋሪ በግብርና ስራ የሚተዳደሩ ሲሆኑ ከሳተላይት ምስሎችን በመመልከት ከ50 በላይ ጎጆ ቤቶች መቃጠላቸውንና ቃጠሎዉ ከሃምሌ 26 እለት ጀምሮ መፈጸሙንም ማረጋገጥ መቻሉን የጋዜጣው ሪፖርት ያስረዳል።

ጋዜጠኛው፥ የሳተላይት ምስል ሪሰርች ባለሙያዎች ሪፖርቱ ላይ አብረው መስራታቸውን የገለፀ ሲሆን ተቀማጭነቱ በእንግሊዝ የደረገው የDX Open Network ተቋም ባለሙያዎች ምስሎቹን በማጥናት በንጹዓኖች ንብረት የደረሰው ጉዳት በቅርብ ርቀት እንጂ በአየር ሃይል ድብደባ የተፈጸመ አለመሆኑ አረጋገጠዋል።

የአከባቢ ነዋሪዎች ስለ ወድመቱ ሲጠየቁ በቆቦ ሮቢት እና ዙሪያው በአጠቃላይ 3 መንደሮች ቤት ለቤት በመዞር ወይ ደግሞ በከባድ ብረት ድብደባ መውደማቸው የተናገሩ ሲሆን ለግዜው አንዲት መንደር ሙሉ ለሙሉ መጥፋቱንና ቢያንስ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሲቪል መኖሪያ የነበረ ንብረት ወደ አመድ መቀየሩን ተረጋግጧል።

ይህንን ሪፖርት ተከትሎ ለህወሃት ቃል አቀባይ የሆነው ፍሰሃ ተመስገን የ “ትግራይ ሃይሎች” በንጹሃኖች መኖሪያ እርምጃ ወስደዋል የሚለው “ሙሉ ለሙሉ ሃሰት ነው” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል። (tikvahethiopia)

በሌላ በኩል በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን በአጋምሳ መንደር ላይ የህወሓት የሽብር ቡድን የፈጸመውን ጭፍጨፋ በማጣራት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንደሚያሳውቅ የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ ቤት አስታወቀ፡፡

የሽብር ቡድኑ በየደረሰበት አሰቃቂ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ፈጽሟል ያሉት  የጽ/ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ይህን ድርጊት በማስረጃ አስደግፎ ማሳወቅ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

አሸባሪው ህወሓት በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ የአንድ መንደር ሰዎችን ሙሉ ለሙሉ መግደሉን ተናግረዋል፡፡

ይህም የሽብር ቡድኑ በቆቦ አጋምሳና አካባቢው ላይ የፈጸመው የዘር ፍጅት የቡድኑ የተለመደ ተግባር ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

ይህ የሽብር ቡድን በየደረሰበት ተመሳሳይ ድርጊት እየፈጸመ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ወደፊት ተመሳሳይ የጅምላ ግድያ የተፈጸመባቸውን አካባቢዎች የክልሉ መንግስት እንደሚገልጽ ተናግረዋል፡፡

የአጋምሳውን የጅምላ ጭፍጨፋ አጣርተን ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ እናሳውቃለን ብለዋል፡፡ (በሰለሞን ጸጋዬ)

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Exit mobile version