Site icon ETHIO12.COM

ኪልባቲ ረሱ በራህሌ ወረዳ ሰርጎ የገባ የትህነግ ጭፍራ ንጿህን ላይ ጥቃት ፈጸመ

የአሸባሪው ህወሀት ታጣቂዎች በትናንትናው ዕለት በአፋር ክልል በኪልበቲ ረሱ(ዞን) በራህሌ ወረዳ ዓላ ቀበሌ ዓሰ ዳ የተባለ ቦታ ላይ ጥቃት የፈፀሙ ሲሆን ጥቃቱን ለመመከት የአፋር ልዩ ሀይል እና ሚሊሽያ ተገቢውን ምላሽ በመስጠት የያዘውን መሳሪያ አንጠባጥቦ እግሬ አውጭኝ ብሎ ፈርጥጦ ነበር።

በዛሬው ዕለት በተመሳሳይ ቦታ ከሌሊቱ 11 ሰአት ላይ ድጋሚ ወረራ ያካሄደ ሲሆን ወደ አርብቶ አደር ማህበረሰብ ሴቶችና ህፃናት ላይ በከባድ መሳሪያ የታገዘ ተኩስ ከፍቷል።

ይሁንና ጀግኖቹ የአፋር ልዩ ሀይልና ሚሊሽያ ዛሬም ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ወረራውን የመመከት ስራ በመስራት ላይ ይገኛሉ ሲል የክልሉ የመንግስት ኮምንኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታውቋል።።

አሸባሪው የህወሀት ጁንታ የአፋርን መሬት ለመቀራመት እና ወደ ትግራይ ክልል ለማካለል፣ ከዚያም ሪፐብሊክ ለመመስረት ያለውን የረጅም ጊዜ ህልም ለማሳካት የአፋርን ህዝብ በመውረር ከፍተኛ የሆነ ቀውስ ማድረሱ ይታወቃል።

ጁንታው ወደ አፋር ክልል ወሰን ሰርጎ በመግባት ህፃናትን፣ አዛውንቶችን፣ ሴቶችን ያለምንም ርህራሄ ዘግናኝ ጭፍጭፋ ለዚያውም ሌሊት ጠብቆ ንፁሀንን ፈጅቷል። በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ አርብቶ አደሮችን ከቀያቸው አፈናቅሎ ለበርካታ ችግሮች ሰለባ አድርጓል።

አሸባሪው ህወሀት በአፋር ክልል ፈንቲ ረሱ በኩል ያደረገው ወረራ አልበቃ ብሎት ትናንትና ዛሬ በኪልበቲ ረሱ/ዞን በራህሌ ወረዳ በኩል ሰርጎ ለመግባት ሙከራ አድርጎ ወደ ንፁሀን አርብቶ አደር ማህበረሰብ ላይ ጦርነት ከፍቷል።

የሽብር ቡድኑ አሁንም ቀቢፀ ተስፋውን ለመሞከር በተለያዩ አቅጣጫዎች ትንኮሳ የማድረግ ሙከራ እያደረገ በመሆኑ ህዝቡ በአቅራቢያው ከሚገኙ የፀጥታ ሀይሎች ጋር በመተባበር በንቃት በመጠበቅ ሰላሙን ሊያረጋግጥ ይገባል ሲል ቢሮው አስታውቋል።

በተመሳሳይ ሌላ የእረፋና ንጹሃንን የመጨፍጨፍ ዜና

ወራሪው ትህነግ ተራ ዝርፊያና ግድያ እየፈፀመ መሆኑን የአማራ ክልል መንግስት አስታወቀ።

ክልሉ የህልውና ዘመቻውን ህዝባዊ ማድረጉን ተከትሎ ዝርፊያና ግድያው ጠላት በሁሉም ግንባሮች እየደረሠበት ባለው ሽንፈት ተስፋ መቁረጡን ማሳያ ስለመሆኑ የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ገልፀዋል።

የህልውና ዘመቻውን ህዝባዊ ማድረግ መቻሉ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ያስቻለ በመሆኑ ወጣቶች ግንባር በመዝመት፣ ማህበረሠቡ በስንቅ ዝግጅትና ደጀንነት የሚጠበቅበትን እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ዳያስፖራው ገንዘብ በማሠባሠብና የዓለም ማህበረሠብን የተዛባ አመለካከት ለመቀየር እንዲሠሩ የተሠጣቸውን ተልዕኮ እየተወጡ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

በየግንባሮቹ በጠላት ላይ እየደረሠ ያለው ሠብዓዊና የቁሳቁስ ኪሳራ ምክንያት ተስፋ በመቁረጥ ላይ ለመሆኑ እያደረሠ ያለው ዝርፊያና ጅምላ ግድያ ማሳያ መሆኑንም ነው የገለጹት።

ጠላት ሠርጎገቦችን ወደ ክልሉ በማስገባት እና የፕሮፖጋንዳ ስራዎች ከጦርነቱ ባልተናነሠ እየሠራ ቢሆንም እስከመጨረሻው የድል እወጃ ድረስ ሁሉም የድርሻውን እየተወጣ በመሆኑ ሊሳካ አልቻለም ነው ያሉት።

በዘመቻው ህዝባዊነት ወጣቶች ሠርጎ ገቦችን ለህግ የማቅረቡ ሂደት መረጃ የማጣራት ብስለትና ትዕግስት እንዲታከልበት ጥሪ ማቅረባቸውን ኢብኮ ዘግቧል።

Exit mobile version