Site icon ETHIO12.COM

ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ በመገንዘብ የንግዱ ማህበረሰብ ገበያውን ማረጋጋት ይጠበቅበታል

ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ በመረዳት ከትርፍ በላይ አገርና ህዝብን በማስቀደም የንግዱ ማህበረሰብ ገበያውን የማረጋጋት ተግባር ማከናወን እንደሚጠበቅበት ተገለጸ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኑሮ ውድነትን አስመልክቶ በምክንያቶችና መፍትሄዎቻቸው ላይ ከከተማዋ የንግዱ ማህበረሰብ ጋር ዛሬ ተወያይቷል።

ለውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የአዲሰ አበባ ንግድ ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዱልፈታ የሱፍ የንግዱ ማህበረሰብ አገርን ለመገባት ለግዙፍ ፕሮጀክቶች፣ ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ በማድረግና ኮቪድ-19ኝን ለመከላከል እያከናወነ ያለውን አስተዋጽኦ አውስተዋል።

ይሁን እንጂ አገርን ለማፍረስ የተነሳው አሸባሪው ህወሃትና ሌሎች የውጭ ሃይሎች የፈጠሩትን ጫና እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ኢ-ፍትሃዊ የዋጋ ድርድር በመፍጠር ገበያውን ለመቆጣጠር የሚሰሩ መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በተለይም በቂ ምክንያት ሳይኖር ዋጋ የሚጨምሩ፣ ምርት የሚያከማቹ፣ የግብይት ሰንሰለቱን የሚያራዝሙና ሌሎች የዋጋ ንረት እንዲፈጠር በማድረግ ህገ-ወጥ ተግባራትን የሚያከናውኑ መኖራቸውንም አብራርተዋል።

ከተከፈተው ጦርነት ባልተናነሰ ሁኔታ ጦርነቱን በሚመግብ መንገድ ከፍተኛ የንግድ አሻጥር እየተከናወነ በመሆኑ መታገል እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

“መነገድ፣ ማትረፍ፣ ማደግና መኖር የሚቻለው አገር ሰላም ሲሆን ብቻ ነው” ያሉት አቶ አብዱልፈታ፤ ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ ተገንዝቦ ለአገር ሉዓላዊነት በጋራ መቆም እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

በተለያዩ ጊዜያት ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ተመሳጥረው የዋጋ ንረት እንዲፈጠር የራሳቸውን አሉታዊ አስተዋጽኦ እያደረጉ ያሉ የንግድ ቢሮው ሰራተኞች በህግ እየተጠየቁ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙ ነጋዴዎች በበኩላቸው ገበያውን በማረጋጋትና የምጣኔ ሃብት አሻጥሮችን በማጋለጥ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

“ህጉ በሚፈቅደውና በተመጣጣኝ ሁኔታ መንግስት እርምጃዎችን እየወሰደ ነው፤ ከወሰደ በኋላ ህዝቡ እንዲያውቃቸው ቢደረጉ” ሲሉ ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የገጠማትን ችግር ለመሻገር ወሳኝ ምዕራፍ ላይ በመሆኗ በአንድነት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

አገርን ለማፍረስ የተነሳው አሸባሪው የህወሃት ቡድን የከፈተው ጦርነት በመሳሪያ ብቻ ሳይሆን ከውስጥም ከውጭም ካሉ ሃይላት ጋር በመናበብ የምጣኔ ሃብት ጦርነት እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ስለዚህ ኢትዮጵያ ያለችበትን ፈታኝ ወቅት ከግምት በማስገባት ነግዶ ለማትረፍ ብቻ ሳይሆን አገርን በትብብር ለማዳን ሃላፊነት መውሰድ እንደሚያስፈልግም አስግንዝበዋል።

በጦር ግንባር የአገራቸውን ሉዓላዊነት ለማስከበር እየተፋለሙ እንዳሉት ሁሉ ገበያውን በማረጋጋት፣ ማዕድ በማጋራት፣ ህገ-ወጥ ተግባራትን በማጋለጥና የምጣኔ ሃብት አሻጥር ውስጥ ባለመግባት እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

ምክትል ከንቲባዋ በመንግስት በኩል ህገ-ወጥ አሰራሮችን ለመቆጣጠርና ገበያውን ለማረጋጋት እስከ ወረዳ ድረስ ከተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት የተውጣጣ አደረጃጀት መዘርጋቱን ጠቁመው፤ ህብረተሰቡ ኢ-ፍትሃዊ አሰራሮች ሲያጋጥሙ ጥቆማ የሚሰጥበት ስርአት በቀጣይ ሳምንት ይፋ እንደሚሆን ተናግረዋል።

አዲስ አበባ ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚሆነው የንግዱ ማህበረሰብ መናኽሪያ በመሆኗ በንግድ ስርዓቱ ውስጥ የሚፈጠሩ ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን በማምከን ወደ ሌሎች የአገሪቷ ክፍሎች እንዳይዛመቱ ያግዘል ተብሏል።

ENA

Exit mobile version