Site icon ETHIO12.COM

አባዱላ መኪና በመቶ ዶላር !!

“ከለውጡ በፊት አስመጪዎች ከህገወጥ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ጋር ተመሳጥረው መኪና በመቶ ዶላር ያስገቡ ነበር” – አቶ ሙሉጌታ ተመስገን፣ በፋይናንስና ደህንነት መረጃ ማዕከል የተግባርና ክትትል ቡድን መሪ


(ኢ ፕ ድ)
በአገር ኢኮኖሚ ላይ በሚሰራው የተቀናጀ አሻጥር ከለውጡ በፊት አስመጪዎች ከህገወጥ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ጋር ተመሳጥረው አባዱላ መኪና በመቶ ዶላር እስከማስገባት ደርሰው እንደነበር በፋይናንስና ደህንነት መረጃ ማዕከል የተግባርና ክትትል ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ሙሉጌታ ተመስገን ተናገሩ።

ዛሬም በውጭ ያሉ የአሸባሪው ህወሓት ደጋፊዎች በተቀናጀና በተደራጀ መንገድ የኢኮኖሚ አሻጥር መክፈታቸውንም ጠቁመዋል።

አቶ ሙሉጌታ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለው ዋነኛው የኢኮኖሚ አሻጥር ህገወጥ የውጭ ምንዛሬ ዝውውር ነው።

በዚህ ረገድ በወጪና ገቢ ምርቶች ላይ ሰው ሰራሽ የዋጋ ጭማሪ ወይም ቅናሽ በማድረግ የአገሪቱ ካፒታል ተሟጦ ወደ ውጭ የሚወጣበትና አገሪቱ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሬ እንዳታገኝ የሚፈጸም የኢኮኖሚ አሻጥር ያለ ሲሆን፤ በተለይ ከለውጡ በፊት አስመጪዎች ከህገወጥ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ጋር ተመሳጥረው በተለምዶ አባዱላ የሚባለውን መኪና በመቶ ዶላር እስከማስገባት ደርሰው ነበር።

እንደ አቶ ሙሉጌታ ገለጻ፤ በገንዘብ ማጭበርበሩ ስልት ከውጭ የሚገቡ እቃዎችን ወይም ማሽኖችን አርቲፊሻል የዋጋ ጭማሬ በማድረግ ከዋጋቸው በላይ በእጥፍ እንዲገቡ በማድረግ አጠቃላይ በአገሪቱ ያለውን የውጭ ምንዛሬ ጠራርጎ ወደ ውጭ የማሸሽ ስራ ይሰራል። በዚህ ረገድ ከለውጡ በፊት የመንግስት ግዥም ይሁን የግለሰብ እቃ ግዥ ዋጋ ስላልተተመነና የዋጋ ዝርዘር ስላልወጣላቸው፤ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡም ሆነ የሚወጡ ዕቃዎችና ምርቶችን ዓለም አቀፍ ዋጋዎችን ያለማወቅ ሁኔታዎች ነበሩ።

ለአብነት፣ ከውጭ የሚገቡ እቃዎች ከዋጋቸው በላይ በተጋነነ ዋጋ ሲገቡ በዋጋቸውም በጥራታቸውም ላይ ቁጥጥር አይደረግም ነበር። በተለይ ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ጋር ተያይዞ አልሚዎች ያስገቧቸው ማሽኖችና እቃዎች አሮጌ በመሆናቸው በገቡ በአሰርና በአስራ አምስት ቀን ውስጥ ሳይሰራባቸው የወደቁ እቃዎች እንዳሉ ይናገራሉ።
https://www.press.et/ama/?p=54052
ተጨማሪ የመረጃ አማራጮቻችን ‼
ዩቲዩብ 👇
https://youtube.com/channel/UCoH2CVwWn9suWP7q0u2L7MA
ቴሌግራም 👇
https://t.me/ethpress
ትዊተር 👇
https://twitter.com/PressEthio
ድረ ገጽ 👇
https://www.press.et/

Exit mobile version